የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለሕፃናት የተብራራ(ማቴ.11፡25)

                            የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ               ቅዳሜ፣ ነሐሴ 24/ 2006 ዓ.ም.
ሕፃናት የሚነገራቸው ጨዋታ እንጂ ቁምነገር አይደለም፡፡ የሰጠናቸውን የሚቀበሉ አዲስ እንግዶች ቢሆኑም የምንሰጣቸው ግን ሕይወትና እውነትን ሳይሆን ጨዋታን ብቻ ነውና ባደጉ ጊዜ የእኛ አይሆኑም፡፡ በጠዋቱ ያልማረክነው እስከ ማታ አይቆይልንም፡፡ ጠዋት የምንለው እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት ከሆነ ለሕፃናት ውድ አምስት ሰዓቶች አልፈዋል ማለት ነው፡፡ ሕፃናት ዘላለማዊውን እውነት ከአራስ ቤት ጀምሮ መስማትና መለማመድ አለባቸው፡፡ እኛ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ልንነግራቸው ብዙ እውነቶችን በልባችን ሰውረናል፡፡ አካለ መጠን ግን እስከዚያ ድረስ የሰሙትን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ የሚወጡበት የመስክ ሜዳ እንጂ የመማሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ ትልቅ የሆነውን ጉዳት ልጅ የወላጆቹን አሳብ ወዲያ የሚልበት ነው፡፡ ብዙ ወላጆች ተሰብረው ያነባሉ፡፡ ግን ውድ ሰዓቶችን ባለማወቅ እንዳሳለፉ አይገነዘቡም፡፡
ሕፃናት እስኪያድጉ ድረስ የማንነግራቸው ብዙ እውነቶች አሉ፡፡ በሽታቸውን፣ እውነተኛ ወላጆቻቸውን፣ የቤተሰቡን ዝብርቅርቅ፣ የቤቱን መሠረታዊ ችግር፣ በአገሪቱ ላይ ያለውን ተጨባጭ አደጋ . . . እንሸሽጋቸዋለን፡፡ ይህ መልካም ሊሆን ይችላል፡፡ ሕፃናት ግን ከእኛ ይልቅ ለእግዚአብሔር የቀረቡ፣ እኛ የከበደንን እምነት በተፈጥሮ የታደሉ፣ እግዚአብሔርን እያዩ ማምለክ የሚችሉ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል፡፡ በማስተዋልም ያበረታቸዋል፤ በፍቅርም ያበለጽጋቸዋል፡፡ በርኅራኄም ያሰለጥናቸዋል፡፡

ሕፃናት በብዙ ቁምነገሮች ተንቆጥቊጠዋል፤ ነገር ግን አንሰማቸውም፡፡ ቊምነገር ሲያወሩን እንቀልድባቸዋለን፡፡ እውነተኛውን እውነት ሲነግሩን ከትልቅ ሰው ይልቅ እንፈራቸዋለን፡፡ ይህስ፣ ይህችስ አያደጉም እንላቸዋለን፡፡ የማይሰሙ እየመሰሉን በፊታቸው ብዙ የማይገቡ ነገሮችን እንናገራለን፡፡ የማይሰማቸው እየመሰለንም ፀያፍ ንግግር እንናገራቸዋለን፡፡ እነርሱን ዘፈን ከልክለን በፊታቸው ስንዘፍን ይገስጹናል፡፡ የሰሙትን የመኖር ጥማታቸውን አንጠቀምበትም፡፡ አጥንታቸው ለመቆም የማይችል ለጋ መሆኑን እየዘነጋን ወንበር አንለቅላቸውም፤ ልጅ ነው ይቁም እንላለን፡፡ ቶሎ ቶሎ እንደሚርባቸው ደግሞም ጉጉዎች መሆናቸውን እየረሳን ልጅ ነው ኋላ ይበላል፣ ትበላለች እንላቸዋለን፡፡ የሚማሩ፣ በንግግር የሚያምኑ ስለማይመስለን በዱላ ብቻ እናሳምናቸዋለን፡፡ ጆን ደብልዩ ሎረንስ የተባለ ፀሐፊ በመጽሐፉ እንዲህ ብሏል፡-


ልጅ እየተወቀሰ ካደገ ማውገዝን ይማራል፡፡
ልጅ በጥላቻ አካባቢ ካደገ መደባደብን ይማራል፡፡
ልጅ እየተፌዘበት ካደገ ዓይነ አፋርነትን ይማራል፡፡
ልጅ በሐፍረት ካደገ ጥፋተኝነትን ይማራል፡፡
ልጅ በመቻቻል ካደገ ትዕግሥተኝነትን ይማራል፡፡
ልጅ በመበረታታት ካደገ በራስ መተማመንን ይማራል፡፡
ልጅ በመሞገስ ካደገ ማድነቅን ይማራል፡፡
ልጅ በአግባብ ካደገ ፍትሕን ይማራል፡፡
ልጅ ዋስትና ባለው ኑሮ ካደገ ሰውን ማመን ይማራል፡፡
ልጅ በተቀባይነትና በወዳጅነት ካደገ በአጠቃላይ ዓለም ፍቅርን ማግኘት ይማራል፡፡
ጌታችን፡- “አባት ሆይ የሰማይና የምድር ጌታ÷ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ” በማለት ጸለየ (ማቴ. 11÷25)፡፡ ይህ ዓለም በመለኪያ የሚታወቅ፣ ይህ ነው ተብሎ ፈርዶ ለመናገር የማያስችል ዓለም ነው፡፡ ይሆናል ያልነው የማይሆንበት፣ አይሆንም ያልነው በረከት እኛን የሚከተልበት፣ ትልቅ ተስፋ የጣልንባቸው መና ሲሆኑ የምናስተውልበት፣ ተስፋ የቆረጥንባቸው አለኝታችን የሚሆኑበት፣ የአንድ ዘመን ደፋር ፈሪ ሆኖ የሚኮስስበት፣ ፈሪው ምድር የማይበቃው ደፋር የሚሆንበት አድራሻ የሌለው፣ ጥቁር ወይም ነጭ የማይባል ዓለም ነው፡፡  
        ይልቁንም በመጨረሻው ዘመን፡- “መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆት÷ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል” ተብሎ ለነቢዩ ኤልያስ ትንቢት ተነግሮአል (ሚል. 4÷6)፡፡ የትንቢቱ ፍጻሜ ልጆች እንደ አባቶች ያስባሉ፣ አባቶች እንደ ልጆች ያስባሉ ማለት ነው፡፡ በእውነት በልጆቻቸው ሐፍረታቸው እየተሸፈነ የሚኖሩ ወላጆች፣ በልጆች ጥረት የቆሙ ትዳሮች ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ትንቢት በዘመናችን ፍጻሜ አግኝቷል፡፡ በየቤተ ክርስቲያኑ የወጣቱን ያህል አረጋውያንን አለማየት ይህን ትንቢት የሚያጠናክር ነው፡፡ ተመካሪው መካሪ፣ መካሪው ተመካሪ በሚሆንበት ዘመንም እግዚአብሔር ምሕረቱን አያርቅም፡፡ ታላቁ ሊቀ ካህን ዔሊ፣ አረጋዊው አገልጋይ እያለ እግዚአብሔር ብሔራዊ ጉዳይን ያወጋው ከሦስት ዓመት ሕፃን ከሳሙኤል ጋር ነው (1ሳሙ. 3)፡፡
        ኦሪት፡- “በሽበታሙ ፊት ተነሣ÷ ሽማግሌውንም አክብር አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” (ዘሌዋ. 19÷32) ይላል፡፡ በሽበታሙ ፊት የሚነሣው በሽበታሙ ወንበር ተቀምጦ የነበረው ጎበዝ ነው፡፡ ሽበታሙ እስኪመጣ፣ ሽማግሌው እስኪሰየም ሽማግሌው ወጣቱ ነው፡፡ ዛሬም ሽማግሌዎች ሊይዙት የሚገባው ብዙ ስፍራ አለ፡፡ ሽማግሌዎቹ እስኪመጡ እኔ ነኝ ሽማግሌው ብሎ መሥራት ይጠበቃል፡፡ እግዚአብሔር የሚያከብረው ዕድሜን ሳይሆን የሚያከብሩትን ነው፡፡ “ያከበሩኝን አከብራለሁና የናቁኝም ይናቃሉና” ይላል (1ሳሙ. 2÷30)፡፡
        ወጣቱ ልስበክ እያለ መሪ ሽማግሌዎች ስብከት አያስፈልግም ካሉ፣ ሊጸልዩ የሚገባቸው አባቶች የልጆችን ጸሎት ካደናቀፉ በርግጥም ትንቢቱ ተፈጽሟል፡፡ እግዚአብሔር በሚሠራበት ቀን ጥበበኞች አላዋቂ፣ ምኞች አስተዋይ ይሆናሉ፡፡ ጌታችን ይህን ባሰበ ጊዜ ታላቅ ሐሴት አደረገና፡- “አባት ሆይ የሰማይና የምድር ጌታ÷ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ” አለ (ማቴ. 11÷25)፡፡
ትምህርት፣ የትምህርት ቤት የማይሰጠን ዕድሜም የማያስገኝልን መንፈሳዊ ጥበብ አለ፡፡ ይህ ዕውቀት መገለጥ እንጂ በወንበር ከተሰየሙ ሊቃውንት አፍ የሚወጣ አይደለም፡፡ ይልቁንም ስለ እግዚአብሔር የምናውቀው እግዚአብሔር ስለ ራሱ ሲገልጥልን ብቻ ነው፡፡ ይህ ዕውቀት ወንበር ካደላደሉ፣ ከታወቁ ሊቃውንት፣ የምስክር ወረቀት ካላቸው፣ የሥነ መለኮት ዲግሪ ከቆለሉ ሰዎች የተሰወረ ለትሑታን ገበሬዎች ግን የተብራራ ነው፡፡
‹‹ራሱን ቸል ብሎ የፕላኔቶችንና የከዋክብትን እንቅስቃሴ ከሚያጠና ትዕቢተኛ ተመራማሪ ፈላስፋ ይልቅ እግዚአብሔርን በንጹሕ ልብ የሚያገለግል ትሑትና መሃይም ገበሬ ይበልጣል፡፡››
ጌታችን፡- “አባት ሆይ የሰማይና የምድር ጌታ÷ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ” በማለት አመሰገነ፡፡ እነዚያ ሕፃናት የተባሉ የገሊላ ገበሬዎች ደቀ መዛሙርቱ ናቸው፡፡ አስተዋዮችና ጠቢባን የተባሉት የሕጉ ተርጓሚዎች ፈሪሳውያንና ጻፎች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ምሥጢር የሆነው ክርስቶስ ከእነዚህ ተመራማሪዎች ተሰውሮ ለምስኪኖች የአእምሮ ሕፃናት መገለጡ ይደንቃል፡፡ ትንቢት የሚያጠኑ፣ ሱባዔ የሚቆጥሩ ያልገባቸው ለዓሣ አጥማጆች ተገለጠ፡፡ ዛሬም ክርስቶስ እየበራላቸው ያሉት ዕውቀታቸውን ለሚያስተነትኑ፣ አቦ አቦ ለሚባሉት ክቡራን ሳይሆን በዕድሜም በአእምሮም ሕፃናት ለሆኑት ወገኖች ነው፡፡ እኛ ሳናየው በየት በኩል አልፎ አገኛችሁት እያሉ እነዚህን ሕፃናት ቢገፏቸውም እግዚአብሔር ግን እንደ ጥንቱ እየሠራ ነውና ደስ ይለናል፡፡ አዎ ነገር ስለሚገባን የክርስቶስ ነገር አይገባንም፡፡ ሳይንስን ባወቅንበት አጠናን ክርስቶስን መረዳት አይቻለንም፡፡ እርሱ በእምነትና በትሕትና የሚገኝ አምላክ ነው፡፡ እርሱ ለሊቃውንት የተሰወረ ለትሑታን የተገለጠ፣ በሊቃነ ካህናት ሞት የተፈረደበት፣ በኃጢአተኞች ግን ውድ ሽቱ የተሰበረለት ነው፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ