የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለእናንተው ነው

“ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል ፤ አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤” ኤፌ. 3፡2-3።

ላም ብታጠባ ትልቁ ጥቅም ለጥጃዋ ነው ። ወታደር ግዳጁ ከራሱ ይልቅ ለአገር የሚጠቅም ነው ። አገልጋይም መስበኩም መኖሩም ጥቅሙ ከግሉ ይልቅ ለምእመናን ነው ። አይገባም እንጂ ምእመናን አገልጋዮችን ከማስፈራራት አገልጋዮች ምእመናንን ቢያስፈራሩ ያስኬድ ነበር ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮም እስር ሳለ ለፊልጵስዩስ ሰዎች፡- “በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና ፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው” ብሎ ነበር ። /ፊልጵ. 1 ፡ 23-24 ።/ ሐዋርያው ዕረፍቱና ዋጋው ያለው የት መሆኑን ያውቃል ። ከድካም ፣ ከእንግልት ፣ ከጤና እክል የተነሣ መሄድን ናፍቋል ። ሞትንም መንገድ አድርጎ “ልሄድ” አለ ። ሞት ሥራውን ላከናወነ የሚናፈቅ እንጂ የሚያነፋርቅ አይደለም ። ከድካም ዓለም ለማረፍ ቅዱሳን ሁሉ ይናፍቃሉ ። እንደ ሙሴ የራሳቸውን ጉድጓድ ቆፍረው “ና” ይሉታል ። ሞት በክርስቲያን ፊት ግርማዊ አይደለም ። ስለ ሞት ሳይሆን ስለ ትንሣኤ የሚወራበት ዘመነ ሐዲስ ነው ። ሐዋርያው ሁለት ነገሮች እኩል ሆነውበት ይጨነቃል ። ከክርስቶስ ጋር በሰማይ መኖርና ከምእመናን ጋር በምድር መኖር ሁለቱ አሳቦች ይወዘውዙታል ። እኛን የሚወዘውዘን ምን ይሆን ? ብለን ብንጠይቅ መልካም ነው ። በምድር ለምእመናን መኖርና በሰማይ ከክርስቶስ ጋር መኖር ሁለቱ ደጋግ አሳቦች የቱን ልምረጥ እያሰኙ ያስጨንቁታል ። ተራ አሳብ ሳይሆን እንቅልፍ እያጣ ይጨነቃል ። ለክርስቲያን ሊያስጨንቀው የሚገባው ከጽድቅና ከኃጢአት የሚል አሳብ ሳይሆን ከጽድቅና ከጽድቅ የቱ ይበልጣል ? ብሎ መጨነቅ አለበት ።

አማኝ በምድር ለሰዎች ይኖራል ፣ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ይኖራል ። መኖር ያለው በሰማይ ነው ፣ በምድር መቆየት ብቻ ነው ። ታዲያ ሐዋርያው የፊልስዩስ ምእመናንን መኖሬ ይጠቅማችኋል ፣ አስፈልጋችኋለሁ ፣ መኖሬ ከእኔ ይልቅ ጥቅሙ ለእናንተ ነው ። እኔ ብኖር ተጨማሪ ስድብና መከራ አለብኝ ። ብሄድ ግን ዕረፍትን አገኛለሁ ፣ በእምነት የማገለግለውን ጌታ በዓይኔ በማየት ናፍቆቴን እወጣለሁ ። ዓይን ነው ዘመዱ እንዲሉ ናፍቆቴ እርሱን አይቶ ወደ ዘላለም እቅፍ መግባት ነው ። አቅፎ በሚገፈትር ዓለም ፣ ምን እንደሚፈልጉ በማያውቁ ሰዎች መካከል ማገልገል ብርቱ ጣር ነው ። ብኖር ከነገጣባዬ ፣ ከነ ቍስሌ ጥቅሙ ለእናንተ ነው ። ሳልሄድ ጠይቁኝ ፣ ሳለሁ ተጠቀሙ እያለ ነው ። ይህ ትዕቢት ሳይሆን እውነት ነው ። ትዕቢትና እውነትን መለየት ያስፈልጋል ። ትዕቢት ውሸትና የፊኛ መነፋት ነው ። ትዕቢት ቤተ ዘመዶቹ ጉራ ፣ ውሸት ፣ ግነት ፣ ራስን ማጽደቅ ፣ ቢጤዎችን ሰብስቦ ራስን ማስመለክ ነው ። ሐዋርያው ከራሱ ይልቅ መኖሩ ለምእመናን ይጠቅማል ። ዛሬ አገልጋዮቻችንን እንደዚህ ባለ ስስት እያየን ይሆን ? ወይስ በጥላቻ ዓይን ፣ ሣንቲም ሊለቅሙ እንደ ተቀመጡ አድርገን እያየናቸው ይሆን ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ።

ሐዋርያው ለኤፌሶን ሰዎችም በጻፈው መልእክት፡- “ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል ፤” ይላል ። ጸጋው ፣ መጋቢነቱ የተሰጠኝ ለእናንተ ነው ይላቸዋል ። በእውነትም መሰበክ እንጂ መስበኩማ ለእነርሱ ነው ። ጦማረ ጽድቁ/የእውነት ደብዳቤው ለእርሱ ሳይሆን ለእነርሱ የሚጠቅም ነው ። የእግዚአብሔር አገልጋዮች እናስፈልጋችኋለን የምንላቸው ሳይሆን የሚያስፈልጉን ናቸው ። አገልጋዮች ስንል የክርስቶስ ሚኒስትሮች ናቸው እያልን ነው ። ጸጋ ፣ ጸጋ ነውና ጠባይና መልክ ታይቶ የሚሰጥ ፣ የመልካምነትም ሽልማት አይደለም ። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ፍቅርና እንክብካቤ የምንረዳው ለአገልጋዮቹ በሰጠው ጸጋ ነው ። አገልጋዮች የምናከብራቸው ስጦታዎቻችን እንጂ ዘግነን የምናልፋቸው ስጦቻችን አይደሉም ።/ ስጥ ፣ የተሰጣ እህል ማለት ነው ። የተሰጣ እህልን እየዘገኑ የሚያልፉ ፣ እግዜር ይስጥልኝ የማይሉ ሌባ መንገደኞች አሉ ። ሌባ ፍየሎችም ስጦ ቃሚ ይባላሉ ።/

ነቢዩ ኤርምያስ መምህር ሁኖ ቢቆም የሚሰማው ተማሪ ግን አላገኘም ። ነቢይ ባለበት ዘመን ተማሪ መጥፋቱ እርግጥ ነው ። ተማሪ ካለ ግን መምህር ይነሣል ። ታዲያ “ደሞ ዛሬ ምን እያለ ይሆን?” እየተባለ የሚታለፍ ሰው የሆነው ነቢይ እንዲህ አለ፡- “እኔም፡- የእግዚአብሔርን ስም አላነሣም ፥ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም ብል ፥ በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ ደከምሁ ፥ መሸከምም አልቻልሁም ።” /ኤር. 20 ፡ 9 ።/

የእግዚአብሔርን ቃል በመናገራቸው መዓት እንዳወሩ ተቆጥሮ “ምነው ዱዳ ባረገኝ” ያሉ በመልካሙ የተጸጸቱ አገልጋዮች ይኖሩ ይሆን ? የደግ አገልጋይ መቃብሩ ተፈልጎ ይቅር በለኝ የሚባልበት ዘመን ይመጣል ። ብቻ ጸጋ ቢሰጥ ፣ መጋቢ ተብሎ ቢሾም ጥቅሙ ለምእመናን ነውና ምእመናን ካህናተ እግዚአብሔርን ማክበር አለባቸው ።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓተ ቅዳሴው ረዘመና “ምነው አረዘማችሁት” ብለው ሊወጡ ሲሉ አቡነ ቴዎፍሎስ፡- “ይሂዱዋ ማን ይቀርበታል ብለው ነው” በማለት ቢናገሩ ንጉሡ መለስ አሉና፡- “ለካ የሚቀርብን ለእኛው ነው” ብለው አምልኮታቸውን ቀጠሉ ። የሚቀርብን ለእኛ ነውና እግዚአብሔርን እየፈራን እንጂ እያስፈራራን መኖር አይገባንም ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ