የትምህርቱ ርዕስ | ሕያው ርእስ

“… እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው ።” ኤፌ. 1፡12።

መናገርም መስማትም የማይችል ፣ አካሉም ለመሥራትና ለመንቀሳቀስ ደካማ የሆነ ወጣት ነው ። ይህ ወጣት በምልክት ቋንቋም ለመነጋገር ያንን አልተማረም ። ካለበት ገጠር መጥቶ በሰለጠነው ከተማ ተቀመጠ ፣ ወትሮም እዚህ ተወልዶ ገጠር ያደገ ነበር ። አንድ ቀን ብስጭት ብሎ ከቤተሰቡ ተጣልቶ ወጣ ። እንደ ልማዱ ሲበርድለት ይመለሳል ብለው ቢጠብቁት እንደ ወጣ ቀረ ። ዓመታት በተቆጠሩ ቍጥር ጥፋቱ የእኔ ነው የሚል ራሱን የሚከስስ በቤተሰብ ውስጥ መፈጠር ጀመረ ። “ያን ቀን ምነው ባልተናገርኩት” የሚል ጸጸተኛ ብቅ እያለ መጣ ። ከሁሉም በላይ እናት እህ እያሉ የአልጋ ቁራኛ ሆኑ ። አየሁ ሰማሁ ፣ ያየሁ መሰለኝ የሚል ምልክት በተገኘበት ሁሉ መሮጥ የዚያ ቤተሰብ ሥራ ሆነ ። ገና ከጠዋቱ ዕድሉ ለመከራ ተጽፎ ፣ በሽታና እንግልት የተፈራረቁበት በመሆኑ የሚያውቀው ሁሉ ማዘን ጀመረ ። ቤተሰቡም ጭንቀቱ እየበረታ ሲመጣ “አንቺ ነሽ” “አንተ” በሚል መካሰስ ውስጥ ገባ ። “አዲሱ ሬሳ የቆየውን አሥነሣ” እንዲሉ ከልጅነት ጀምሮ እየተረኩ ለመጣላት የተዘጋጁ መሰሉ ። በዚህ ሁሉ ጭቅጭቅ ውስጥ ሁሉም በየራሱ ወጣ ብሎ ፈልጎ ይመለሳል ። ያ ወጣት ግን ሕልም እልም ሁኗል ። “ቀብሬው ቢሆን ኖሮ አይቆጨኝም ነበር ፣ ከዘመድ ጋር አልቅሼ ይወጣልኝ ነበር” የሚል ድምፅ እየጨመረ መጣ ። “ደኅና ነዎት ወይ?” ስላቸው እኒያ እናት፡- “ምን ደኅና ነኝ ፣ ልጄ አብሉኝ አጠጡኝ እንኳ እንዳይል አንደበት እንኳ የለው ፣ ይህን ሳላይ ምነው በሞትሁ” ይላሉ ።

አንድ ታላቅ ገዳም ቆይቼ ለዓይን ያዝ ሲል በምሽት ጉዞ ጀመርሁ ። ቤተ ክርስቲያኑን አለፍ እንዳልሁ የሚለምኑ ድሆች በቀኑ ውሎአቸው ተስፋ ቆርጠው ይሆን ተስፋ አድርገው ለመተኛት ይሰናዳሉ ። ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ውለው ፣ አፈር ላይ ለመተኛት ሲሰናዱ በጨለማው ውስጥ በጥቂቱ ይታያሉ ። እኔም ግራ ቀኙን አማተርሁ ። ድንገት አንድ ወጣት መኝታውን እያነጠፈ ፣ አፈር ከመሰለው መልኩ ጋር አፈር የመሰለ ልብስ አፈር ላይ ያነጥፋል ። ልብሱም ከአፈር አይሻልም ፣ አፈርን ለመሸሽ አፈር ላይ አፈር መሳዩ ያነጥፋል ። አፈር ሰው ፣ አፈር መሳይ ልብስ ፣ የልብሱና የሰው መገኛ የሆነው አፈር በደንብ ይታዩኛል ። መኝታውን እያነጠፈ ወደ ግራ ዞር ብሎ ፈገግ እያለ ያየናል ። አዝነን ብንሰጠው ተመኝቶ ቀኑን ከመዝጋቱ በፊት እንድ ምጽዋት ናፍቆ ይሆናል ። እኔም ልቤ ደነገጠ ። ያየሁትን ማመን አቃተኝ ። እንዳያውቀኝ ዞር ለማለት ሞከርሁ ። ያ የጠፋው ልጅ ነው ። ስልክ አነሣሁና ወንድሙ ጋ ደውዬ “ወንድምህ ተገኘ ወይ” ብለው “በፍጹም” አለኝ ። “አገኘሁት” ስለው ስልኩን ሌሎች ቤተሰቦች ነጥቀው ጠየቁኝ ። በፍጥነት እየበረርን አዲስ አበባ መጣን ። ሰዓቱ ከምሽቱ 2፡30 ሆኗል ። ቤቱ በጎረቤት ተሞልቷል ። ወንድሙም ጥሩ ልብስ አዘጋጅቶ ፣ ድሬቶዬን አልጥልም ቢልስ ብሎ መያዣ ነገር ከረጢት አዘጋጅቶ ነበርና በመጣንበት ፍጥነት ሄድን ።

ያንን ወጣት ሲያነጥፍ አይቼዋለሁና ባትሪ አበራንበትና አሥነሣነው ። እኛ መሆናችንን ሲያውቅ የሚሆነውን አጣ ። መሬት ላይ ይወድቃል ፣ ይነሣል ። በዙሪያው የነበሩ ድሆች በሙሉ ማልቀስ ጀመሩ ። ወንድሙም ከደስታውና ከመተቃቀፉ በኋላ ልብሱን በሙሉ ቀየረለት ። የፈራው አልቀረም ፣ ድሪቶዬን አልጥልም አለ ። ድሪቶውን ከኋላ ጭነን እርሱን ከፊት አስቀምጠን ለመሄድ ስንነሣ ድሆቹ ወገኖቻችን፡- “ምነው እኛንም እንዲህ የሚሰበስበን ባገኘን” ብለው ስንሄድ ምርቃትም ምኞትም አስተላለፉልን ። ለካ ያ ልጅ የእናቱን ቤት ያገኘ እየመሰለው ሲጓዝ መመለስ አልቻለም ነበር ። እቤት ስንደርስ እገሌ ተገኘ ተብሎ ሰው ሁሉ እንቅልፉን ትቶ ወጥቶ እየጠበቀን ነው ። የእናቱን ቤት የተከራዩ ብዙ ተከራዮች ከነልጆቻቸው ወጥተው እየጠበቁን ነው ። ደስታው ምስጋናው ድብልቅልቁ ወጣ ። እኔንም ሁሉም እየተነሣ ያቅፈኛል ፣ ያመሰግነኛል ። ፈልጌ እንዳገኘሁት ተቆጠርሁ ። በዚያ ጨለማ እንዴት ላየው እንደ ቻልሁ አምላክ ብቻ ያውቀዋል ። ተገኝ ሲለው መላ ያዝለታል ከማለት ውጭ ምን ይባላል ? ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያቺን ቀን እያስታወሱ ያመሰግኑኛል ፣ ላልሰማ እርሱ ነው እያሉ ይመሰክሩልኛል ።

ለካ አዳም ትእዛዝን ባለመስማቱ ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር ባለማየቱ ጠፍቶ የነበረው እንዲህ ነው ። ለሰማይ መዳረሻ ተፈጥሮ ሳለ አሁን ግን የመጣበትን አፈር ሲያርስ ኖሮ መልሶ አፈር ይሆናል ። የሕይወት ታሪኩ ሲነበብም “ከአፈር ተፈጥሮ ፣ በአፈር ሲጫወት ኖሮ ፣ ወደ አፈር ተመለሰ” የሚል ነው ። ይህ ግን የእግዚአብሔር አሳብ አልነበረም ። አዳም በጨለማው ፣ በመቃብሩ ፣ በአፈር መኝታው በተገኘ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት የሰማይን ደጅ ከበው ይጠብቁ ነበር ። ሁሉ እያለው ሁሉ የሌለው ሁኖ በመኖሩ ፣ እመለሳለሁ ሲል መጥፋቱ ፣ ደረስሁ ሲል መራቁ በሰማይ ኀዘን ፈጥሮ ነበር ። አዳም በአጋጣሚ አልተገኘም ። አዳም በታላቅ ፍለጋ ፣ በደም ዋጋ ተገኘ ። የተገኘው አዳም በታየ ቍጥር ያገኘውን ክርስቶስ ሲያመሰግኑት ፣ ሲስሙት ፣ ሲመሰክሩለት ይኖራሉ ። አዳም ለክርስቶስ ምስጋና ሕያው ርእስ ነው ።

ሐዋርያው እንዲህ አለ፡- “… እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው ።” ኤፌ. 1፡12።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /22

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም