የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለበጎ ነው

“በአንድ ወቅት አንድ መንፈሳዊ አባት ከነበሩበት ቦታ ወደ በረሃ መሰደድ ግድ ሆነባቸው። ከቅዱስ መጽሐፋቸው ሌላ ሦስት ነገሮች ነበሯቸው። እነሱም፦ ቅዱስ መጽሐፉን በጨለማ ወቅት ለማንበብ የሚጠቅማቸው ቀንዲል(ኩራዝ)፣ ጎህ ከመቅደዱ በፊት ከእንቅልፍ የሚቀሰቅሳቸው አንድ አውራ ዶሮ እና ለመጓጓዣነት የሚገለገሉበት አንድ አህያ ነበሩ።
 አንድ ቀን ምሽት ከጉዞ የተነሣ በጣም ስለ ደከሙ እኚህ መንፈሳዊ አባት ወደ አንድ መንደር ቀርበው ማደሪያ ቢጠይቁም መንደርተኛው ፈቃደኛ ባለመሆኑ ማንም አልፈቀደላቸውም። ስለዚህም ከመንደሩ አቅራቢያ አንድ ጉድጓድ ያገኙና በዚያ ውስጥ ገብቶ ለማደር በመወሰን ገብተው አደሩ። እንደ ወትሮው ቅዱስ መጽሐፋቸውን ለማንበብ ቀንዲላቸውን ቢለኩሱትም የነበረው ብርቱ ነፋስ አጠፋባቸው፤ ስለዚህም ለመተኛት ጋደም እንዳሉ ተኩላ መጥቶ አውራ ዶሮዋቸውን፣ አንበሳም አህያቸውን በሉባቸው። የተደራረበ ጉዳት ስለደረሰባቸው ሽማግሌው እርዳታን በመሻት ወደዚያ መንደር ቢመለሱ ዘራፊ ሽፍታዎች የመንደሩን ነዋሪዎች በሙሉ ገድለው ንብረት ዘርፈው ዖና መንደር ሆኖ አገኙት። ሽማግሌው ይህን ሁሉ ባጤኑ ጊዜ እግዚአብሔር ምን ያህል መልካም ነገርን እንዳሰበላቸው አስተዋሉ። በዚያች ምሽት በመንደርተኞቹ በአንዱ ቤት ቢያድሩ ኖሮ የዘራፊዎች ሰለባ ሆነው ሊገደሉ በቻሉ ነበር፤ ቀንዲላቸውንም ነፋስ ባያጠፋው የብርሃኑ ወጋገን እዚህ ጋር ሰው አለ በማለት ለሽፍታዎቹ ያሳብቅ ነበር። አውራ ዶሮአቸውና አህያቸውም ባይበሉ ኖሮ ከሽፍታዎቹ ተደብቀው ማደር ባልቻሉ ነበር።”
እግዚአብሔር ከክፉ ነገሮች ውስጥ መልካም ነገር ማውጣት የሚችል አምላክ ነው። ሰይጣን ለእኛ ለበጎ እንዲሆን የሚያመጣው ምንም ነገር የለም። እግዚአብሔር ግን የሁሉ የበላይ ነውና ክፉውን ወደ በጎ በመለወጥ እኛን በደስታ፣ ጠላትን በሐፍረት ይሞላዋል። አዳምና ሔዋንን በመጣሉ ሰይጣን ፈጽሞ ደስ እንዳይለው እግዚአብሔር በተስፋ ቃል መታው /ዘፍ. 3፡15/። ዛሬ የመጣል ተራ ቢያገኝ ነገ ደግሞ ደም መላሽ በሆነው በክርስቶስ እንደሚወድቅ ነግሮ አሳፈረው። ሰይጣን ፈጽመን ከእግዚአብሔር እንድንቆራረጥ ባመጣው ውድቀት ክርስቶስ ዘመዳችን፣ የዘላለም ውዳችን ሆነ። ሰይጣንን እንደ አዋቂ እንስለዋለን። እርሱ ግን ጨለማና የጨለማ ሠራተኛ ነው። ሰይጣን አዋቂ ቢሆን ኖሮ የክርስቶስ ሞት የእርሱ ሞት መሆኑን አውቆ እንዳይሞት ይንከባከበው ነበር። የክርስቶስን ሞት ባፋጠነ መጠን የእርሱ ሞት ፈጣን እንደሚሆን አላወቀም ነበር።

አንድ ሰው፡- “ጌታ ሆይ ስለማልፍበት የሕይወት ውጣ ውረድ ለምን ቀድመህ አልነገርከኝም?” አለው። እግዚአብሔር ግን፡- “እኔ የምናገረው የማያልፈውን እንጂ የሚያልፈውን አይደለም” ብሎ መለሰለት ይባላል። የትኛውም ብርቱ መከራችን ያልፋል። ማለፍ ስለፈለገ ሳይሆን ማለፍ የተፈጥሮ ሕግ ስለሆነና አሳላፊው ጌታ በዙፋኑ ስላለ ነው። እኛ ጋ የሚቆይበትን ጊዜ የሚወስነው ራሱ መከራችን አይደለም። የጊዜ መቆጣጠሪያው ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው። ብረቱ በማቅለጫው ውስጥ ሲያልፍ እሳቱ በዝቶ እንዳይበትነው፣ አንሶ ለመቀጥቀጥ እንዳያስቸግር የተቆጣጣሪው እጆች ያሉት በመቆጣጠሪያው ማሽን ላይ ነው። መከራው በዝቶ እንዳይገድለን፣ አንሶ መማር ያለብንን ሳንማር እንዳንቀር የሚቆጣጠረው ያ የፈጠረንና የተቸነከረልን የክርስቶስ እጅ ነው። እነዚያ ሩኅሩኅ እጆች መከራችንን እየተቆጣጠሩት ነውና መስጋት የለብንም።
ሁለት ሰዎች በአንድ ጉዳይ አብረው ይጸልያሉ። አንደኛው ጸሎቱ ተመለሰለት፣ አንደኛው ሳይመለስለት ቀረ። በዚህ ጊዜ ጸሎቱ ያልተመለሰለት ምእመን፡- “ጌታ ሆይ ሁለታችንም እኩል ጸለይን ለእርሱ ሰጥተኸው ለእኔ የከለከልከኝ ለምንድነው?” አለው። እግዚአብሔርም ሲመለስ፡- “ለእርሱ ባልሰጠው ይጠፋል፣ ላንተ ከሰጠሁህ ትጠፋለህ” አለው ይባላል። እግዚአብሔር ከራሳችን በላይ እኛን ያውቀናል። ለአንዳችንን በመስጠት፣ አንዳችንን በመከልከል ዕድሜአችንን ያረዝመዋል። መስጠቱም መንሣቱም ሁለቱም ፍቅር ነው።
ብዙ ነገሮች እንደዚህ እንደሆኑ እንጂ ለምን እንደሆኑ አናውቅም። ዘመናት ካለፉ በኋላ ግን ክፉ የሚመስለው ነገር መልካም እንደ ነበረ እንረዳለን። እግዚአብሔር የነገሮችን ዝርዝር አይነግረንም። እርሱ ንጉሥ በመሆኑ ለእኛ ዝርዝር መንገር አይጠበቅበትም፣ ደግሞም ብንሰማው የማንሸከመው ብዙ ነገር አለ። እንኳን መከራን እውነትን ለመሸከምም አቅማችን ውስን ነው /ዮሐ. 16፡12/። ያለፍነው እንዳለፍን የምናውቀው ብቻ አይደለም። ሳናውቀው ያሳለፈን እጅግ ብዙ ነው። አንዳንድ ነገሮች ካለፉ ባመቱ ስንሰማቸው እንኳ አንቀጥቅጠውናል። የምናመሰግነውም እንዳደረገልን ራሱ በሚያውቀው ልክ ነው። ዘመናት ካለፉ በኋላ ብዙ እንዳለፍን ስንረዳ፡- “ጌታ ሆይ ሰልፉን ላንተ፣ ድሉን ለእኔ ሰጠህ” ብለን በዕንባ እናመሰግናለን።
ማደሪያ አጥቶ ዱር ማደር፣ ከነፋስ የተነሣ ማንበቢያው መቅረዝ መጥፋቱ፣ ቀስቃሽ ዶሮና ሠረገላዋ አህያ መበላታቸው ክፉ ነው። በዚህ ውስጥ ግን እግዚአብሔር ነገርን ለበጎ በመለወጥ ሕይወትን ያጣፍጥልናል። ምናልባት ዛሬ ትንንሽ ችግራችን ከትልቅ ችግር የተጋረድንበት ይሆን? እግዚአብሔር ሞትን በሕመም ለውጦልን ይሆን? ከቤቱ እንዳንወጣ ኩነኔን በማጣት ቀይሮልን ይሆን? ለበጎ ነው። በጨለማ የሚጓዝ አንድ ሰው ዝናቡ ያበሰብሰዋል። አንድ እግሩን እልም ወዳለ ገደል ሊሰድ ሲል መብረው ብልጭ ብሎ መለሰው። ወደ ሰማይ አንጋጦ፡- “አይ ጌታዬ አንተ በመዓቱም ትምርበታለህ” ብሎ አመሰገነ። ለበጎ ነው!
እኔ የክርስቶስ ባሪያ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ