የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለማስተማር የሚበቃ

“እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል ፤ … ለማስተማር የሚበቃ” 1ጢሞ. 3 ፡ 2
ፀሐይ ስትጠልቅ ሁሉም ወደ ቤቱ ይሰበሰባል ፤ ፀሐይ ስትወጣ ሁሉም ወደ ተግባሩ ይሰማራል ። ብርሃን የመውጣት ድፍረት ነውና ። ብርሃን የዓይን ዋጋ ነው ። ብርሃን ራስን መመልከቻ ነው ። ብርሃን ሌላውን የምናይበት ነው ። ብርሃን ውበትን ማድነቂያ ነው ። ብርሃን መገናኛ ነው ፤ ብርሃን ማታ የተሰነባበተ ጠዋት “እንዴት አደርህ ?” የሚባባልበት ነው ። ብርሃን ነጻ ስጦታ ነው ። ብርሃን ተስፋ ሰጪ ነው ። ብርሃን መንገድን መመልከቻ ነው ። ብርሃን እግርን ከገደል የሚያድን ነው ። ብርሃን መታከሚያ ነው ። ብርሃን ማፍቀሪያ ነው ። “ዓይን ነው ዘመዱ” እንዲሉ ። ብርሃን የወደቀውን አይቶ ማዘኛ ነው ። ብርሃን አራዊትን የሚገሥጽ ነው ። ብርሃን የፈሩትን የሚያደፋፍር ነው ። ብርሃን ሕመም የጠናባቸውን የሚያስታግሥ ነው ። በሽተኛ ሌሊት ሲብስበት ቀን ይሻለዋልና ። ብርሃን የልብ ድፍረት ነው ። በአጠቃላይ ራሱ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ። ነቢዩም፡- በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን” ብሏል ። መዝ. 35 ፡ 9 ። በብርሃን ቃልህ ብርሃን ልጅህን/ወልድን/ እናያለን ማለቱ ነው ።

እውቀት ብርሃን ሲሆን ማስተማርም ብርሃን ማብራት ነው ። ብርሃን የሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት እየሆነ መጥቷል ። ትምህርትም የሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት ነው ። የሚያስተምር ብርሃን የሚያበራ ብቻ ሳይሆን እንደ ገና የሚወልድም ነው ። ፀሐይ ስትጠልቅ ሁሉ እንዲሰበሰብ አላዋቂነት ሲነግሥም አዋቂ ይሸሸጋል ። ፀሐይ ስትወጣ ሁሉ እንዲወጣ እውቀት ዋጋ ሲያገኝ ጨዋዎች ድፍረት ያገኛሉ ። ሴቶች ከማጀት ወደ አደባባይ የሚወጡት በትምህርት ነው ። ብርሃን ድፍረት እንዲሰጥ እውቀትም ድፍረት ይሰጣልና ። ዓይን ያለ ብርሃን ለጌጥ እንኳ እንደማይሆን ፣ እንደ ተፈጠረ ያለ ሰውም ያለ ትምህርት ብቁ አይሆንም ። ብርሃን ራስን መመልከቻ እንደሆነ እውቀትም ያሉበትን አድራሻ የሚያሳውቅ ነው ። ብርሃን ሌላውን እንደሚያሳይ እውቀትም ስለ ሌሎች ማሰብን ይሰጣል ። ብርሃን ውበትን ማድነቂያ እንደሆነ እውቀትም በተፈጥሮ ላይ ያረፈውን የእግዚአብሔርን ጥበብ ያሳያል ። ብርሃን መገናኛ እንደሆነ እውቀትም የተራራቁትን ያቀራርባል ። ብርሃን ነጻ ስጦታ እንደ ሆነ እውቀትም አይሸጥም ። ከዋጋ በላይ ነውና ። ብርሃን ተስፋ ሰጪ ነው ፤ ብርሃን በሚሰወርባቸው ወራት ብዙ ሰዎች ድብርት ውስጥ ይገባሉ ። እውቀትም በዛሬው ነገር እንዳንዳከም ይነግረናል ። ብርሃን መንገድ ማመልከቻ እንደሆነ እውቀትም መድረሻን ያሳያል ። ብርሃን እግርን ከገደል እንዲያድን እውቀትም ከጥፋት ይመልሳል ። ብርሃን መታከሚያ እንደሆነ እውቀትም አስተሳሰብን ይፈውሳል ። ብርሃን ማፍቀሪያ እንደሆነ እውቀትም ከጥላቻ ነጻ ያወጣል ። ብርሃን የወደቀውን አይቶ ማዘኛ እንደሆነ እውቀትም ለተጎዱት መራራትን ይሰጣል ። ብርሃን አራዊትን እንዲገሥጽ ፣ እውቀትም ጨካኞችን ይገሥጻል ። ብርሃን ለፈሪዎች ድፍረት እንዲሰጥ እውቀትም ለምስኪኖች ሞገስ ይሆናል ። ብርሃን ሕመም እንዲያስታግሥ ትምህርትም ከንቱ ጉዳትን ይቀንሳል ። ብርሃን እግዚአብሔር እንደሆነ ሁሉ ልንማረው የሚገባን አምላክ ነው ።
በዚህ ዓለም ላይ ገዳይ መሣሪያ የሠሩ አዋቂዎች አሉ ። ዘረኝነትን ያስፋፉ የተማሩም አልጠፉም ። እውቀት ያልነው ግን እግዚአብሔርን ማወቅ ነው ። የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው እንዲል እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ሀሁ ነው ። እግዚአብሔርን መፍራት የሌለበት እውቀት ያልተጀመረ እውቀት ነው ። ጨለማን የፈራ ጤነኛ ነው ፤ ብርሃንን የፈራ መታገዝ ያለበት ታማሚ ነው ። አለማወቅን መፍራት ሲገባ እውቀትን መፍራት ግን ሕመም ነው ።
ኤጲስ ቆጶስ ለማስተማር የሚበቃ መሆን አለበት ። ባለ ማወቅ ምክንያት ወደ ራሳቸው በጣም በማየት ተስፋ የቆረጡ ፣ ወደ ሰዎች በጣም በመመልከት ድንጉጥ የሆኑ ብዙ አሉ ። ኤጲስ ቆጶስ ለማስተማር ሲነሣ እነዚህን ምንዱባን ያድናል ። ካሉበት ዓለም ውጭ ሌላ ዓለም አልታይ ብሏቸው የሚኖሩ የኅሊና እስረኞች ፣ እኔ ዋጋ የለኝም ብለው ባርነትን አጣጥመው ለመቀጠል የፈቀዱ ሞኞች ዛሬም አሉ ። ተምረው የደነቆሩ ፣ አውቀው የደነዙ ብዙ ሰዎች በየዕለቱ እየፈሉ ነው ። ከልብስ ዘልቀው ማየት የማይችሉ ፣ ሰውን በቤቱ የሚለኩ ብዙ ሚዛን የለሾች እየተስፋፉ ነው ። ራሳቸውን አጽድቀው ሌላውን የሚኰንኑ ፣ እኔን ብቻ ይድላኝ ብለው ጎረቤታቸውን የሚያውኩ አያሌ ናቸው ። የእኔ የግሌ ፣ የእነ እገሌ የጋራችን ነው ብለው የሚያስቡ ፣ ለእነርሱ የተፈጠረውን ዓለም ማየት ያልቻሉ ፣ በጉዳተኝነት ስሜት የሚያነክሱ ፣ ተጎዳሁ እንጂ ጎዳሁ የማይሉ ፣ የሚያገናኙ ድልድዮችን አፍርሰው የሚለያዩ ግንቦችን የሚሠሩ ፣ መሰናበት እንጂ መገናኘት የማይችሉ ፣ ቆጥበው የማይጣሉ ፣ ገርበብ አድርገው ሳይሆን በር ቆልፈው የሚሄዱ ፣ መመለሻ ድልድያቸውን የሚያፈርሱ የትየለሌ ናቸው ። ነጻ የሆነውን ፍቅር ፣ ነጻ የሆነውን መልካም ቃል ለመስጠት የተቸገሩ ፣ ለክፋት ነቅተው ለደግነት የሚተኙ ፣ ነገ አልታይ ብሏቸው ዛሬ ለመጫረስ የወጡ ፣ አይተው መርገጥ ተስኖአቸው ረግጠው የሚያዩ ፣ ገደል አፋፍ ላይ የሚጨፍሩ ፣ ታስረው የሚዘፍኑ ፣ ምነው የሰው ሁሉ አንገት አንድ በሆነልኝ ብለው በአሳብ የሚፈጁ ፣ ከራሳቸው ጋር ላለመገናኘት መምህራንን የሚጠሉ ብዙ ናቸው ። ኤጲስ ቆጶስ ለማስተማር የሚበቃ መሆን ያለበት እነዚህ ሁሉ ስለሚጠብቁት ነው ። ወታደር ሰይፍ ይይዛል ፣ ካህንም ትምህርት ሊይዝ ይገባዋል ። ያለ መሣሪያ ወታደርነት ፣ ያለ ትምህርት ክህነት ለመሸነፍ ነው ።
“የየጁ ደብተራ ቅኔ ቢያልቅበት ቀረርቶ ሞላበት” እንዲሉ በአደባባይ ስድብ የሚያስጠኑ አስተማሪዎች ትምህርት ያለቀባቸው ናቸው ። አደባባይ መቆም ሥራው የሆነ መናገር ግዴታው ነው ። የሚያስተምረው ከሌለው የሚሳደበው አያጣም ። ለማስተማር የማይበቃ ለመበጥበጥ የሚበቃ ነው ። ወታደርን ወታደር የሚያሰኘው ልብሱ ብቻ አይደለም ፣ ስልጠናውም ነው ። ካህንንም ካህን የሚያሰኘው ማስተማሩ ነው ።
አስተማሪ ፣ ገበሬና ወታደር አገር የሚጠብቁ ናቸው ። አስተማሪ ካለ ማወቅ ፣ ገበሬ ከረሀብ ፣ ወታደር ከወራሪ የሚያድኑ ናቸው ። ወላጅ ልጁን በጠዋቱ አምኖ የሚሰጠው ለአስተማሪ ነው ። አስተማሪ ሁለተኛ ወላጅ ፣ የትውልድ ተንከባካቢ ፣ ብርሃን ገላጭ ፣ የቡሩክ እግዚአብሔር ተንታኝ ነው ። አስተማሪ ፊደል ቀርፆ ፊደል የሚያስጠና ፣ ንባብን ከነትርጓሜ ፣ ትርጓሜን ከዜማና ከቅኔ ጋር የሚያሰርጽ ፣ የነፍስ ምጽዋት የሚሰጥ ደግ ነው ። አይሁዳውያን ልጃቸውን ከሰባት ዓመቱ እስከ አሥራ ሁለት ዓመቱ ለረቢው ወይም ለመምህሩ ይሰጡታል ። ፊደልን ከሕጉ ጋር ተምሮ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ሙሉ ሰው ይባላል ። አስተማሪ ሙሉ ሰውን የሚያወጣ ነው ። አሪስቶትል ትምህርት ቤት ደጃፍ ላይ፡- “ልጆቻችሁን አምጧቸው ሰው አድርገን እንመልሳቸዋልን” የሚል ጽሑፍ ይነበብ ነበር ። በኢትዮጵያ ቤተ  ክርስቲያንም ከፊደል እስከ ትርጓሜ ፣ ከዜማ እስከ ቅኔ ትምህርት ይሰጣል ። ዛሬ በገዛ ፊደሏ የሚሰድቧትና የሚጽፉባትን ስናይ ይደንቀናል ። መሳደቢያ ፊደሉንም ያገኙት ከቤተ ክርስቲያን ነው ። ቤተ ክርስቲያን እየጠሏትም እንጀራ ናት ።
ኤጲስ ቆጶስ ለማስተማር የሚበቃ መሆን አለበት ። ሥልጣኑ ያለው ማስተማር ላይ ነውና ። ካላስተማርን ነገ ተከታይ አይኖረንም ። ማስተማር ዘር መዝራት ነው ። ማስተማር የተዘራውን ማሳደግ ነው ። ማስተማር ያደገውን ፍሬ መሰብሰብ ነው ።
ልዑል አምላክ መምህራንን ያብዛልን ።
1ጢሞቴዎስ 39
ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ