የትምህርቱ ርዕስ | ወደዚህ መቼ መጣህ ?

“በነገው በባሕር ማዶ ቆመው የነበሩ ሕዝቡ ከአንዲት ጀልባ በቀር በዚያ ሌላ ጀልባ እንዳልነበረች ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ አዩ ፤ ዳሩ ግን ሌሎች ጀልባዎች ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አጠገብ ከጥብርያዶስ መጡ ። ሕዝቡም ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ ፥ ራሳቸው በጀልባዎቹ ገብተው ኢየሱስን እየፈለጉ ወደ ቅፍርናሆም መጡ ። በባሕር ማዶም ሲያገኙት፡- መምህር ሆይ ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ ? አሉት ።” ዮሐ. 6 ፡ 22-25 ።
እኛ ውርደትን እንሸሻለን ፣ ጌታ ግን ክብርን ሸሽቶ ተሰወረ ። እርሱ ዘላለማዊ ንጉሥ ነውና ጊዜያዊ ንግሥናን ትቶ ፈቀቅ አለ ። እርሱ የአጽናፈ ዓለሙ ጌታ ነውና የአጥቢያ ገዥነትን እንቢ አለ ። የዓለም ንግሥና ቀጥሎ ሌባ የሚያሰኝ ነው ፤ የአጥቢያ ገዥነትም በእስር ቤት የሚጠናቀቅ ነው ። ጌታ ንግሥና እንዳለው አላወቁምና ሊያነግሡት መጡ ። ሊያነግሠን እንደመጣ ባለማወቅ ሊያነግሡት መጡ ። በሰማይ የነገሠ በምድር መንገሥ እንደማያስፈልገው አላወቁምና ሊያነግሡት መጡ ። ጌታ የስሜት አንጋሾችን ሲሸሽ የእውነት ሰቃዮችን ግን ተጋፈጠ ። ስሜትና የአረፋ ኳስ ሁለቱም አንድ ናቸው ፣ ሲጨብጧቸው ባዶ ናቸው ። የከበረን ቢያከብሩት አይከብርም ያከብራል እንጂ ። የነገሠን ላንግሥህ ቢሉት አይነግሥም ፣ ያነግሣል እንጂ። ከስሜት አንጋሾች መሸሽ ፣ ክበው ከሚንዱ መጠንቀቅ ፣ ከእውነት ይልቅ ለግለታቸው ዋጋ ከሚሰጡ መራቅ ተገቢ ነው ። ስሜታውያን የተጋጋሉበትን ነገር ሲተዉት እንኳ አይጨነቁም ። ስሜታውያን መቼ እንደሚጀምሩና እንደሚያቆሙ አይታወቁም ።
 
“በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ” ይላል ። አውቆ” የሚለው ቃል ሊሰመርበት ይገባል ። ጌታ የሚያደርገውን ሁሉ አውቆ ነው ። የሚወደንም አውቆን ነው ። ሰውን ስናውቀው የምንጠላው ከሆነ የፍቅራችን መሠረት አለማወቅ ነው ። እርሱ ግን አውቆን ሊያግዘን ይወደናል ። ዛሬም ተአምር አድራጊዎችን ካላነገሥን የሚባለው ለዚህ ነው ። ተአምር ፈላጊ ስሜታዊ ስለሆነ ። ብዙ ሰው የሚጠነቀቀው የሚቃወሙትን ነው ። በስሜት የሚያጅቡትን ግን ይወዳል ። ይህን ዓለም የምንሻገረው በጥንቃቄ ነው ። እጅግ ጥንቃቄም አለማመንን እንዳይወልድ በወጉ መጠንቀቅ ይገባል ። ጥንቃቄአችንንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። ጌታ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ ።የስሜት ጎርፍ አጠገብ ያሉትንም ይነካልና ሐዋርያቱ ለምን አትቀበልም እንዳይሉ ብቻውን ፈቀቅ አለ ። ተአምር ፈላጊዎች እናንግሥ ቢሉም የዘላለሙን ነገር መስማት ይሰለቻቸዋል ። የማይታየውን እግዚአብሔር የሚቀበሉት ለሚታየው ዓለም ያስፈልገናል ብለው ነው ። እነዚህ ሰዎች በአንድ አዳር ተለውጠው ንግግሩ የሚያስጨንቅ ነው ብለዋል ። ዛሬም ሰዎች በደረጃ ስለማይወጡ በደረጃ እየወረዱ አይደለም ። በምኞት ማንገሥና በሐቅ ማዋረድን ተክነውበታል ። እንኳን በቅጡ የሚያመሰግን በቅጡ የሚሳደብም እየጠፋ ነው ።  ሰውን ሲወዱ መልአክ ነው ማለት ፣ ሲጠሉ ሰይጣን ነው ከማለት ሰው ነው ማለት በቂ ነበር ።
ደቀ መዛሙርቱ የብቻቸውን መንገድ ጀምረው በባሕሩ ላይ በነፋስ ይማስኑ ነበር ። ባሕር ወራጅ አለ የማይባልበት ጎዳና ነው ። የባሕር መውረጃው ወደቡ ነው ። ጌታ ወደ እነርሱ አልመጣም ነበርና አሁንም ጨልሞ ነበር ይላል ። ኢየሱስ ክርስቶስ ካልመጣ የጨለማው ዕድሜ ይረዝማል ። ጌታችን ወንጌል ካልተሰበከባቸው አገሮች በተሰበከባቸው አገሮች ይገረማል ። ተሰብከው እንዲህ ከጨከኑ ባይሰበኩ ምን ይሆኑ ነበር ብሎ ያዝናል ። ባሕር ላይ መናወጥ ተጨምሮ ከባድ ነው ። “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንዲሉ ። ኢየሱስ እስቲመጣ አንደኛ ጨለማ ሁለተኛ መናወጥ ሦስተኛ መድኃኒቱን ራሱን መፍራት ይቀጥላል ። ኢየሱስ ክርስቶስ በመፍትሔነቱ እንኳን ተፈርቷል ።
ጌታ ከአንጋሾች ግርግር ራቀ ። ብዙዎቻችን መከራችን ለዓመታት የረዘመው በአንጋሾች ይሉኝታ ተይዘን ነው ። ዓለም እውነተኛ አዋራጆች ሐሰተኛ አክባሪዎች አሏት ። ሐዋርያት በባሕሩ ላይ ወደኋላ ለመመለስም ሩቅ ሆነባቸው ፣ ወደፊት ለመሄድም ማዕበሉ ደረቱን ሰጣቸው ። ለዚህ መፍትሔው ክርስቶስ ነው ። ደቀ መዛሙርቱ ከማዕበሉ ጋር ብዙ አሳብ በውስጣቸው ሳይመጣ አይቀርም ። እነርሱም በልባቸው ክርስቶስን የማንገሥ አሳብ ነበራቸው ። ባልተጨበጠ የሹመት ስፍራ ሲከራከሩ ኑረዋል ። የአሳብ ወንበርም ያጣላቸውና ትዕቢተኛ ያደርጋቸው ነበር ። ጌታ በባሕር ላይ እየተራመደ ሲመጣ ግን የተመኙት የሚያንሰውን እንደሆነ ሳይረዱ አልቀረም። እነርሱ በታንኳ ያቃታቸውን እርሱ በእግሩ እየረገጠ መጣ ። ባሕር በእግር አይረገጥም ። የባሕር ጫማ መርከብ ነው ። ጌታ ግን በእግሩ ይረግጠዋል ።
ሰው ጨለማን ማዕበልን በፈራበት መጠን እየመጣ ያለውን ጌታ ከፈራ ጤነኝነት አይደለም ። ደቀ መዛሙርቱ ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ ነበሩ ። ቀኑ ትልቅ ተአምር የነበረበት ቢሆንም ምሽቱ ግን ብርቱ ማዕበል የሚያገሣበት ሆነ ። ታላላቅ በረከቶች ታላላቅ ሁከቶች አለባቸው ። ከታላቅ ምስጋና ፣ ከታላቅ ምስክርነት በኋላ ታላላቅ ሞገዶች እንደሚነሡ ማወቅ ያስፈልጋል ። ደቀ መዛሙርቱ በባሕር ላይ ሲጨነቁ ፣ አንዳቸው አንዳቸውን መርዳት በማይችሉበት ሁኔታ ፣ ወደ ወደቡ ቀርበው ሳለ ነገር ግን መጨረሻው ላይ ትንቅንቅ ሲገጥማቸው ፣ ደርሰው ሳለ እንዳልደረሱ ሲያደናግራቸው ጌታ ደረሰ። “እባብ ያየ በልጥ ይደነብራል” እንዲሉ ጌታ መሆኑን ስላላወቁ ተጨነቁ ። ጌታም “እኔ ነኝ” በሚለው ድምፁ አረጋጋቸው ። “እኔ ነኝ” ያህዌ ነኝ ማለት እንጂ ተራ ድምፅ አይደለም ። ያህዌ የማይለወጠው የእግዚአብሔር መገለጫ ነው ። ማዕበሉን እንደፈራችሁት እኔንም አትፍሩ ፣ ፀጥታችሁ ነኝ ማለቱ ነው ። በሚናወጠው ታንኳ ላይ ማንንም አይጋብዙም ። ጌታን ግን ጋበዙት ። በሚናወጠው ነገር ላይ እርሱን መጋበዝ መፍትሔ አለው ። መናወጡን ረስተው ግባ አሉት ። እርሱን መጋበዝ እየተናወጠ ሳለ ነው ፣ ፀጥ አድራጊው እርሱ ነውና ። ነገር ግን ወዲያው ወደ ወደቡ ደረሱ ። ታላላቅ ፈተናዎች ከመጡ ደርሰናል ማለት ነው ። መድረሻውን እንዳናይ የሚያደናግሩ የጠላት ስልቶች ናቸው ። “አይጥ ወልዳ ፣ ወልዳ ጅራቱ ሲቀራት ታንቃ ሞተች” እንዲሉ መጨረሻው ላይ እጅ እንዳንሰጥ መጠንቀቅ ይገባናል ። ማዕበሉ መድረሳቸውን አላሳይ ብሎአቸው ነበርና ጌታ ብርሃን ሆነላቸው ። ማዕበሎች የተጠናቀቀውን ጉዞ እንዳናይ ያደርጉናል ። ከምንኖርባቸው ጊዜዎች የኖርንባቸው ዘመኖች ይበዛሉ ።
“በነገው በባሕር ማዶ ቆመው የነበሩ ሕዝቡ ከአንዲት ጀልባ በቀር በዚያ ሌላ ጀልባ እንዳልነበረች ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ አዩ ፤ ዳሩ ግን ሌሎች ጀልባዎች ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አጠገብ ከጥብርያዶስ መጡ ።” ጌታን የማንገሥና የእንጀራ ጥያቄአቸውን ለዘለቄታው የመመለስ አሳብ የነበራቸው ወገኖች ሌላ ተአምር እንደ ተከናወነ ማወቅ ችለዋል ። ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን እንደሄዱ ጌታም በባሕሩ ላይ በእግሩ እንደ ተራመደ አስተውለዋል ። በሙሴ ዘመን በቀይ ባሕር ላይ ከተፈጸመው ተአምር የበለጠ ተአምር ነው ። ባሕሩ ዳርቻ ላይ የተአምራት ምልክት ታይቷል ። የእግዚአብሔር ሥራ የተከናወነባቸው ቦታዎች አሻራቸው ለዘመናት አይፋቅም ። ዛሬም እዚህ ዳርቻ ላይ ብዙ ጎብኚዎች ተገኝተው እግዚአብሔር ኑሮአቸውን እንዲባርክ ይማጸናሉ ። ደቀ መዛሙርቱ በነበረችው አንዲት መርከብ ጌታን ጥለው ለምን እንደተጓዙ አናውቅም ። ምናልባት በተራራው ላይ እንደ ልማዱ ከአባቱ ጋር እየተነጋገረ ያነጋል ብለው ሊሆን ይችላል ። አንጋሾቹ ግን አንዲት ታንኳ እንደ ነበረችና ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ተሳፍረው እንደሄዱ አስተውለዋል ። ጌታ ወደ ተራራው ፈቅ ስላለ እነዚህ አንጋሾች ደቀ መዛሙርቱ ጋ ሁነው እየጠበቁትና ነጥቀው ሊወስዱት እየከጀሉ ነበር ። ደቀ መዛሙርቱ የሄዱበት ሁለተኛው ምክንያት የእነዚህን ሰዎች ስሜት መሸከም ስላቃታቸውም ሊሆን ይችላል ። ሌሎች ጀልባዎች ግን ኢየሱስ እንጀራን ወደባረከበት ስፍራ ከጥብርያዶስ መጉረፍ ጀመሩ ። ዝናው ፈጥኖ ወጥቶ ነበር ። የተቀቡትን ሽቶ ሌላ ሰው እንዳይሸተው መከልከል እንደማይቻል የጌታ ሥራም እንደ ሽቶ ያውዳል ።
“ሕዝቡም ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ ፥ ራሳቸው በጀልባዎቹ ገብተው ኢየሱስን እየፈለጉ ወደ ቅፍርናሆም መጡ ። በባሕር ማዶም ሲያገኙት፡- መምህር ሆይ ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ ? አሉት።” ዮሐ. 6 ፡ 24  ።
እነዚህ ሰዎች ፍቅርን ሳይሆን መብልን መሠረት አድርገው እየፈለጉት ነበር ። ክርስቶስ ለእነርሱ የምግብ እንጂ የሕይወት ዋስትና አልነበረም ። ነገሥታት በቀን ሦስት ጊዜ ሕዝብን ለመመገብ ቃል ይገባሉ ። በበረከት የሚመግበው እርሱ ቢያነግሡት መልካም ነው ብለው ይፈልጉታል ። እርሱ ግን ስለ ፍቅሩ ስለ ምሕረቱ የሚመለክ አምላክ ነው ። እነዚህ ሰዎች ፍለጋቸው ተራ አልነበረም ። በየብስ በባሕር ነው ። ምክንያታቸው ግን ትንሽ ነው ። በተቃራኒው ደግሞ ትልቅ ምክንያት ትንሽ ድካምም አለ ። የድካሙ ብዛት ምክንያቱን ትልቅ አያደርገውም ። ብዙ ሰዎች ከድካሙ የተነሣ ምክንያቱ ከፍ ይበልልን ይላሉ ። እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል ።
ጌታን ሲያገኙት መምህር ሆይ ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ ? አሉት።” ያጠገባቸውን ኃይልና ፍቅር አላዩም ፣ የሚያዩት መጥገባቸውን ብቻ ነው ። ለመብላት የሚኖሩና ለመኖር የሚበሉ ሰዎች አሉ ። እነዚህ በሁለት የተራራቀ ጽንፍ ላይ የተቀመጡ ናቸው ። ለመብላት የሚኖር ማንም ያብላው ላበላው ይኖራል ። ሆዳምነት ኃጢአትና የኃጢአት ሥር ነው ፣ ከዚህም የምንድነው በመጠን ኑሩ በሚለው ትእዛዝ ነው ።
“ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም”  አላቸው ። ዮሐ. 6 ፡ 26 ። ጌታችን እውነቱን ነገራቸው ። በዚህ ምዕራፍ ላይ ሁለት ጊዜ ቊርጥ ንግግር ሲያደርግ እናነባለን ። የመጀመሪያው ለአንጋሾች የተናገረው ሲሆን ሁለተኛው ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው ነው ። ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ፡- እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ።”/ቁ. 67/ ። ጌታችን እውነቱን እየተናገረ እንጂ እያባበለ ማንንም ገንዘቡ አያደርግም ። እውነትን እርሱ ሲናገር ዓላማው ሰዎቹን መለወጥ ብቻ ነው ። ደግሞም የሚለውጥ ኃይሉንም አዘጋጅቶ ነው ። ጥዋት ተበልቶ ቀትር ላይ የሚጠፋው ምግብን አይተው ተከተሉ እንጂ የዚህ ተአምር ምልክትነት ምንድነው ? እግዚአብሔር በመካከላችን ምን እያከናወነ ነው አላሉም ። የሚያልፉ ተአምራቶች ምልክትነታቸው ለማያልፈው ሕይወት ነው ። በጌታችን ንግግሮች ውስጥ ሦስት ሰዎችን እናያለን ፡-
1-  ስለጠገቡ ብቻ የሚከተሉ ፣ እነዚህ ሰዎች ከእንጀራ አልፈው ማየት አይችሉም ።
2-  ምልክት ፈልገው የሚከተሉ ፣ እነዚህ ሰዎች ከእንጀራ አልፈው ተአምር እንደ ተከናወነ ያያሉ ፤ ተአምራትን ለሥጋ ስኬት አሁንም ይፈልጋሉ ።
3-  ምልክቱን ትተው ዋናው ዓላማ ላይ የደረሱ ሰዎች አሉ ። እነዚህ በነፍስም በሥጋም እግዚአብሔርን የተጠጉ ናቸው ።
በመቀጠል ጌታችን ፡- “ለሚጠፋ መብል አትሥሩ ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና ” አላቸው ። ዮሐ. 6 ፡ 27 ።
ጌታችን በተአምራት የበረከተውንም ምግብ የሚጠፋ መብል ነው አለ ። ማቃለሉ አይደለም ፣ የማይጠፋ መብል እንዳለ ሊገልጥ ነው ። ጌታችን ጥልቅ እውነቶችን እንደ ዋዛ ተናግሯል ። ፍለጋቸው ይህ ሁሉ ድካማቸው እንጀራን ለማግኘት ብቻ እንዳይሆን እያስጠነቀቃቸው ነው ። የዘላለም ሕይወት ከዚህ በፊት ባሉት ምዕራፎች በውኃ ሲመሰል አሁን ደግሞ በመብል ተመስሏል ። መብል በሕይወት ለመቆየት የማይግደረደሩበት ፍላጎት ነው። የዘላለም ሕይወትም የማይጠፋ ህልውናን መልበስ ነው ። መብል ሌላ ተግባርን ለመፈጸም አቅም ነው ። የዘላለም ሕይወትም በጎ ለመሥራት ብርታትን የሚሰጥ ነው ። መብል ደካማውን ሰው የሚያጸና ነው ። የዘላለም ሕይወትም ፈታኙን ዓለም የሚያስረሳ ነው ። መብል የማያቋርጥ ፍላጎት ነው። የዘላለም ሕይወትም ያለ ማቋረጥ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ነው ። መብል አብረው ሲበሉት ቃል ኪዳን ነው ፣ ደግሞም ያፋቅራል ። የዘላለም ሕይወትም የዳነች አንዲት ቤተ ክርስቲያንን ይመሠርታል ። መብል የትግል ውጤት ነው ፣ መዘራት ፣ መታጨድ ፣ መወቃት ፣ መለቀም ፣ መፈጨት ፣ መጋገር አለበት ። የዘላለም ሕይወትም የክርስቶስ የሞቱ ፍሬ ነው ። መብል ራሱን ሠውቶ ሌላውን ያኖራል ፣ ጌታም ስለ እኛ በመሞት ሕይወቱን ሰጥቶናል ። እንጀራ ቅርጹ ክብ ነው ፣ የዘላለም ሕይወትም ለሁሉ ነው ። እንጀራ ዓይኑ ብዙ ነው ፣ የዘላለም ሕይወትም ጸጋው ብዙ ነው ።
የዘላለም ሕይወት ስጦታ ሲሆን ሰጪውም ክርስቶስ ነው ። የዘላለም ሕይወትን በተመለከተ “በሥራ አይዳንም ፣ ያለ ሥራ አይዳንም” የሚል አጭር መግለጫ ብንሰጠው መልካም ነው ። እግዚአብሔር አብ ያተመው የዘላለም ሕይወትን ነው ፣ ሁሉም ሰው በእንጀራ አይደላውም ፤ የዘላለም ሕይወት ግን ለወደደ ሁሉ ነው ። የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም መምጣቱን ማመን ግዴታ ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም