የትምህርቱ ርዕስ | ሁልጊዜ

                                       ቤተ ጳውሎስ ቅዳሜ ሰኔ 23/2004 ዓ.ም.
ምሽቱ እጅግ መልካም ነበር፡፡ ስለ እግዚአብሔር ታላቅነት፣ ስለቅድስና ኑሮ፣ ስለጸሎት ኃይል፣ ስለአንድነት ማሰሪያ፣ በኑሮ ስለሚገለጠው ምስክርነት፣ ስለበቂ አመራር፣ ከማድረግ በፊት መሆን እንደሚቀድም … የተነጋገርንበት ምሽት ስለነበር ደስታዬ ብዙ ነው፡፡ እውነተኛ እውነት፣ እውነተኛ ፍቅር፣ እውነተኛ ኅብረት ደስ ያሰኛል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ማሰሪያ ምኞትንና ፈቃድን በሙሉ ለእግዚአብሔር የምንተውበት ጸሎት ሲሆን የጸሎት ማሰሪያም ቆይታውን መንፈሳዊነትን ይጎናጽፈዋል፡፡ የሰው ልጅ ምኞት የሚጎላው፣ ፈቃዱ ፍጻሜ የሚያገኘው በእግዚአብሔር ሲሆን ንግግራችንን ከተራ ስብሰባ፣ ጉባዔአችን ከተለመደው ሸንጎ ልዩ የሚያደርገው የጸሎትን ኃይል ስንጠቀም ብቻ ነው፡ መኸሩ ሲታጨድ ወደ ጎተራ እንዲደርስ በነዶ መታሠር አለበት፡፡ በነዶ ካልታሠረ እርሻው ላይ ተበታትኖ ይቀራል፡፡ ጸሎት የነዶው ማሠሪያ፣ የአሳብ መጠቅለያ፣ የስምምነት ፊርማ፣ የጅማሬ ሞተር፣ የፍጻሜ ውበት ነው፡፡
ካለፉት ዘመናት ይልቅ ወጣቶች እግዚአብሔርን ለማገልገል መቁረጣቸውን ሳይ፣ ጠላት ለክፋት የጨከነውን ያህል የእግዚአብሔር ልጆች በቅድስና ለመግፋት በመጨከናቸው ደስ ይለኛል፡፡ በቅዳሴው ላይ የወንጌልህን ቃል በመጨከን እንድንሰማ እርዳን ይባላል፡፡ ወንጌልን ለመስበክም ሆነ ለመስማት ጭካኔ ያስፈልጋል፡፡ ወንጌል ልምዴ፣ ተፈጥሮዬ፣ ርእዮተ ዓለሜ፣ ዕውቀቴ፣ ባሕሌ፣ ዕድሬ፣ … ከምንለው ጋር ስለማይስማማ የወንጌልን ቃል በመጨከን መስማት ግድ ይላል፡፡ አሳባቸውን እንዲያጸድቅላቸው ወደ እግዚአብሔር የሚመጡ መንጌልን ሊሰሙ አይችሉም፡፡ ወንጌል የእግዚአብሔር ዘላለማዊ አሳብ ነው፡፡ የሰው አሳብና የእግዚአብሔር አሳብ ርቀቱ እንደ ሰማይና ምድር የማይገናኝ ነው/ኢሳ. 55፡8-9/፡፡ እኛ ወደ እግዚአብሔር አሳብ እንጠቀለላለን እንጂ እግዚአብሔር ወደ እኛ ሐሳብ አይጠቀለልም፡፡ እንዲያ ከሆነ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሆኑ ይቀራል፡፡ ወንጌልን ለመቀበል ከእኔ ዕውቀት ሞኝነት የሚመስለው የእግዚአብሔርን ወንጌል ይበልጣል ማለትን ይጠይቃል/1ቆሮ.1፡25/፡፡ እነዚህ ሁሉ መንፈሳዊ ወጎች ልቤን ሞልተውታል፡፡
ማለዳው እንዲቀለን እራት በጊዜ መብላት፣  በጊዜም መተኛት ተገቢ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ የቀኑን ሩጫ በእውነት ቃል ፈጽሞ መተኛት፣ ወሎውን ሁሉ በእግዚአብሔር የሥልጣን ዙፋን ፊት አስተንትኖ ማረፍ ማለዳውን በኃይል እንድንነሣ ያደርገናል፡፡ እግዚአብሔር ርእስ የሆነበት ምሽት፣ እግዚአብሔር ብቻውን የከበረበት ሌሊት የማለዳው ጣዕም ነው፡፡ ከወትሮ በተለየ በማለዳ የደረሰኝ መንፈሳዊ መልእክት የበለጠ ልቤን በኃይል፣ አንበደቴን በምስጋና ሞላው፡፡ ለመጻፍ ገና ብዕሬን እንዳነሣው የደረሰኝ ጥቅስ የጠዋት ቁርስ ሆነልኝ፡፡ አብሮ መብላት ባህልም ነውና አብረን ብንበላው ብዬ ያሰብኩትን ትቼ ያሰበልንን ለመጻፍ ተነሣሁ፡፡ እግዚአብሔርን እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁ፡፡ ቃሉን የዕለት ምሪት፣ የዘመናት ጌጥ አድርጎ ስለሰጠኝ በልቤ አከብረዋለሁ፡፡ የተመረተውን ጥይት አስገብተን ብንተኩሰው እንገድላለን፡፡ የተጻፈውንም ቃል ብንልከው እናድናለን፡፡ የዳንኩበት ያ ጥቅስ እንዲህ ይላል፡-
“ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤
ሳታቋርጡ ጸልዩ፤
በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር
ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና”
                         (1ተሰ. 5፥16-18)፡፡
ክርስትና አንዳንድ ጊዜ፣ ክርስትና በሠርክ ጉባዔ፣ ክርስትና በሰንበት አምልኮ፣ ክርስትና በዓመት በዓል፣ ክርስትና በወር መባቻ፣ ክርስትና በጡረታ ዘመን፣ ክርስትና ነገሮች ሲወዳድሙ፣ ክርስትና ግራ ሲገባን ሳይሆን ክርስትና የሚያቋርጥ ሕይወት ነው፡፡ ክርስትና በየዕለቱ የሚበላ እንጀራ እንጂ የበዓል ቀን የምንቆርሰው ኬክ አይደለም፡፡ ክርስትና ሕይወት ነው፡፡ ሕይወት የማያቋርጥ የኑሮ ሥርዓት፣ የተዋበ መገለጫ ነው፡፡ ለብዙዎች ክርስትና ወቅታዊ ነው፣ ክርስትና በዓል ነው፡፡ ስለ ክርስትና ተናገሩ ሲባሉ ከክርስቶስ ልደት ስለ ገና ጨዋታ፣ ከክርስቶስ የትሕትና ጥምቀት፣ ስለ ጥምቅት ዘፈንና መተጫጨት፣ ከክርስቶስ ትንሣኤ ለወላጆች ስለሚወሰደው አክፋይ፣ ከደብር ታቦር መለኮታዊ ክብር ስለ ቡሄ ጨዋታ፣ … ይናገራሉ፡፡ ክርስትና ባሕላዊ እሴት ሳይሆን ክርስትና ሕይወት ነው፡፡ ክርስትና ባሕሉን ያደምቀዋል እንጂ ባሕሉ የክርስትና ምትክ መሆን አይችልም፡፡ ክርስትና የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅር በደም የተጻፈበት መንፈሳዊ ሰነድ ነው፡፡ ይህ ካልገባን ከሥጋው ጦመኛ ነኝ ከመረቁ አውጡልኝ የምንል ይመስላል፡፡ ፍቅሩን እየጦሙ መረቁን መጠጣት ጠቀሜታው ያነሰ ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የክርስትናን ሕይወትነት “ሁልጊዜ – ሳታቋርጡ – በሁሉ” በሚሉ ቃላቶች ይገልጸዋል፡፡
ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ
የምናውቀው ደስታ ስሜት እንደሆነ ነው፡፡ የሚያስደስት ነገር ሲገጥመን ደስ ይለናል፡፡ በዚህ ክፍል ላይ ደግሞ ደስታ ትእዛዝ ነው፡፡ ትእዛዝ አማራጭ ያለው ነገር ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ የምንደሰተው ደግሞ ስናገኝ፣ ጤና ስንሆን፣ ወዳጆቻችንን ስናገኝ፣ በትምህርት ስንመረቅ፣ ስናገባ፣ ልጆቻችንን ስንድር ሳይሆን ሁልጊዜ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ለልጆቹ የመደበው የማያቋርጥ ደስታን ነው፡፡ የደስታ መሠረቱ ሁኔታው ሳይሆን እውነቱ ነው፡፡ እውነቱ ቋሚ የሆነው ጌታ ነው፡፡
ሁልጊዜ ደስ የምንሰኝበት ምሥጢሩ ምንድነው; ስንል በሌላ ስፍራ ላይ መልሱ ተቀምጧል፡- “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ” ይላል (ፊልጵ. 4፥4)፡፡ የሁልጊዜ ደስታ ምሥጢሩ ጌታ ነው፡፡ የደስታ መሠረቱ ራሱ እግዚአብሔርና እግዚአብሔር የሠራው ነገር ነው፡፡ ማዘን መብታችን እንደሆነ ቢሰማንም ደስታ ግን ከመለኮት የተሰጠን መብታችን ነው፡፡ ስለዚህ በጌታ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ሁልጊዜ በሀብት፣ ሁልጊዜ በትዳር፣ ሁልጊዜ በልጅ ደስ መሰኘት አይቻልም፡፡ የሁልጊዜ ደስታ ክርስቶስ ጌታ ብቻ ነው።
አንድ አባት ሁልጊዜ አግኝቻቸው እንደምን ዋሉ; ስላቸው ምን ደህንነት አለ? ብለው ይበሳጫሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የፖለቲካው ውዝግብ፣ የኢኮኖሚውን መቃወስ፣ የሃይማኖቱን መተራመስ፣ የቤት ኪራይ ውድነት፣ … ይተነትኑታል፡፡ አዎ ሁኔታውን ካሰብን መደሰት አንችልም፡፡ ከሁኔታዎች በላይ የሆነው ጌታ ግን ደስታችን ነው፡፡ ሁኔታው እንዲህ ሆኖ መኖራችን ይህ የእግዚአብሔር ፍቅር ነውና ደስ ሊለን ይገባል፡፡
መንፈሳዊ ደስታችንን ለመጠበቅ አብዝተን መጸለይ፣ ከመረጃ ይልቅ መርጃ የሆነውን ቃሉን ማንበብ፣ ድሆችን መጐብኘት፣ በበጎ ሥራ መጽናት፣ የይቅርታ ሕይወትን መለማመድ አስፈላጊ ነው፡፡ የሀዘን ነፋስ ባለበት ዓለም የማይጠፋ የደስታ መቅረዝን መለኰስ መታደል ነው፡፡
ሳታቋርጡ ጸልዩ
አንዲት ዘበናይ ሴት ስለ ጸሎት ስንነጋገር፡- ‘‘እግዚአብሔር ሁልጊዜ ስለምትጨቀጭቁት እናንተን የጠላችሁ ይመስለኛል፡፡ እኔ በዓመት አንድ ጊዜ ነው የምጸልየው’’ አለች፡፡ ጸሎት ግን ኅብረት እንጂ ጉዳይ አይደለም፡፡ ጤናዬን የሚከታተል ሐኪም አለኝ፡፡ ወዳጄ ነው፡፡ ከመወዳጀታችን የነሣ ላለፉት 18 ዓመታት በነጻ ያክመኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ካንተ ሕመም የእኔ ይበልጣል፣ ያንተን ተወውና ቃሉን ንገረኝ ይለኛል፡፡ ታዲያ ይህንን ወዳጄን ካላመመኝ በቀር ልጠይቀው ሄጄ አላውቅም፡፡ እግዚአብሔር አባት ነው፡፡ ልጅ አባቱን የሚያገኘው ለፍቅር እንጂ ለጉድለት ብቻ አይደለም፡፡ ጸሎት የጥቅም ማሟያ ሳይሆን የፍቅር ኅብረት ነው፡፡ እግዚአብሔር ልጆቹን ማግኘት ይፈልጋል፡፡ “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር” በሉኝ ያለው ለዚህ ነው፡፡
ጌታችን ሳይታክቱ ስለመጸለይ ተናግሯል/ሉቃ.181-7/፡፡ ሳይታክቱ መጸለይ እምነት ነው፡፡ አንድ ልጅ አባቱን ያለማቋረጥ የሚለምነው አባቱ እንደሚያደርግለት ስላመነ ነው፡፡ የማያቋርጥ የጸሎት ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ከጠላቶቻችን ይልቅ አለመጸለያችን እንዳይጥለን ያሰጋል፡፡ ጦርነት ጀምሮ በውጊያ መሐል መዝናናት የጀመረ ወታደር ዕድሜው አጭር ነው፡፡ እንዲሁም ጸሎትን ጀምሮ ሊገፋ ያልቻለ ውጊያው ይበዛበታል፡፡ ይህ ጠላትን አነቃቅቶ ወደኋላ እንደማለት ነው። በመንገድ ስንሄድ፣ ዐረፍ ስንል፣ አውቶቢስ ስንጠብቅ፣ ሰዎች ቀጥረውን ሲዘገዩ፣ … ጊዜውን በጸሎት መጠቀም ወደ ድል ምሥጢር፣ ወደ ጣዕመ ሕይወት ያደርሳል፡፡ የጸሎት ሰዎች ዕድሜአቸው የገፋ፣ ደስታቸው የበዛ፣ በረከታቸው የሰፋ ነው፡፡ ንጉሡን ለመርዳት እኛ ደካማ ነን። ብንጸልይ ግን ንጉሡን እንረዳዋለን፡፡ የደካሞች ሁሉ ኃይላቸው ጸሎት ነው፡፡
በሁሉ አመስግኑ
የገዛ ቃላችን እንዳንደሰት፣ እንዳንራመድ ያስረናል፡፡ ብዙ ሰዎች ጠግበው ከበሉ በኋላ፡- “ይህን በላ ብለህ አታሳጣኝ” ይላሉ፡፡ የሰጠህ እንዳይመስልህ ማለታቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ማመስገን እንዴት ይችላሉ? ምስጋና የመደነቅ ውጤት ነው፡፡
የደረሱብን ነገሮች በርግጥም የሚያሳዝኑ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ እንድናመሰግን እግዚአብሔር ፈልጓል፡፡ እግዚአብሔር ይህን ያለው ጉልበተኛ ስለሆነ ይሆን; አይደለም። በምስጋና ውስጥ ድል ስላለ ነው፡፡ ጨለማው የሚበራው፣ የወኅኒው ደጃፍ የሚከፈተው፣ ሰንሰለቱ የሚበጠሰው፣ .… በምስጋና ነው/የሐዋ.16፡25-34/፡፡ አመስጋኞች ያለ ውጊያ ድል ያደርጋሉ። ቃሉ፡- ‘‘ዝማሬውንም ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ ’’ ይላል/2ዜና. 20፡22/፡፡
ትላንት ስላለፍነው ቀይ ባሕር ብቻ ሳይሆን ከፊታችን ስላለውም የዮርዳኖስ ፈሳሽ ምስጋና እንጀምር። ምስጋና ባሕር ይከፍላል!
የሁልጊዜ ሰዎች እንሁን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም