“በተናደድህበት እያንዳንዷ ደቂቃ ስድሳ ሰከንድ የደስታ ጊዜ ታባክናለህ ።”
መናደድ መበሳጨት ፣ መንደድ ፣ መቃጠል ፣ ራስን መጉዳት ፣ ሰዎችን ማሳቀቅ ፣ ለበሽታና ለጭንቀት ሰውነትን አሳልፎ መስጠት ነው ። መናደድ ስላለፈው ፣ ስለ አሁኑና ስለሚመጣው ሊሆን ይችላል ። ስላለፈው የሚናደዱ ሰዎች በራሳቸው ስህተትና በሰዎች ክፋት ልባቸው የሚያዝንባቸው ሊሆኑ ይችላሉ ። እንዲህ ባይሆን ኖሮ እንዲህ አይሆንም ነበር የሚል ስሜት መናደድን ያስከትላል ። ይህ ስሜት ለአንድ ጊዜ ሊሰማን ይችላል ። እየመረዘን እንዲኖር ግን መፍቀድ አይገባንም ። የሆነን ነገር መለወጥ አይቻልም ። ከተማርንበት ግን የትላንቱ ለነገ ስንቅ ይሆነናል ። ያለፈው ጊዜ ላይ መማር እንጂ ማቀድ አይቻልም ። እንደ ሞኝም ምነው እግሬን በሰበረው ፣ ምነው አፌን ዱዳ ባደረገው ማለት የንስሐን ጥቅም አለመረዳት ነው ። ቆሻሻ ባይኖር ኖሮ ውኃ ለንጽሕና አያስፈልግም ነበር ። በራሳችን ስህተትና በሰዎች ግድፈት ላይ መዘግየት አይገባንም ። የተሰጠን ዕድሜ የተሰፈረ ነውና ሥራን በቁጭት ተክተን ማሳለፍ አያስፈልገንም ። የትላንት ጥሩ ጊዜ በትዝታነቱ ፣ ክፉ ገጠመኙ ደግሞ በትምህርትነቱ ይኖራል ። የሰው ልጅ የማይረሳ ትምህርት የሚያገኘው ከደስታው ይልቅ በጉዳቱ ነው ።
ሰዎች በዛሬው የሚናደዱት ምንም ተግዳሮት በመንገዳቸው ላይ እንዲቆም ባለመፈለጋቸው ነው ። ቀኑ የራሱ ክፋት ወይም ትግል አለው ። አንድ ቀን የምንለው ግማሽ ጨለማ ፣ ግማሽ ብርሃን ነው ። ሕይወትም በየቀኑ ደስታና ኀዘንን የምታስተናግድ ናት ። በየቀኑ ሊመጡ የሚችሉትን እንቅፋቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት “የዛሬው ትግል ይህ ነው ማለት ነው” ብሎ መረጋጋት ይገባል ። የዛሬውን የምናልፈው የትላንቱን እንዳለፍነው ነው ። ችግር ጊዜያዊ ነው ። በመበሳጨት ግን ዘላቂ እናደርገዋለን ። በመንቀሳቀስ እንጂ በመናደድ የሚወገድ ተራራ የለም ። የመጣው የዛሬ ፈተና ይለወጣል ፣ ችግሩ ካልተለወጠ ደግሞ እኛን ይለውጠናል ። በእያንዳንዱ ገጠመኝ እውቀታችን እየጨመረ ይመጣል ። ለዕለቱ ተግዳሮትም በብስጭት አለመወሰን ፣ ለደስታውም በስሜት ቃል አለማግባት ይገባል ። ሲያድር ሁሉም ነገር ይለወጣል ። የደፈረሰውም ውኃ የሚጠራው በጊዜ ውስጥ ነው ። ሰከንድም ጊዜ ነውና እያንዳንዱ ደቂቃ ትዕግሥትን ይጠይቃል ። ሥራችንን በጸሎት መጀመር ፣ “እግዚአብሔር ሆይ ሁሉን ባንተ አግኝቻለሁ” ብሎ የምስጋና ልብ መያዝ ፣ ደኅና ብሎ በሞተው ነገር ላይ ሕይወትን ማወጅ ይገባል ።
ስለ ነገ መናደድ የሚከሰተው እውቀታችን ያድግና አሻግሮ ያያል ፣ የሚመጣውን ችግር በመገንዘብም ያስባል ፣ ያሳስባል ። ለማንቃትም ደወል ሲደውል አገርና ትውልድ ይተኛል ። በዚህ ጊዜ አዋቂው መናደድ ይጀምራል ። መክረን ምክራችን ተቀባይነት ሲያጣ መገንዘብ ያለብን ነገር አለ ። የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ ያለው ፍጡር ነውና ማስገደድ አንችልም ። ዳግመኛም ሁሉም ሰው የሚጓዘው የምርጫውን ውጤት ለመቀበል ነው ። የታየን ሁሉ ለሰዎች ላይታያቸው ይችላል ። ከማዘንና ከመናደድ “ያሳየኸኝን ግለጥላቸው” ብሎ መጸለይ ይገባል ። ማወቅ ያለ እግዚአብሔር እርዳታ ኀዘንን ይወልዳል ። አላዋቂው የገዛ ሞቱ ላይ ተኝቶ ያንኮራፋል ። አዋቂው ግን ያዝናል ። ኖኅ መርከብ የሠራው መዓት የመጣ ቀን አይደለም ። መዓቱ ከመምጣቱ ከብዙ ዓመታት በፊት ነው ። ቢተባበሩት ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ይድኑ ነበር ። እያፌዙበት ይሄዱ የነበሩት ሲጠፉ ኖኅ ግን ዳነ ። አዋቂና መንፈሳዊ ሰውም ይመክራል ፣ አልሰማ ካሉት እንደ ሎጥ ራሱን ያድናል ። ሎጥ ሚስቱንም ልጆቹንም አላተረፈም ። እውቀት በመማር እንጂ አብሮ በመኖር የሚጋባ ነገር አይደለም ። መንፈሳዊነትም ምርጫ እንጂ አብሮ የመኖር ውጤት አይደለም ። መጽሐፍ፡- “በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል ፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች” ይላል ። ማቴ. 24፡40-41።
እግዚአብሔር እያንዳንዱን ደቂቃ የደስታ ምክንያት አድርጎ ሰጥቶናል ። በእግዚአብሔር ሀልወት ፣ በተቀደሰው ጠባያቱ ፣ እኛን ባዳነበት ምሕረቱ ፣ በማያቋርጠው መግቦቱ ፣ በቀኑ በምሽቱ ፣ በማብላት በማጠጣቱ ፣ በልደት እያመጣ በሞት በመውሰድ ታሪክን በማስቀጠሉ ደስታችን ብዙ ነው ። መኖራችንን በማይፈልጉ ጠላቶች መካከል በሕይወት በመኖራችን ፣ ከሚያጠቁን አጋንንት የሚራዱን መላእክት ብዙ ስለሆኑ መደሰት ይገባናል ። ቆጥረን እንዳማረርን ቆጥረን ብናመሰግን ምሬት ይጠፋልን ነበር ፣ ያለን ከጎደለን የብዙ ብዙ ነውና ። ከትላንት የተሻለ ዛሬ ብለን የምንጠራው መክሊት በእጃችን አለ ፣ ከሄደው የመጣው መልካም ነገር ብዙ ነው ።
ቢሆንም ስንናደድ አእምሮአችንን እናጣለን ። ስሜታችንን እናዳምጣለን ። የዓመቱን በዕለት እናፈርሰዋለን ። ጤናችንን እናቃውሳለን ። አመላችንን እናስገምታለን ። አልምጦችን ደስ እናሰኛለን ። መንፈሰ እግዚአብሔር እንዲርቀን እናደርጋለን ። በጸሎት ሳይሆን በጉልበት ለመፍታት እንነሣለን ። ከሁሉ በላይ ኀዘን ፊታችንንና ልባችንን ያጨልመዋል ። ንዴት አቃጥሎ ይጨርሰናል ። ብስጭት በጎዳና በቤት እንደ ዕብድ እንድንታይ ያደርገናል ። ጭንቀት ወጥሮ ይይዘናል ። አጥፍቶ መጥፋት ያምረናል ። በተበሳጨንበት ሰዓት ቦታ እንለውጥ ፣ ውኃ አብዝተን እንጠጣ ፣ ሊያበርዱን የሚችሉ ሰዎችን እንፈልግ ፣ የዜማ መሣሪያ መጫወት የምንችል ከሆነ በገና መደርደር እንጀምር ። ንዴታችን ለመንፈሰ እግዚአብሔር ቦታ እየለቀቀ ይመጣል ። ጭስ የማይታይበት ቃጠሎ ንዴት ነው ። አዎ “በተናደድህበት እያንዳንዷ ደቂቃ ስድሳ ሰከንድ የደስታ ጊዜ ታባክናለህ ።”
በደስታ ዋሉ ።
የብርሃን ጠብታ 26
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም.