የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሁለቱንም አዳናቸው

“ነገር ግን ሰው እንደሚገባ ቢሰራበት ሕግ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን፤” 1ጢሞ. 1፡8
ሕገ ልቡና ፣ ሕገ ኦሪት ፣ ሕገ ሐዲስ በመባል ሕግ በሦስት ይከፈላል ። ሕገ ልቡና የተፈጥሮ ሕግ ፣ ሕገ ኦሪት የጽሑፍ ሕግ ፣ ሕገ ሐዲስ የመንፈስ ሕግ ነው ። ሕገ ልቡና ለሰው ዘር ሁሉ ፣ ሕገ ኦሪት ለእስራኤል ልጆች ፣ ሕገ ሐዲስ በክርስቶስ ለሚያምኑ ተሰጥተዋል ። ሕገ ልቡና በኅሊና ሰሌዳ ላይ ተጽፎ በተፈጥሮ አማካይነት ተሰጥቷል ። ሕገ ኦሪት በድንጋይ ጽላት ተጽፎ በደብረ ሲና ተሰጥቷል ። ሕገ ሐዲስ በቀራንዮ ተሰጥቷል ። አንዳንድ ሰዎች ኦሪቱንም ሐዲሱንም አልሰሙም እንዴት ይጠየቃሉ ? ብለን እናስብ ይሆናል ። በተሰጣቸው የኅሊና ሕግ ይጠየቃሉ ። የኅሊና ሕግ ሙሉ በመሆኑ የሕገ ኦሪትን ያህል ያስጠይቃል ። እግዚአብሔር ሕጉን የጻፈባቸውን ነገሮች ስንመለከት ቅድስና ምርጫ አለመሆኑን እንረዳለን ። ሕገ ልቡናን ያለ ቀለምና ያለ ሰሌዳ በኅሊና ላይ ጻፈ ። ይህን ሊያደርግ የሚችልም እርሱ ብቻ ነው ። ሕገ ልቡና የእግዚአብሔርን ሀልዎትና የሰውን ክብረት ያስረዳል ። ሰው ከደመ ነፍስ እንስሳት የሚለየው በውስጡ ባለው ረቂቅ ሕግና የዘላለም ሕይወት ነው ። አዳም የተኰነነው በሕገ ኦሪት አይደለም ። በሕገ ልቡናና በገነት ውስጥ በተሰጠው “አትብላ” በምትለው አንዲቷ ትእዛዝ ነው ። ሕገ ኦሪትም የተሰጠው በድንጋይ ጽላት ላይ ተጽፎ ነው ። በድንጋይ ላይ የሚጻፉ ጽሑፎች ለሺህ ዓመታት ይነበባሉ ። እግዚአብሔርም እንዳይረሳ የሚፈልገውን ትእዛዝ በድንጋይ ጽላት ላይ ጽፎ ሰጠ ። ሕገ ሐዲስንም በደሙ ቀለም ፣ በመንፈስ ቅዱስ አስታዋሽነት ለቤተ ክርስቲያን ሰጠ ። የሕገ ልቡና ተቀባይ ነፍስ ነበረች ። የሕገ ኦሪት ተቀባይ ቤተ እስራኤል ስትሆን የሕገ ሐዲስ ተቀባይ ግን ቤተ ክርስቲያን ናት ።

ሕጉ ለሰው ክብረት ሰጥቷል ። የሰው ልጅ ከጥፋት የሚመልሰውና መሳሳቱን የሚነግረው ሕግ ስላለው ከእንስሳት ይለያል ። ሰውን ሕግና እቅድ ከእንስሳት ልዩ ያደርጉታል ። እንስሳት የነገ ተስፋና እቅድ የላቸውምና ። ሕገ ልቡና የሰው ክብር ነው ። ኢማኑኤል ካንት የተባለ ሰው ሁለት ነገሮች ይደንቁኛል ብሏል ። የመጀመሪያው በኅሊና ላይ የተቀመጠው ሕግ ሲሆን ሁለተኛው በሰማይ ሰሌዳ ላይ የማያቸው ከዋክብት ናቸው ብሏል ። ሕገ ልቡና ፈላስፎች እንኳ የተደነቁበት ነው ። በዓለም ላይ ለሚገኙት ሕግጋት መሠረቱም ይህ የኅሊና ሕግ ነው ። ማንም ሰው ቢማርም ባይማርም ክፉ ፣ ክፉ ደግም ደግ መሆኑን ያውቃል ። ይህ እውቀት የመጣው በሕገ ልቡና ነው ። ሕገ ልቡና ትልቅ ስጦታ ነው ። በሕገ ልቡና ተመርተው እግዚአብሔርን የተከተሉ እነ ሄኖክ ፣ ኖኅና አብርሃምን ማስታወስ አለብን ። ታላላቅ አባቶች የነበሩት በሕገ ልቡና ነው ። ሕገ ልቡና በቂ ሕግ ስለሆነ ነው እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን በጥፋት ውኃ ፣ በሎጥ ዘመን በእሳት የቀጣው ። ሕግ ባይኖር ኑሮ ሰብአ ትካትና ሰብአ ሰዶም ባልተቀጡ ነበር ። ሕገ ልቡና ለቅጣት በቂ ሕግ ነው ።
የእስራኤል ሕዝብ በዙሪያቸው ከነበሩት አሕዛብ ቢያንስ በሁለት ነገር ልዩ ናቸው ። በግዝረትና በሕገ ኦሪት ። ግዝረት የቃል ኪዳን ማኅተም ሲሆን ሕጉ ደግሞ መሪ ነው ። ታላቁ እስክንድርን ሳይቀር ያስደነቀው የሞራል ሕጋቸው ፣ የአምልኮ ሥርዓታቸው ፣ ሁሉም ነገራቸው መጽሐፋዊ መሆኑ ነው ። እስራኤል ጥንታዊ ሥልጣኔና ሕገ መንግሥት ያላት አገር የሚያሰኛት ሕጉ ነው ። ሕጉ ለእስራኤል ክብር ነው ።
ሕገ ሐዲስም ፍቅር ሲሆን ይህም ሕግ የተሰጠን እግዚአብሔር ስለ ሰው ልጆች ቤዛ ሁኖ ነው ። በዓለም ላይ ለንጉሣቸው የሚሞቱ ሠራዊት አሉ ። ለሠራዊቱ የሞተው ግን መድኃኔ ዓለም ነው ። ሕገ ሐዲስ በፍቅር ተጀምሯልና በፍቅር ይፈጸማል ።
ሐዋርያው ጳውሎስ የሕግ አስተማሪዎች ለመሆን የሚፈልጉትን ወደ ወገኝነትና ወደ ፈራጅነት ለመሄድ የሚሹትን ኤፌሶናውያንን ሲመክር ሕጉን ከሕጋውያን በመለየት ነው ። ስስታም ባለጠጎች የሚሰጡ ይመስላሉ ፣ የተቀባቡ ሴቶችም ቆንጆ ይመስላሉ ፣ የሚፎክሩ ወንዶችም ጀግና ይመስላሉ ። ሕጋውያንም ሕግ አክባሪ ይመስላሉ ። እንደ ስስታሙ ቆይ እባክህ እያሉ ኪሳቸውን ይዳብሳሉ ። ነገር ግን ዕዳ አይከፍሉም ። እንደ ቆንጆዋ ሴት ቆንጆ ይመስላሉ ፣ ቤታቸው ሲገቡ ግን ጌጡን ያወልቃሉ ። እንደ ወንድ ጀግና ይመስላሉ ፣ ፈተና ሲመጣ ይሸሻሉ ። ሕጋውያን ሲገድሉ እንጂ ሲሞቱ አይታዩም ። ዘመነ ሰማዕታትም የሐዲስ ኪዳን ዘመን ነው ። ሕጋውያንን ከሕጉ መለየት በጣም ያስፈልጋል ።
ሕጋውያን ሕጉን የሚጠቀሙበት ሌላውን ለመግዛት ነው ። ፖሊስ የሚያከብር ሕጉን ግን የማያከብር ብዙ ሰው አለ ። ሕጋውያንም እነርሱ ከተከበሩ ለሕጉ መፍረስ ደንታ የላቸውም ። ክብራቸው ግን የሕጉ መከበር ነው ። ሕጉን የደፈረ ፖሊሱን ይደፍራል ። ትራፊክ ፖሊሱን የሚያከብር ሕጉን ግን የሚጥስ ሾፌር አለ ። ሕጋውያን የሚያመርቷቸውም አስመሳዮችን ነው ። ሕጉ ግን መልካም ነው ። ከመልካሙ እግዚአብሔር የተገኘ ነውና ።
ሕጉ መልካም ነው ። የሚመራን ወደ ቀና ጎዳና ነውና ። የግብረ ገብነት ደረጃ ብናወጣ፡-
1-  ጨዋ ፣
2-  በጎ አድራጊ ፣
3-  የእግዚአብሔር ልጅ ፣
4-  ክርስቶስን የሚመስል ብለን ማውጣት እንችላለን ።
ሕገ ልቡና ጨዋዎችን ፣ ሕገ ኦሪት በጎ አድራጊዎችን ፣ ሕገ ሐዲስ የእግዚአብሔር ልጆችን ያስገኛል ። የእግዚአብሔር ልጆችም እንደ ክርስቶስ በመኖር መልኩን ያሳያሉ ። “አባቱን የማይመስል ልጅ ዲቃላ ነውና ።” የሕግ አስተማሪ ሊሆኑ የሚወዱ ሕጉ በአብዛኛው “አታድርግ” የሚል ጨዋነት የሚሰብክ ነው ። ከዚያ የላቀ ዓለም ተገኝቷል ። አዲስ ፕላኔት ሲገኝ ወደዚያ የመርማሪዎች ቀልብ እንደሚሳብ ወደ አዲሱ ኪዳን እንዲሳቡ ይመክራል ። ክርስቲያን ማለት ልክ እንደ ክርስቶስ ወይም ክርስቶስ በምድር ማለት ነው ።የሕግ አስተማሪ ሊሆኑ የሚወዱ ከዚያ የተሻለውን የክርስቶስን ፍቅርና ርኅራኄ ለዓለም ሊያንጸባርቁ ይችላሉ ። ክፉን ባለማድረግ ሳይሆን በጎ በማድረግ ከዚያም በላይ ለወዳጅ ራስን አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርሰውን የፍቅርን ዓለም ማየት ይችላሉ ። ዓለም በመንደራችን ልክ አይደለችም ፣ ዓለም ሰፊ ናት ። እንዲሁም መንፈሳዊው ዓለም እጅግ ሰፊ ነው ። እነዚህ ኤፌሶናውያን መጀመሪያ ህልውናቸውን ለተቀበለው ሕገ ሐዲስ እውቅና መስጠት አለባቸው ። ለማያውቃቸው ሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ ከመከጀል ለክርስቶስ ክብር መስጠት ያሻቸዋል ። ሐዲሱ ያለው ኦሪቱም አለው ። ሐዲሱ የሌለው ኦሪቱም የለውምና ይኸው አይሁድ የገዛ መጽሐፋቸው ተጣልቷቸው ይኖራሉ ።
ሐዋርያው፡- “ነገር ግን ሰው እንደሚገባ ቢሠራበት ሕግ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን”ይላል 1ጢሞ. 1፡8 ። የሐዋርያው ቅሬታ ሰው ሕጉን መፈጸም አልቻለም የሚል ነው ። ሕጉ ደግሞ ተደልሎ የሚያሳልፍ አይደለም ፣ የሚጠብቀውን ይጠብቃል ። ሰው ግን ደካማ ሥጋ በመሸከሙ ሕጉን መጠበቅ አልቻለም ። በዚህ ምክንያት ሕጉና ሰው ዓይንና ናጫ ሁነው ሰነበቱ ። ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ሁኖ በመምጣቱ ሁለቱንም አዳናቸው ። ለሰው ልጅ መንፈሱን በመስጠት ሕጉ እንዲፈጸም አደረገ ። በዚህም ሰው ከመሳቀቅ ፣ ሕጉም ካለመከበር ዳኑ ። ሮሜ. 8፡3-4 ። 
ክብር ምስጋና ለአምላካችን ይሁን !
1ጢሞቴዎስ /12/
ኅዳር 17 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።