የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰው ምን ያደርገኛል ?

“በእግዚአብሔር ታመንሁ ፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል ?” መዝ. 55፡11
በአንተ ላይ እደገፋለሁ ። በአንተ ላይ እደላደላለሁ ። ምሰሶዬ አንተ ነህ አትነቃነቅም ። ከስፍራህ አትታጣም ። ስደገፍህ የማትሰበር ምርኩዜ አንተ ነህ ። ስጠጋህ የማትሸሸኝ ወዳጄ አንተ ነህ ። ከፍ የምልብህ ደብሬ አንተ ነህ ። ካንተ አግኝቻለሁና ከሰው አጣሁ ብዬ አላዝንም ። ባንተ ተክሻለሁና ከሰርሁ ብዬ አላጉረመርምም ። የቤቴ ብርሃን ፣ የትዳሬም ዘውድ አንተ ነህ ።የበረታው ሲደክም ፣ የተሾመው ሲሻር አንተ ግን በዘመናት ያው ሁነህ አይሃለሁ ። ያለመድኩት ጠባይህ ፣ ይህ ብቻ ነው ብዬ ያልገለጥሁት ማንነትህ የተመሰገነ ይሁን ። አንተ ልዑል ስትሆን የምረገጥ ጭቃ የሆንሁት እኔ አመሰግንህ ዘንድ መፍቀድህ በእውነት በመደነቅ እንዳመሰግንህ ያደርገኛል ። የገዛ አቅሜ ሲከዳኝ በእርጅናዬ የማትጥለኝ ጓዴ አንተ ነህ ። እስከ ማታ ይቆያል ያሉት በጥዋቱ ሲያልቅ አንተ ግን እንደ በዛህ ትኖራለህ ። በክፉ ቀን ይቆምልኛል የምለው ራሱ ክፉ ቀን ሲሆን አንተ ግን በፍቅር ቅላፄ ታናግረኛለህ ። ያየኸው እንጂ የገላመጥኸው ማንም የለም ። ፊትህን ስትመልስ እደነግጣለሁ ፣ ስምህን ስጠራ ወዲያው አይዞህ ትለኛለህ ። ደስታዬን ፈውሰህ ባንተ እንድደሰት ስለረዳኸኝ ፣ ነፍሴ ከእውቀት ተራቁታ እንዳታስቸግረኝ በብዙ ትምህርት የደገፍከኝ አንተ እንደሆንህ አውቃለሁ ። በዚህ ዘመን ስላስነሣሃቸው አባቶችና ካህናት ምስጋና አቀርብልሃለሁ ። በሚክዱት መሐል አማኝ ለመሆን የበቃነው ባንተ ቸርነት ነው።
መሠረቴ አንተ ነህ ። ከመነቃነቅ ከመነቀል ትጠብቀኛለህ ። ነፋሱ እንዳይጥለኝ ሥር ሁነህ የያዝኸኝ ፣ ከልጅነቴ ጀምሮ የደገፍከኝ አንተ ነህ ።የዓለቱ መሠረት ጸንተህ የምታጸናው ሆይ ተመስገን ። የሰው ልጆች መናወጥ በዝቷልና ። ብዙ ኑሮም በጭካኔ ይፈርሳልና ለምን ዝም አልከን ። እባክህ ተለመነን ። አንተ ከጨከንህብን የሚራራልን ፣ አንተ ካለፍከን የሚያየን ማንም የለም ። በሰፊ አገር ላይ የታሰርን እስረኞች እንዳንሆንብህ እባክህ አስበን ። ለምን ዓይነት ቀን እየተዘጋጀን እንደሆነ አናውቀውም ። ጊዜ ከተገኘ ሁሉም ገዳይ ነውና እባክህን መልሰን ። የምንሠራውን አሳውቀን ። ሰው ለሰው ደስታው እንጂ ኀዘኑ አይሁን።
ባንተ ከታመንሁ ምን እፈራለሁ ? የምፈራው ራሱ ካንተ የተነሣ ይፈራል ።እምነቴም ድፍረቴም አንተ ሁንልኝ ። ፍጹም ፍቅር ከፍርሃት ያድናልና ፍጹም ፍቅር ስጠኝ ። ማመኔን እስከ መጨረሻው ባንተ አድርግልኝ ። ለዘላለሙ አሜን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ