የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

…ነገር ግን…

“ነገር” አለ ፣ “ግን”ም አለ ። የፊት “ነገር” አለ ፣ የኋላ “ግን” አለ ። የተናገሩለት ረጅም “ነገር” አለ ፣ ዝም የሚያሰኝ ደግሞ “ግን” አለ ። በኩራት ያናገረ “ነገር” አለ ፣ የሚያሳፍር “ግን” አለ ። ዕድሜ ጠገብ “ነገር” አለ ፣ አላሳልፍ የሚል “ግን” አለ ። “ነገር” ባይኖር “ግን” አይኖርም ። “ግን” ባይኖርም ደጉ “ነገር” አይመሰገንም ። “ነገር” አዎንታዊ ነው ፣ “ግን” አፍራሽ ነው ። ሁለቱ ግን ተለያይተው አያውቁም ። “…ነገር ግን…” እየሳቁ ማልቀስ ፣ እያነቡ እስክስ ማለት ነው ።

ሰው “ነገር” አለው ፣ መልካም ነው ። ሰው “ግን” አለው ፤ ሰው ክፋት አለው ። ሰው “ነገር” ነው ፣ ይነበባል ፤ ሰው “ግን” ነው የማይፈታ ቅኔ ይሆናል ። ሰው “ነገር” ነው ፣ ያውቁታል ፤ ሰው “ግን” ነው ሳያውቁት ይሞታል ። ሰው “ነገር” ነው አፈር ልብላልህ እያለ ያጎርሳል ፣ ሰው “ግን” ነው ፣ አፈር ያበላሃል ። ሰው “ነገር” ነው ፣ ስለ ሰፊነት ያወራሃል ፤ ሰው “ግን” ነው ፣ ጠባብነትን ይኖረዋል ። ሰው “ነገር” ነው ፣ ቤተ ክርስቲያን ይሳለማል ፣ ሰው “ግን” ነው ፣ ከቤተ ክርስቲያን ተመልሶ ሰፈር ሲያውክ ይውላል ። ሰው “ነገር” ነው ፣ ዝክር ይጠራሃል ፣ ሰው “ግን” ነው ፣ መታሰቢያህን ያጠፋዋል ። ዛሬ “…ነገር ግን…” ናት ። በወጣው ፀሐይ ደስ ይልሃል ፣ በጨለሙ የወዳጅ ፊቶች ይከፋሃል ።

አገር “…ነገር ግን…” ናት ። የእኛ ናትና ታስደስተናለች ፣ የእናንተ አይደለችም በሚሉ ደግሞ ታደናግረናለች ። መሪዎች “…ነገር ግን…” ናቸው ፣ “ነገር” ሁነው የምንፈልገውን ያውሩልናል ፣ “ግን” ሁነው የሚፈልጉትን ይጭኑብናል ። አድናቂዎች “ነገር ግን” ናቸው ። እየለመኑ መጥተው እየተሳደቡ ይሄዳሉ ። “ነገር” ሦስት ፊደል ናት ። “ግን” ሁለት ፊደል ነው ። “ግን” ሁለት ፊደል መሆኑ ዓለም ሁለት ነው ማለቱ ነው ። ዓለም “ግን” ነው ። “ግን…” አፍራሽ ቃል ነው ፤ ዓለም የአፍራሽ ፣ የፈራሽ ፣ የፍራሽ ስፍራ ናት ። “…ነገር ግን…” የሕይወት መገለጫ ነው ፣ የኋላው ክፉ የፊቱን መልካም ነገር እንዳያስረሳን መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። “…ነገር” ከሚለው በፊት መልካም አለ ፣ “ግን…” ከሚለው ለጥቆም ክፉ አለ ። መርጦ መስማት የሰው ምርጫ ነው ።

ጌታ ሆይ ! አንተ ግን የሕይወት ቃል አለህ ። ጨርሶ የሞላለት ፣ ፈጽሞ የጎደለበት የለም ። አንተ ግን አንድ መልክ ያለውን ዓለም ታወርሰናለህ ። የተቀደሰው ስምህ ይቀደስ ። እኛም እንቀደስ ዘንድ ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ