የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ ስለ እምነትና መስቀል

 

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም.

www.ashenafimekonen.blogspot.com

መስቀል የሚለው ቃል “ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው . . . ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።” /1ኛ ቆሮ 1÷18፣ 1ኛ ቆሮ 2÷14-14/  በእምነት ለማይቀበሉት፣ የእግዚአብሔርን መልካምነትና ሁሉን ቻይነት ለማያምኑ በተቃራኒው መለኮታዊ የሆነውን ነገር ሰዋዊና ተፈጥሮአዊ በሆነ አመክንዮ ለሚመረምሩ ሞኝነት ነው።  ከእግዚአብሔር የሆኑት ነገሮች ሁሉ ከተፈጥሮ፣ ከምክንያትና አሳብ በላይ ናቸው። አንድ ሰው እግዚአብሔር እንዴትና በምን ምክንያት ሁሉንም ነገር ከምንም ወደ ሕያውነት እንዳመጣ ቢጠይቅና መልሱን በተፈጥሮአዊ ምክንያት መድረስ ቢያልም ሊረዳውና ሊገነዘበው አይቻለውም። እንዲህ ያለው እውቀት የተሰጠው ለመናፍስቱ ነውና። ነገር ግን አንድ ሰው በእምነት እየተመራ መለኮታዊውን መልካምነት፣ ሁሉን ቻይነት፣ እውነት፣ ጥበብና ፍትህ ቢያስብ ሁሉም ነገሮች የተቃኑ ብሎም ፊት ለፊት ሆነው ያገኛቸዋል። “ያለ እምነትም መዳን አይቻልምና” ። ሁሉም ነገሮች ሰዋዊ ይሁን መንፈሳዊ የሚጸኑትና የሚቀጥሉት በእምነት ነውና። ያለ እምነት ገበሬው አያርስም፣ ነጋዴውም ትንሿን እንጨት አምኖ ሕይወቱን ለማዕበል አሳልፎ አይሰጥም፣ ጋብቻም አይመሠረትም አልያም የትኛውም ውሳኔ አይወሰንም። ነገር ግን በእምነት ሁሉም ነገሮች በእግዚአብሔር ኃይል ከምንም ወደ ሕይወት እንደመጡ እንቀበላለን። ከዚህ በተጨማሪ እምነት ከጣልቃ ገብ ምርመራዎች ሁሉ የራቀና ነጻ የወጣ ነው። 

ስለዚህ የክርስቶስ ሁሉም ተግባራትና ተአምራት እጅግ ታላቅ፣ ድንቅና መለኮታዊ ናቸው። ነገር ግን ከሁሉም የሚደንቀው እጅግ ውድና ክቡር የሆነው መስቀል ነው። ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በስተቀር ሞትን ያሸነፈ፣ የቀደምት ቤተሰቦቻችን ኃጢአት ያስተሰረየ፣ ሲኦልን የበዘበዘ፣ ትንሣኤን የሰጠ፣ አሁንም ሞትን በንቀት እንድንመለከት ኃይል የሰጠ፣ ወደ ቀድሞ ቅድስናችን መመለስን ያዘጋጀ፣ የገነትን በር የከፈተ፣ ባሕርያችን በእግዚአብሔር ቀኝ እንዲቀመጥ ያደረገ፣ የእግዚአብሔር ልጆችና ወራሾች ያደረገን ሌላ የለም። በመስቀሉ ሁሉም ነገር ተስተካከለ፤ ደህናም ሆነ። ሐዋርያው እንዲህ አለ “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?” ሮሜ 6÷3 “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።” ገላ 3÷27 ከዚህ በተጨማሪ ክርስቶስ “የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ።” 1ኛ ቆሮ 1÷24 የክርስቶስ ሞት ማለትም መስቀሉ የእግዚአብሔርን ጥበብና ኃይል አለበሰን ። የእግዚአብሔር ኃይል የመስቀሉ ቃል ነው፣ ይህም የእግዚአብሔር ኃይል ማለትም ሞትን ማሸነፍ በመስቀል በኩል ነው የተገለጸልን። አሊያም  የመስቀሉ አራት ጫፎች መሐል ላይ ባለው በአንድ ችንካር እንደሚጣመሩት ልክ እንደዚሁ በእግዚአብሔር ኃይል ከፍታውና ዝቅታው፣ ቁመቱና ስፋቱ፣ ማለትም የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት በሙሉ ይጠበቃሉ ፣ መግቦትንም ያገኛሉ። 

ልክ ግርዛት ለእስራኤላውያን እንደ ምልክት እንደተሰጣቸው ይህም ለእኛ እንደ ምልክት ግንባራችን ላይ ተሰጠን። በእርሱ እኛ አማኞች ከኢአማንያን እንለያለን። ይህ ከሰይጣን ለሚመጣው (ጦርነት) ጋሻና ጦር፣ ብሎም ሽልማት ነው ። መጽሐፉ እንደሚለው አጥፊው እንዳይነካን  (የምንጠበቅበት) ምልክት ነው። ይህ ለሞቱት ትንሣኤ፣ ለቆሙት ደጋፊ፣ የደካሞች ምርኩዝ፣ የመንጋው (መጠበቂያ) በትር፣ የቅኖች መልካም ምግባር ፣ ወደ ፊት ለሚጓዙት ፍጹምነት፣ የነፍስና የሥጋ ድኅነት፣ ክፉ የሆኑ ነገሮች ሁሉ መራቂያ፣ መልካም የሆኑ ነገሮች ሁሉ ጠባቂ ፣ የኃጢአት ሥርየት፣ የትንሣኤ ዕፅ፣ የዘላለም ሕይወት ዛፍ ነው።  

ስለዚህ ክርስቶስ ራሱ ስለ እኛ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ይህ በእውነት ክቡር የሆነው መስቀል ፣ ከቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ጋር ተገናኝቷልና ሊከበር ይገባዋል። ልክ እንደዚሁ ምስማሮቹ ፣ ጦሩ ፣ አልባሳቱ ፣ ቅዱስ ድንኳኑ ማለትም (የተወለደበት) ግርግም ፣  ዋሻው ፣ ድኅነትን የሰጠበት ጎልጎታ ፣ ሕይወትን የሰጠው መቃብር፣ የቤተ ክርስቲያን መከለያ የሆነችው ጽዮን እነዚህ ሁሉ ሊከበሩ ይገባቸዋል። በሥጋ የወልደ እግዚአብሔር አባት የሆነው በዳዊት ቃላት መሠረት “ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን”። መስቀሉ “አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” በሚለው ቃል ግልጽ የሆነ ነው።  ትንሣኤው ከመስቀሉ በኋላ የመጣ ነውና። የምንወዳቸው እንደ ቤት፣ አልጋና ልብስ ያሉ ነገሮችን የምንናፍቃቸውና የምንወዳቸው ከሆነ ፣ የእውነት ድኅነት ያገኝንበትን የእግዚአብሔር የአዳኛችን የሆነውን መስቀል አንናፍቅም አንወድምን ? 

ከዚህ በተጨማሪ ሕይወት ሰጪ የሆነውን መስቀል ሥዕልም እናከብራለን። ምንም እንኳን ከሌላ እንጨት የተሠራ ቢሆንም የምናከብረው እንጨቱን ሳይሆን ሥዕሉን እንደ ክርስቶስ ምሳሌ በመመልከት ነው። “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል” /ማቴ 24÷30/ ይህም ማለት መስቀሉ ማለት ነው። ልክ እንደዚሁ የትንሣኤው ዕለት መልአክ ሴቶቹን እንዲህ አላቸው “የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ” ማር 16÷6። ብዙ ክርስቶሶች ብዙ ኢየሱሶች ያሉ ቢሆንም የተሰቀለው ግን አንዱ ነው። ተሰቀለ አለ እንጂ (በጦር) ተወጋ አላለም። በዚህም የመስቀልን ምልክት እንድናከብር ያሳስበናል። ምልክቱ ያለበት የትኛውም ቦታ እርሱ አለ። ነገር ግን የመስቀል ምልክት የተቀረጸበትን ቁስ ከወርቅ የተሠራ ይሁን ከከበረ ድንጋይ እንድናከብር የሚያሳስበን አይደለም፣ እነዚህ ይጠፋሉና። ስለዚህ ለእግዚአብሔር የተሰጠውንና የዋለውን ነገር ሁሉ ክብሩን ለእርሱ (ለእግዚአብሔር) በመስጠት እናከብረዋለን።

በገነት በእግዚአብሔር የተተከለው የሕይወት ዛፍ ይህንን ውድና ክቡር መስቀል አስቀድሞ አሳይቷል ፣ ምሳሌውም ነበር። ሞት የገባው በእንጨት ነበርና ፣ ሕይወትና ትንሣኤም በእንጨት ይሰጥ ዘንድ የተገባ ነው። ያዕቆብ የዮሴፍን ቀሚስ በሚያሸትበት ወቅት መስቀሉን ያመላከተ የመጀመሪያው ሰው ነበር። ልጆቹንም እጆቹን አመሳቅሎ በሚባርክበት ጊዜ እጅግ ግልጽ በሆነ መልኩ የመስቀል ምልክትን አደረገ። የሙሴ በትርም ልክ እንደዚሁ አደረገ፣ እርሱ ባሕሩን በበትሩ በመስቀል አምሳል በመታበትና እስራኤልን ባዳነበት ጊዜ ፈርዖንን በጥልቁ አሰጠመው። ልክ እንደዚሁ እጁን በመስቀል ምልክት አመሳቅሎ በዘረጋ ጊዜ አማሌቃውያንን አሸነፈ። መራራው ውኃ ጣፋጭ የሆነውም በእንጨቱ ነበር፣ ዓለቱም የተከፈለውና የውኃ ምንጭ ያወጣውም በእንጨቱ ነበር። የሊቀ ካህኑ የአሮን ክብር የነበረው ይህ እንጨት ነው ። (የናሱ) እባቡ ልክ እንደ ሞተ ሆኖ እንጨት ላይ የተሰቀልው በድል ነበር፣ ይህም ጠላቶቻቸው በእምነት እንደሞቱ ለተመለከቱ ድኅነትን የሚያሰጥ እንጨት። ልክ ክርስቶስ ኃጢአትን ሳያውቅ በኃጢአተኛ ሥጋ (ምሳሌ) እንደተሰቀለው። ታላቁና ኃያሉ ሙሴ እንዲህ እያለ ጮኸ “ነፍስህም ታመነታለች፤ ሌሊትና ቀንም ትፈራለህ፥ በሕይወትህም አትታመንም” (ዘዳ 28÷66) ኢሳያስም እንዲህ አለ “መልካም ባልሆነው መንገድ፥ አሳባቸውን እየተከተሉ፥ ወደሚሄዱ ወደ ዓመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሁሉ እጆቼን ዘረጋሁ” (ኢሳ 65÷2)። ይህንን የምናከብር እኛ ከተሰቀለው ክርስቶስ እንድንካፈል ይሁንልን አሜን!

ያጋሩ