የትምህርቱ ርዕስ | ለዘመኑ ዘመን የሌለው

“ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ። እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው።” ዮሐ. 14 ፡ 6-7 ።

የዮሐንስ ወንጌል የተጻፈበት ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምነን እንድንድን ነው ። አይሁድ የሰው ልጅ መሆኑን አልካዱም ፣ ለሞት ያበቃው ግን “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” ይላል የሚለው ክስ ነው ። ሁሉም ሃይማኖቶች ክርስቶስ ደግ ሰው እንደሆነ ያምናሉ ። ሃይማኖት የለንም የሚሉ ሰዎችም በምድር ላይ የመልካም ሥነ ምግባር ተጽእኖ እንዳመጣ  ይናገራሉ ። ነገር ግን ክርስትናን ልዩ የሚያደርገው ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር መሆኑን መቀበልና መመስከር ነው ። የዳነው ሰው በሆነው አምላክ ነው ። አምላክ በባሕርዩ አይሞትም ፣ በለበሰው ሥጋ ግን ለእኛ ቤዛ ሁኗል ። ቤዛነት አምላክነት ያሻዋል እንዲሉ ቤዛ የሆነው አምላክ ባይሆን ኖሮ ድኅነትን አናገኝም ነበር ፤ በፍጡር መዳን አይቻልምና ። በርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ።

ማለዳውን ስነሣ ዘመን የሌለውን ባለ ዘመን ፣ ፍለጋ የሌለውን ባለጠጋ ፣ ምክንያት የሌለውን ነዋሪ እያሰብኩ ነበር ። ዘመን የተሰጠን ባለ ዘመን ፣ ዘመን የሚያልቅብን የጊዜ ተቀባዮች ነን ። ዘመናችን እንደ ቀኑ ነው ፣ ቀኑ ንጋትና ምሽት አለው ፤ የእኛም ዘመን ይነጋል ፣ ይመሻል ። ትላንት ንጉሥ የነበሩ ወርደው እስረኛ ሆነው ሊኖሩ ይችላሉ ። እግዚአብሔር ብቻ “ነበር” የሚል ኃላፊ ግስ አይስማማውም ። ህልውናው ከክብሩ ጋር ለዘላለም የሚኖር ነው ። ንጉሥ ፣ ንጉሥ ያልነበረበት ዘመን ነበር ፣ ንጉሥ የማይሆንበትም ጊዜ ይመጣል ። ወኪል ነውና የወከለው ውክልናውን ሲያነሣበት በቅጽበት ይታጣል ። የትላንት ጌታ ፣ የዛሬ ከርታታ ይሆናል ። በቅርቡ ሶሪያን ለ24 ዓመታት ያስተዳደሩት በሽር አል አሳድ ጠዋት ገዥ ከሰዓት ስደተኛ ፣ ጠዋት መላው ሶሪያ የእርሳቸው ፣ ከሰዓት በራሽያ በአንድ ቤት የሚወሰኑ ሆነዋል ። ቀጥሎ የእንቅስቃሴ ማዕቀብ ፣ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መጠራት ይገጥማቸዋል ። እግዚአብሔር ብቻ በግዛቱ ፀሐይ አይጠልቅም ። ፀሐያቸው የሚጠልቅ ነገሥታትን ከመተገን አንዱን አምላክ ማመን በእውነት የተሻለ ነው ። እግዚአብሔር በሰው ይሁንታ አልነገሠምና በሰው ዓመፅ አይሸነፍም ። አምላካችን ንጉሥ ያልነበረበት ዘመን የለም ፣ ወደፊትም አይኖርም ።

ባለጠግነቱ ፍለጋ የለውም ። ሲለምኑት ከየት ያመጣዋል ? ብለው አያዝኑለትም ። ሲሰጥም አያልቅበትም። አንድ ቢሊየነር አንድ ብር ቢሰጥ አይጎዳውም ፣ ግን አንድ ብር ጎድሎበታል ። እግዚአብሔር አምላካችን የዚህ ማለዳና ቀን ጌታ ሀብቱ ፍጹም ነውና አይጎድልበትም ። ሀብቱን ከየት አመጣው ?  ተብሎ ፍለጋው አይጠናም ። ሐዋርያው በዚህ ቢደነቅ፡- “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው ፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው ፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም ።” አለ ። ሮሜ. 11 ፡ 33 ። የምድር ባለጠጎች በየዓመቱ የሀብታቸው መጠን ይዋዥቃል ፣ ተወዳድረው ከፍና ዝቅ ይላሉ ። እግዚአብሔር ግን ለሰውና ለመላእክት የህልውናቸው መሠረት ነውና ከማንም ጋር አይወዳደርም ። የማያበድሩት ባለጠጋ ነው ። ጸጋውን ሳይሰፍር የሚሰጥ ነው ። የሀብታት መዝገብ ነው ። ንብረቱንም ማንም አልቆጠረውም ። እንኳን የእኛ የሆነው እኛም የእርሱ ነን ። ብዙ ባለጠጎች የሀብታቸውን ምንጭ እንዳይጠየቁ ይሰጋሉ ። ስለዚህ ለነገሥታት ሎሌ ሆነው ፣ ጨለማውን ብርሃን እያሉ ይኖራሉ ። ሰውን ፈሪ የሚያደርግ ሁለት ነገር ነው ፤ እነርሱም አለማወቅና ገንዘብ ናቸው ። ሀብታቸውን በዘመድ ባዝማድ ስም የሚያደርጉ ፣ እንደገና ቢክዱኝስ ብለው የሚጨነቁ አሉ ። የሀብታቸው ምንጭ በደኅንነት ሠራተኞች ይጠናል ። በውጪው ዓለም የሰው ልጅ ነጻነት አለው ተብሎ ቢታሰብም በብዙ ሕጎች ተጠፍሮና ፈሪ ሆኖ የሚኖር ነው ። አንድ ትርፍ ገንዘብ በሂሳብ ቍጥሩ የገባ እንደሆነ የትመጡ ይጣራል ። በአንዳንድ አገር የቅርብ ዘመዶች ሳይቀር የሀብቱ ደባቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ይበረበራሉ ። እግዚአብሔር ግን ለሀብቱ ፍለጋ የለውም ።

በእግዚአብሔር ተፈጥረን በእርሱ ሕያዋን ሆነን የምንኖር ነን ። ባሕር በወሰን እንደ ተያዘች እኛም የምንኖርበት ዘመንና ቦታ ተወስኗል ። እግዚአብሔር ለህልውናው በፍጥረቱ አይደገፍም ። በማንም ሞትም አይከሰስም ፣ ምክንያቱም መግደልና ማዳን ሥልጣኑ ነውና ። እግዚአብሔር ለህልውናው የተመረኮዘው ምንም ነገር የለም ። በራሱ ሕይወተ ባሕርይ ነዋሪ ነው ። እኛ ግን ከእርሱ የእስትንፋስ ምጽዋተኞች ነን ። እስትንፋስዋን ቢያቆማት በራሳችን ለመኖር የሰከንድ አቅም የለንም ። ታዲያ ይህ ሁሉ ትዕቢት ምን ይሆን ? አዎ ማለዳውን ዘመን የሌለውን ባለ ዘመን እያሰብኩ ፣ እያንጎራጎርኩ ነበር ።

ለማትታጣው ጌታ ምስጋናና ክብር ይሁን !
ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም