ያለ ክፍያ ተአምራት የምታደርግ ፣ የተአምራትህ ታዳሚዎች ችግረኞች እንጂ ጋዜጠኞች ያይደሉ ፣ ከተአምራቱ በኋላም ምስጋናን እንጂ ምንዳን የማትጠይቅ ክርስቶስ ሆይ ሰላም እልሃለሁ ! ሰው ሰውነትን በጠላበት ዓለም ሰው ሁነህ ፣ ለይሉኝታ ሳይሆን ለፍቅር ሰርግ ቤት ተገኝተህ ፣ አለቀ ሲባል “መጥነው አይደቁሱም ወይ ?” ሳትል ፣ በእናትህ በድንግል ማርያም ምልጃ ውኃን የወይን ጠጅ ያደረግህ ጌታ ሰላም እልሃለሁ ። ውኃውን ወይን ጠጅ ለማድረግ ያልለፋህ ፣ ተአምራት ለማድረግ ላቦት ማውጣት ያላስፈለገህ ፣ ታዳሚው ጸጥ ይበል ብለህ መናገር ያላሻህ ፣ አንተና ችግረኞቹ ብቻ በምትተዋወቁበት ምሥጢር ጉድለትን ለመሙላትህ ሰላም እላለሁ ። ያንተ ስጦታ ዜና የለውም ፤ ቸርነትህም ደብቀህ የምታጎርሰው ነው ።
ቅዱሳን ከመታዘብ መጸለይ ይወዳሉና እናትህ ለመነችህ ። አንተም ማልዱ ብለህ አዘሃልና ተለመንሃት ። ዙፋንህን ሳትለቅ በበረት ፣ ምስጋናህ ሳይጓደል በሰርግ ዘፈን መሐል ለመገኘትህ ሰላም እላለሁ !! በሰማይ ሳትታጣ በምድር የተገኘኸው ፣ ሁሉን ቻይነትህን ሥጋዌህ ያልሻረው ፣ ተዋሕዶህ እንደ ቃና ውኃ መለወጥ የሌለው ፤ ምድሩን እንዳልጠላ የምድር ነዋሪ ሆነህ ፣ ሰውነትን እንዳልመረር ሰው ሁነህ መጥተህ የረዳኸኝ ፣ ደስታው ቶሎ ኀዘን ሲሆንብኝ ከጉድ ያወጣኸኝ የቃና ዘገሊላ እድምተኛ ኢየሱስ ሆይ ሰላም እልሃለሁ !!
ያንተ ተአምራት የዕድገት ሕግ የለውም ። ማስተዋልህም ካምና ዘንድሮ አይባልም ። ሁሉን ከፍጹምነትህ ትሰነዝራለህና ሰላም እልሃለሁ !! አንተ የቆሮንቶስ ባሕታዊ ነህ ፣ ብሕትውናንም ትባርካለህ ። አንተ የቃናው እድምተኛ ነህ ፣ ማኅበራዊነትንም ትወድሳለህ ። ሁሉ ገንዘብህ ነው ፣ ሁሉ ግዛትህ ነውና የምትታጣበት ቦታ የለም ፤ ለከሀሊነትህ ሰላም እላለሁ ። እንዳይናገሩት ሐፍረት ዱዳ ፣ እንዳይኮሩ ባዶነት ዕራቁት ላደረጋቸው የአደባባይ ሸማ ሆንካቸው ። በአደባባይ የተራቆተውን ካንተ በቀር የሚያለብሰው ማንም የለምና ሰላም እልሃለሁ !! ሰርጉ ኀዘን ፣ ጅምሩ ፍጻሜ ፣ ማለዳው ሠርክ ለሆነባቸው አንተ ተስፋ ነህ ። ቶሎ የሚያልቀው ወዳጅነት ፣ ቶሎ የሚጠናቀቀው የዓለም ደስታ ልቡን ለሰበረው እባክህ አንተ ተዋሰው ። ነጻነት የሆነው ፍቅር ሸክም ፣ መልስ የሆነው ቸርነት ዕዳ ለሆነበት እባክህ አሳርፈው ። የተጠራው ትውልድ መጥቶ ሳያበቃ ዓለም ድግስዋ እየተጠናቀቀ ነውና ከመጨረሻው የምትጀምረው ሆይ ክንድህን አንሣ ። አሜን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም.