ቤተ ጳውሎስ፣ ማክሰኞ ሚያዚያ 2 2004 ዓ.ም.
ከብርሃናት ዙፋን የአህያ ጀርባ
ከወርቅ ምንጣፍ ይልቅ መናኛ ዘንባባ
ከሊቃውንት ይልቅ የህፃናት አፍላ
ወዶ የመረጠ እንደ ማር ወለላ
ዝቅ ዝቅ ብሎ ውርንጫይቱን ሽቶ
ባማረ ሰገነት መቀመጥን ትቶ
ሠላማዊ ነቢይ የሰላም አለቃ
በሚጠቡ ህፃናት ለመመስገን በቃ፡፡
በፍርድ ምልክት እሾሀማ ዘንባባ
በፈውስ ትዕምርት በልስልሱ ወይራ
ታጅቦ በህጻናት በአላዋቂዎች
ታየ መድሀኒዓለም ድንቁ የምስራች
ቃል አካላዊ ቃል ሰማያዊ
ድሀ የማትረሳ ደግ ሣምራዊ
ሆሳዕና ላንተ አሁን ለምታድን
ለነፃነት ጌታ ለምትፈታ እስርን
ርቃችሁ የምትቆሙ ሊቀ ሊቃውንቱ
ተከፍቶ ዕልፍኙ የልባችሁ ቤቱ
ምስጋናውን አብዙ ለከበረ ስሙ
ለትሁቱ ጌታ በትህትና መንፈስ እናንተም ተቀኙ፡፡
ህፃን አፍን ከፍቶ
ድንጋይ ድምጽ ሠጥቶ
ድርቡን ምስጋና ቅኔ ከተቀኘ
እናንተ ታላላቅ ምነው ቀኝ ዐይናችሁ ክፉ ተመቀኘ?
ሆሳዕና ለርሱ ላዳነን መከታ
በክንፎቹ ጥላ ላሳረፈን ጌታ፡፡