“የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር ፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው ?” ገላ. 3፡1 ።
እያየሁ የማላይ ፣ እየሰማሁ የማላስተውል ፣ እያነበብሁ የማልጠነቀቅ ነኝና ወልድ ሆይ እባክህ በማስተዋል ባርከኝ ። አንተን በማይበት ዘመን ባሕር ጸንቶልኝ ፣ ወጀብ ተቀዝፎልኝ ፣ ፍርሃት ድል ተነሥቶልኝ ፣ ጨለማው በርቶልኝ ተራምጃለሁ ። ዓይኔን ካንተ ፣ ጆሮዬን ከቃልህ ስመልስ ግን ጨለማው እየዋጠኝ ፣ የራሴ ድምፅ መልሶ እየተሰማኝ ተናውጫለሁ ። እባክህ ዓይኔ አንተን እንዳየች ትቅር ። ጆሮዬም አንተን እንደ ሰማች ትቅር ። ድኜ እንዳልቀር ዓይኔን ካንተ እመልሳለሁ ፣ ጆሮዬንም ከቃልህ አርቃለሁ ። የአማኝ ፈሪ ፣ የክርስቲያን ዓለም አፍቃሪ መሆን አይገባኝምና እባክህን እንደገና ልይህ ። የማየውን አንተን በማየት ካልሻርሁት ፣ የምሰማውን ባንተ ድምፅ ድል ካልነሣሁት እሰጥማለሁና እባክህ እርዳኝ ። ትልቁ ማስተዋል አንተን ማየት ነው ። የቅርብ ረዳትም የቅርብ ጠላት ፣ የቅርብ ልጅም የቅርብ ሕመም ሊሆን ይችላል ። አንተን ማየት ግን ሁሉን ያስረሳል ። እንኳን አንተን የወዳጅን ፊት ሲያዩት ያበረታል ፣ ለልብም መጽናናት ይሆናል ። አምስት ሺህ ሰው በቁራሽ እንጀራ እንዳጠገብህ ዘንግቼ ገና እፈራለሁ ፣ ቀይ ባሕርን እንደከፈልህ ረስቼ ገና በቦይ ውኃ እደነግጣለሁ ። እባክህን አንተን ልይህና እንዳልደከመ ሁኜ ልበርታ ። አንተን ማየት ትርፍ አለው ። አንተን ካላየሁ የመሰከርኩትን ልክደው ፣ የወደድኩትን ልጠላው ፣ የጨበጥኩትን ልወረውረው ዝግጁ ነኝ ። አንተን ካላየሁ የማልሆነው ነገር የለም ። ወደ ኋላ እንዳልል ፣ ቀምሼህ እግዚአብሔር ማነው ብዬ እንዳልናገር ፣ ለምጄህ አዲስ እንዳልሆን እባክህን ማስተዋልን ስጠኝ ። ከሰው እንዳልለይ ብዬ አንተን እንዳልጥል ፣ ለእንጀራ ብዬ ሰማይን እንዳልሰርዝ ፣ ለዝና ብዬ ክብርህን እንዳልከስር ፣ በምድር ትልቅ ሁኜ በሰማይ እንዳላንስ እባክህ ማስተዋል ስጠኝ ።
ቃልህ ከመነበብ በላይ ሲኖሩት ፍቺው ያበራል ። የመኖር ማስተዋልን ስጠኝ ። በፊትህ ወድቆ መጸለይ ብዙ ጭንቀትን ይጥላል ። የመጸለይ ብልሃትን አድለኝ ። ከአባቶች ጋር መመካከር ፈተናን ያበርዳል ። እረኞቼን የማክበር ጥበብ አድለኝ ። በእውነት ቃል የምትገሥጽ ፣ በጥበብ መንገድ የምታሳይ ያንተ ማስተዋል ከእኔ ጋር ትሁን ። ለአበባ ገለባ ለጥላቻ ፍሬ የለውምና እባክህን ማስተዋል ስጠኝ ። በማስተዋል የምኖረውን በጉልበት ልኑር እንዳልል በማስተዋል ባርከኝ ። የትላንቱ እንቅፋት መልሶ እንዳይመታኝ ፣ በወደቅሁበት እንደ ዛፍ እንዳልቀር እባክህን ማስተዋል ስጠኝ ። እያየሁ እንዳላየ እንዳልኖር አዚሜን አንሣልኝ ። በማይፈጸም ምስጋና ተመስገን፤ ለዘላለሙ አሜን ።