“ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤” ኤፌ. 1፡18-19።
ሐዋርያው የጸለየው አንድ ነገር ነው ። ያ አንድ ነገር ደግሞ ሦስት ነገሮችን ያሳያል ። እርሱም የልባቸው ዓይኖች እንዲበሩ ነው ። ልብም ሁለት ዓይኖች አሉት ወይ ? ቢሉ ሁለት ዓይን ለሚዛን ይረዳል ። ልብ አንዱ ሲጨክን አንዱ የሚራራ ሁለት ዓይኖች አሉት ። ልብ አንዱ ሲያለቅስ አንዱ የሚያስለቅስ ሁለት ዓይኖች አሉት ። ልብ አንዱ ሲያፈቅር አንዱ የሚበቀል ሁለት ዓይኖች አሉት ። ልብ አንዱ ስህተት ሲፈልግ አንዱ ይቅርታ የሚያደርግ ሁለት ዓይኖች አሉት ። ልብ አንዱ ሲሰበር አንደኛው የሚጸና ሁለት ዓይኖች አሉት ። ሙሉ ለሙሉ መልካም ሰው ፣ ሙሉ ለሙሉ ክፉ ሰው የለም ። አንድ ሰው እንደገለጸው፡- በጣም ጥሩ የሚባለው ሰው በውስጡ ሰው ያላያቸው ጥቂት መርዛም እባቦችን ተሸክሞ ይሄዳል ። በጣም ክፉ የተባለው በውስጡ ሌላውን የሚያጠግቡ ጥቂት ፍሬዎች ይዞ ይኖራል ። ከብዙ መልካም ጥቂት ክፋትን ያዩ ሰዎች ፣ ሰው ክፉ ነው ይላሉ ። ከብዙ ክፉ ጥቂቱን መልካም ያዩ ደግሞ ሰው መልካም ነው ይላሉ ። ይህ የሚሆነው ግን የልብ ዓይኖች ሲበሩ ነው ። በዓለም ላይ ብዙ ጨለማዎች ቢኖሩም የልብ ጨለማ ግን አስፈሪ ነው ። ብርሃን ለማግኘት ግድብ ከመገደባችን በፊት ፣ የሰው ልብ እንዲበራ ክፋትን መገደብ አለብን ።
አንዳንድ ጊዜ በመኖሪያ ቤታችን የሳሎኑ መብራት ይጠፋና የጓዳው ይሠራል ። አንዳንድ ሰዎች የላይ ዓይናቸው ጠፍቶ የውስጡ ግን ይበራል ። ሌሎች ደግሞ የሳሎኑ መብራት አለ ፣ የአውቶብስ ቍጥር ከሩቅ ይመነጥራል ፣ ውስጣቸው ግን ክርስቶስን ላለማየት ታውሯል ። የላይ አለማየት ኃጢአት አይደለም ፣ የውስጥ አለማየት ግን ጠፍቶ ማጥፋትን የሚያመጣ ኃጢአት የሆነ ነው ። የላይ ብርሃን በተአምራት ሲመለስ ፣ የውስጥ ብርሃን ግን በትምህርት ይመለሳል ። የልብ ጨለማ ሲጸና ሰው አፈር ላፈር ብቻ ይጫወታል ። ከሩቁ የቅርቡን እያሰበ ፣ ከእውነቱ ለስሜቱ እየታመነ ታሪኩን ያበላሻል ። የልብ ጨለማ ያለባቸው ሰዎች ማሳነስና ማራከስ ትልቁ ተግባራቸው ነው ። ለአገር የሚበቃውን ለማኅበር በማድረግ ማሳነስ ፣ ሌሎች ሊሠሩት ያለውን በተንኮል በመጀመር ማራከስ ይፈጽማሉ ። ሁሉን በእኔና ለእኔ ሲሉ ብዙ ደጎችን ይቀጫሉ ። ሰው የሚፈልገውን እንደ አዝማሪ እያዜሙ በልባቸው ግን ያልካዳቸውን ይክዳሉ ።
በጣም ድንቅ ከሆኑ ዝማሬዎች አንዱ፡-
“ቃልህ ሲነገር ልስማ ፣ ጌታ ሆይ እባክህ ፤
ልቤን ክፈተው ፣ ልቤን ክፈተው ፤
የልድያን ልብ እንደ ከፈትኸው” የሚለው ነው ። ቃለ እግዚአብሔር ለመስማት ተመጥቶ ይህን መዘመር ትልቅ ጥበብ ነው ። መስማትን ማስተዋል ፣ መናገርን መተግበር ካልተከተለው ሁሉም ነገር ከንቱ ነውና ። በቅዳሴአችንም፡- “ሀበነ እግዚኦ አዕይንተ አእምሮ ወትረ ኪያከ ይርአያ ወአዕዛንነሂ ቃለ ዘባሕቲትከ ይስማዓ” እንላለን ።
ትርጉሙ:-
“አቤቱ የዕውቀት ዓይኖችን ስጠን ። ዘወትር አንተን ያዩ ዘንድ ፣ ጆሮቻችንም ያንተን ብቻ ቃል ይሰሙ ዘንድ ።” ማለት ነው ። (ቅዳሴ እግዚእ/ የጌታ ቅዳሴ) ።
የልብ ዓይኖች ሲበሩ ምን ይከሰታል ?
1- የመጥራቱ ተስፋ ታላቅነት ፤
2- በቅዱሳን ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለጠግነት ፤
3- የኃይሉን ታላቅነት መረዳት ይከሰታል ።
የተጠራነው በተስፋ ካርድ ነው ። የተስፋ መጥሪያ ካርድ ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው ። መጀመሪያ ባለጠጋውን እናገኛለን ፣ ከዚያ ጸጋውን እንቀበላለን ። እኔን አስቀድሙ ከዚያ ወዲያ የእኔ የሆነውን ትወርሳላችሁ ይለናል ። እግዚአብሔር ባለመጥፋት እንድናበራ ፣ ባለጸጋውን ይዘን ጸጋውን እንድንቀበል ጠርቶናል ። ከሰማዩ ቤተ መንግሥት ፣ ከንጉሡ አዳራሽ ፣ ከዘላለም ድንኳን የእራት ግብዣ ተጠርተናል ፤ እግዚአብሔር በአንድ ልጁ ሰርግ ላይ ታዳሚ ሳይሆን ሙሽሪት እንድንሆን ወስኗል ። ይህ ትዳርም ከሞትና ከምጽአት የሚጀምር ነውና ለዘላለም የሚጸና ነው ።
በቅዱሳን ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለጸግነት የሚደንቅ ነው ። ተቆጥሮ የማይፈጸም ነውና “ባለጠግነት” አለው ። የስርቆሽ አይደለምና “ክብር” በማለት ጠራው ። ብዙ ርስት የያዙ ሌቦች አሉ ። እግዚአብሔር ሰጥቷቸው ሳይሆን የድሆችን ቀምተው ባለጠጋ የተባሉ ብዙዎች ናቸው ። እነ ውርደት ልብሱ በሌላው ሞት ላይ መኖርን ያቅዳሉ ። ይህ ሁሉ ጥሏቸው የሚሄድ ሀብት ፣ ጥለውት የሚሄዱት ርስት ነው ። ያችን ሦስት ክንድ ከስንዝር የሆነችውን የመቃብር ስፍራም በምጽአት ጊዜም እንለቃታለንና በምድር ላይ ምንም ርስት የለንም ። የእግዚአብሔር ርስት ግን ክብርና ባለጠግነት ያለው ነው ።
ከሁሉ በላይ የኃይሉን ታላቅነት ማወቅ ነው ። ኃይለኞች ነን የሚሉትን ስናይ ተስፋ እንቆርጣለን ። የኃይሉን ታላቅነት ብናይ ግን ሁሉን እያሳለፈ ነዋሪ በሆነው ጌታ እንደገፋለን ። ትላንት ያስፈራን አልፏል ። ላያልፍ የመጣም ማንም የለም ። ኃይል የእግዚአብሔር ነው ብሎ ማረፍ በእውነት መታደል ነው ። ቀድሞ ለኤፌሶን ሰዎች ፣ ዛሬ ይህን መልእክት ለምናነበው ሐዋርያው የጸለየልን የልባችን ዓይኖች እንዲበሩ ነው ።
ሐዋርያው የኤፌሶን ሰዎች ጥሩ ባለሀብት ሁነው አሕዛብን እንዲያስቀኑ ፣ በሥልጣን ማማ ላይ ወጥተው “ኢየሱስ ልጆቹን ያከብራል” እንዲሉ ፣ መልካም ትዳር ይዘው “ንጉሥ ለወደደው እንዲህ ይደረግለታል” ብለው ለራሳቸው እንዲያዜሙ ፣ ብዙ ሺህ ሕዝብ እያጋፉ እግራቸውን እንዲያሳልሙ ፣ የተዋቡ ልጆችን ወልደው ያልወለዱትን “ርግማን አለባችሁ” እንዲሉ ፣ ያማረ ለብሰው የተራቆቱትን እንዲያሳቅቁ ፣ የተገፉበት ዳገት ላይ ሲደርሱ እነርሱም ተረኛ ገፊ እንዲሆኑ ፣ ማንነታቸውን በአደባባይ ሳያፍሩ እንዲገልጡ ፣ የቤተሰባቸውን ታሪክ እየተረኩ “ይህን ሁሉ ጥዬ ነው ፣ ክርስቲያን የሆንሁት” ብለው ምስክርነት እንዲሰጡ አልጸለየላቸውም ።
“አቤቱ የዕውቀት ዓይኖችን ስጠን ፣ ዘወትር አንተን ያዩ ዘንድ ።
ጆሮቻችንም ያንተን ብቻ ቃል ይሰሙ ዘንድ ።”
አሜን ጌታ ሆይ !
የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /26
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 24 ቀን 2014 ዓ.ም.