የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሁለት ዓይነ ሥውራን

                                         
                                          የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ ….. ሰኞ የካቲት 10 / 2006 ዓ/ም
          
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋና የነፍስ መድኃኒት ነው፡፡ ሥጋ በቊስል፣ ነፍስ በኃጢአት ሲታመሙ ገዳዩን ገድሎ የሚያድነው መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የድንግል ልጅ ነው፡፡ የሥጋ ሕመም መነሻው የነፍስ ሕመም ነው፡፡ ሰው ነፍሱ በኃጢአት በታመመች ጊዜ ሥጋው ታማሚና በጭንቅ የሚኖር ሆነ፡፡ ሰው ሥጋው ጤነኛ ሆኖ በነፍሱ ከታመመ እጅግ በሽተኛ ነው፣ ነፍሱ ተፈውሳ ሥጋው ቢታመም ግን ጉዳቱ ጊዜያዊ ነው፡፡ ይልቁንም በዚህ ዓለም ላይ መታመምም ጤነኛ መሆንም ሁለቱም ያልፋሉ፡፡ የነፍስ ፈውስ ግን የማያልፍ ነው፡፡
          በዓለም ላይ ብዙ ሐኪሞችና ብዙ መድኃኒቶች አሉ፡፡ ሐኪሞቹ መድኃኒት ያዝዛሉ እንጂ ራሳቸው መድኃኒት አይሆኑም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሐኪምም መድኃኒትም ነው፡፡ ሦስት ታላላቅ መድኃኒቶችም ከእርሱ ይወጣሉ፡-
1.     ለመንፈሳዊ ውጊያ የስሙ ኃይል፣
2.    ለኃጢአት በሽታ የደሙ ስርየት፣
3.    ለመቀደስ የትንሣኤው ጉልበት ይወጣሉ፡፡ ሦስቱም ያለመቀላቀል ይሠራሉ፡፡ ለኃጢአት በክርስቶስ ስም መገሰጽ አይጠቅምም፣ በንስሐና በደሙ መታጠብ ብቻ ይጠቅማል (1ዮሐ. 1÷7)፡፡
በዓለም ላይ ብዙ ሐኪሞች ብዙ መድኃኒቶች አሉ፡፡ ክርስቶስ ግን አንዱ ሐኪምና አንዱ መድኃኒት ነው፡፡ በዓለም ላይ ብዙ ሐኪሞች ቢኖሩም ነፍስን ማከም፣ ብዙ መድኃኒቶች ቢኖሩም ነፍስን መፈወስ አይችሉም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የነፍስ አለኝታ፣ ከኃጢአት የሚያድን ብቸኛ መድኃኒት ነው (ማቴ 1÷21)፡፡ በዓለም ላይ ያሉ መድኃኒቶች በመርፌ፣ በኪኒን ተወስደው ጊዜያዊ ፈውስ ይሰጣሉ፡፡ በእምነት ተወስዶ ለዘላለም የሚያድን ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ መድኃኒቶች አስቸኳዩን በሽታ ካዳኑ በኋላ ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚነሣ ጠባሳ ጥለው ይሄዳሉ፡፡ ክርስቶስ ግን መድኃኒትነቱ መድኃኒት ብቻ እንጂ ተዘዋዋሪ ጉዳት የለበትም፡፡ በዓለም ላይ ያሉ መድኃኒቶች ሁሉ ይገዛሉ፣ ክርስቶስ ግን የገዛን መድኃኒት ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ መድኃኒቶች ሁሉ ከበሽታ እንጂ ከሞት አያድኑም፡፡ ክርስቶስ ግን ከሞት የሚያድን የሞት መድኃኒት ነው፡፡ ሞት ገዳይ ሆኖ ገዳይ አጥቶ ኖረ፣ ክርስቶስ ግን ለሞት ሞትን ከፈለ፡፡ መድኃኒቶች ሁሉ እየሞተ ያለውን ነገር ይመልሱት፣ ስቃይን ያስታግሡት ይሆናል እንጂ የሞተን አካል መመለስ አይችሉም፡፡ ክርሰቶስ ብቻ የጠፋውን ዓይን የሚያበራ፣ ግንባር በሆነ ዓይን ላይ የዓይን ቅርጽ ሠርቶ የብርሃን ባለቤት የሚያደርግ ነው (ዮሐ. 9÷1-ፍጻሜ)፡፡

ቃሉ፡- “ኢየሱስም ከዚያ ሲያልፍ ሁለት ዕውሮች፡- የዳዊት ልጅ ሆይ÷ ማረን ብለው እየጮኹ ተከተሉት፡፡ ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ÷ ኢየሱስም፡- ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን? አላቸው፡፡ አዎን  ጌታ ሆይ አሉት፡፡ በዚያን ጊዜ፡- እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፡፡ ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ፡፡ ኢየሱስም፡- ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ ብሎ በብርቱ አዘዛቸው፡፡ እነርሱ ግን ወጥተው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ” (ማቴ 9÷27-31)፡፡
ዓይነ ሥውራኑ ባሕርይ
1.     በኅብረት የሚኖሩ ነበሩ፤
2.    አብረው ይጮኹ ነበር፤
3.    ብርሃንን ይለምኑ ነበር፤
4.    በትዕግሥት የልመናቸውን መልስ ይጠብቁ ነበር፤
5.    የእምነት ምላሽን ሰጥተዋል፤
6.    ስለ እርሱ ይናገሩ ነበር፡፡
1.    በኅብረት ይኖሩ ነበር
እነዚህ ዓይነ ሥውራን ልባቸው ብሩህ ነበር፡፡ በዕድላቸው የሚመረሩ፣ ጌታንም የሚወቅሱ አልነበሩም፡፡ የኅብረታቸው ደኅንነትም በምስጋና ውስጥ ያለ ነው፡፡ ምስጋና የሌለው ኑሮ መሰለቻቸትና መገፋፋትን ያመጣል፡፡ የማያስተውል ሰው ከብርሃኑ ብርሃን ማውጣት ያቅተዋል፣ አስተዋይ ግን ከጨለማው በላይ ለጭላንጭሉ ብርሃን ዋጋ ይሰጣል፡፡ አመስጋኝነት ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋርም ያለንን ኅብረትና ጣዕም ይጠብቃል፡፡ የኅብረታቸው ምንጩ የጋራ ችግር ሳይሆን የጋር እምነት ነበር፡፡ የጋራ ችግር ያጣመራቸው ችግሩ ሲወገድ እርስ በርስ መባላት ይጀምራሉ፡፡
2.   አብረው ይጮኹ ነበር
አባቶች በቅዳሴ ላይ የግል ጸሎት ማድረስ በፀሐይ ፊት ሻማ መለኮስ ነው ይላሉ፡፡ አሳባቸው ከግል ጸሎት የኅብረት ጸሎት ይበልጣል ለማለት ነው፡፡ የጋራ ጸሎት የሥልጣን ጸሎት ነው፡፡ በጋር የምንጸልየውን ጌታ በሰማይ ያደርገዋል (ማቴ. 18÷19)፡፡ እርሱ ኅብረትን የሚወድ አምላክ ነው፡፡ ግለኝነት ለአሁኑ ዘመን ተስማሚ ቢመስልም ጌታ ግን አይወደውም፡፡ ኅብረቱም በጋራ ለመጸለይ እንጂ በጋራ ለመበደል መሆን የለበትም፡፡ ኅብረት የሚባለው የበጎ ነገር ጥምረት ነውና፡፡ ተስማምተን በመጸለይ ያለውን ድል መለማመድ ይኖርብናል፡፡
3.   ብርሃንን ይለምኑ ነበር
እስከ ዛሬ ከሰዎች ገንዘብን ለምነው ይሆናል፣ ብርሃንን ግን ለምነው አያውቁም፡፡ ብርሃንን ቢለምኑም ሁሉም ይስቅባቸዋል፡፡ ብርሃን የሚገኘው ከብርሃናት ጌታ ነውና፡፡ እነዚህ ዓይነ ሥውራን ልበ ብርሃን ነበሩና ከጌታ ትልቁን ነገር ብቻ ሳይሆን ጌታ ብቻ የሚሰጠውን ለመኑ፡፡ ዛሬም ጌታ ብቻ የሚሰጠውን ጥበብ፣ ማስተዋል፣ መዳን ከእርሱ መለመን ይገባናል፡፡
4.  በትዕግሥት የልመናቸውን መልስ ይጠብቁ ነበር
ለጸሎት ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ትዕግሥት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ከመሥራቱ በፊት እኛን ይሠራል፡፡ አሊያ በረከቱን መሸከም አንችልም፡፡ የትዕግሥቱ ጊዜ የእኛ መሠራት ጊዜ እንጂ እግዚአብሔር አቅም የሚያሰባስብበት ጊዜ አይደለም፡፡ እነዚህ ዓይነ ሥውራን ጌታ በአደባባይ ሲለምኑት ዝም ባላቸው ጊዜ ወደ ቤት ተከትለውት ገቡ፡፡ ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ አልተመለሱም፡፡ አንዳንዴ ወደ ቤት እስክንገባ በጽሞናና በፀጥታ እስክንሆን ጌታ ዝም ይላል፡፡ የእግዚአብሔርን ድምፅ የምንሰማው ከግርግሩና ከአጀቡ ለየት ስንል ነው፡፡ ገበሬ የዘራውን በዕለቱ ለማጨድ እንደማይከጅል እኛም የጸለይነውን ጸሎት በጊዜው ለማጨድ ትዕግሥተኛ መሆን ይገባናል፡፡
5.   የእምነት ምላሽን ሰጥተዋል
ጌታ “ምን ያህል ትችላላችሁ?” አይለንም፡፡ “ምን ያህል እንደምችል ታምናላችሁ?” ይለናል፡፡ እርሱ እንዳመነው መጠን መገለጥ ይችላል፡፡ አለማመናችን እንጂ አቅሙ ገድቦት አያውቅም፡፡ እርሱ የእምነት ቃላችንን መስማት ይፈልጋል፡፡ የምናስበውን ቢያውቅም እንድንናገረው ይፈልጋል፡፡ የተናገርነውን እንደገና እናስበዋለንና፡፡ እምነትን ለማሳደግ ስለ እምነት መስማትና መናገር ይገባል፡፡
6.   ስለ እርሱ ይናገሩ ነበር
     ስለ እርሱ እንዳይናገሩ ከልክሏቸው ነበር፡፡ እነርሱ ግን በአገር ሁሉ አወሩ፡፡ በርግጥ የተደረገላቸው ዝም አያሰኝም፡፡ በመንፈሳዊው ዓለም ግን የዝምታና የንግግር ጊዜን ማወቅና ማክበር ይገባል፡፡ የማንናገረው የመሰከርነው ምስክርነት የሚያመጣውን ፈተና መቋቋም እስክንችል ነው፡፡ ደግሞም ሰዎች ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ እውነትን መቀበል አይችሉም፡፡ ስለዚህ ከመናገራችን በፊት መጸለይ ምስክርነትን ቀላል ያደርገዋል፡፡ ወንጌልን የምንናገርው ኃላፊነታችንን ለመወጣት፣ “አረረም መረረም ድግሴን ተወጣሁት” በሚል ሂሳብ ሳይሆን ለሰዎቹ መዳን ካለን ጥልቅ ፍላጎት ተነሥተን ሊሆን ይገባዋል፡፡
የእነዚህ ሁለት ዓይነ ሥውራን እምነት ምን ዓይነት ነበረ? ብለን መጠየቅ ያስፈልገናል፡-
1.     የክርስቶስን ፍጹም ሰውነት ያወቁ ነበር፣ 
2.    የክርስቶስን ፍጹም አምላክነት ተረድተዋል፣
3.    ኃጢአታቸውን አምነዋል፣
4.    ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይ እንደሆነ ተቀብለዋል፡፡
ጌታችን ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ከተዋህዶ በኋላ መለኮትና ሰውነት በአንዱ የክርስቶስ አካል ያለመለያየትና ያለመቀላቀል ፀንተው ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የዳዊት ልጅ ሲሉ ሁለት ነገሮችን ተረድተዋል፡-
1-     ጌታችን ፍጹም ሰው መሆኑንና
2-    የዳዊትን ተስፋ የሚፈጽም ንጉሠ ነገሥት መሆኑን አምነዋል፡፡
ደግሞም “ማረን” በማለታቸው ፍጹም አምላክነቱን ተረድተዋል፡፡ ምሕረትን የሚሰጥ መንግሥት የሆነው ክርስቶስ እንደሆነ አምነዋል፡፡ ኃጢአተኝነት ተሰምቷቸዋል፡፡ በክርስቶስ ቅድስና ፊት ስንሆን ማንነታችን በጉልህ ይታየናል፡፡ ኃጢአተኝነታችን ሲገባን ደግሞ ክርስቶስ በጣም እንደሚያስፈልገን ይገባናል፡፡ እነዚህ ሰዎች የለመኑት የዓይን ብርሃንን ሳይሆን አስቀድመው ምሕረትን ነው፡፡ እግዚአብሔር ከማራቸው ምንም እንደማይቀርባቸው ተረድተዋል፡፡ ከምሕረት በፊት ምንም አልጠየቁም፡፡ ንስሐ ቀዳሚ ነውና፡፡ ያሉበትን ጉዳት አይገባንም አላሉም፡፡ ይገባናል ያሉ ይመስላሉ፡፡ ይገባኛል ማለት ስቃይን ይቀንሳል፡፡ ጌታም ይገባኛል ለሚሉ ተነሣሕያን/ንስሐ ገቢዎች/ ጸጋን ያትረፈርፋል፡፡ እርሱ ችግሩን ሳይሆን የችግሩን ምንጭ ይደፍናል፡፡ ለዚህ ውድቀት ያበቃቸው የችግሩ ምንጭ ብርሃንን ማጣት ነው፡፡ ያንን አስወገደላቸው፡፡ ዛሬም የችግሩ ምንጭ ዕውቀት ማጣት ነው፡፡ ጌታ የልብ ዕውቀትን፣ እውነተኛ ዕውቀትን፣ የሕይወት ዕውቀትን ያድለን!!!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ