የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ልባችሁ አይታወክ

 “ልባችሁ አይታወክ ፤ በእግዚአብሔር እመኑ ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ ።”
                                  /ዮሐ. 14፡1 ።/
እጃችን ሲንቀጠቀጥ የያዝነውን ዕቃ እንጥላለን ፣ እግራችን ሲንቀጠቀጥ መሬት መርገጥ ያቅተናል ፣ ዓይናችን ሲርገበገብ ማየት ይሳነናል ፣ አፋችን ሲንቀጠቀጥ መናገር ያቅተናል ። ልባችን ሲታወክም ማሰብ ያቅተናል ። መታወክ የያዝነውን በቁማችን እንድንለቅ ያደርገናል ። የሚወዱንን እንድንገፋ ፣ ዋጋ የከፈልንላቸውን ወዳጆቻችንን እንደ ቀላል እንድንተው ያደርገናል ። መታወክ ሁሉም ነገር ሥፍራውን የለቀቀ አስመስሎ ይስልብናል ፣ ስንታወክ መሬት የተናወጠ ፣ ሰማይ የተቆረሰ ፣ አድማስ የጠበበ ይመስለናል ። ታውከን መስማት የማንፈልገው ድምፅ ታውካችኋል የሚለውን ነው ። ሁሉም ነገር ባለበት ነው ፣ እኛ ግን በመታወክ ባለንበት እምነትና ድፍረት አይደለንምና ሁሉም ነገር ዞር ያለ ይመስለናል ። ልጆቻችን ጥሩ ናቸው ፣ ለምን ፍጹም አልሆኑም ብለን መቀጥቀጥ እንጀምራለን ። የትዳር ጓደኛችን ከሌላው የተሻለ ወይም የተሻለች ናት ። ነገር ግን ለምን ሣራን አልሆነችም እያልን መፍታትን እንፈልጋለን ፤ ለምን አብርሃምን አልሆነም እያልን ገላግለኝ የሚል ጸሎት እንጀምራለን ። መታወክ እኛ እየተጓዝን በመሆኑ ሁሉም ነገር እየሄደ አስመስሎ ያሳየናል ። እኛ ወደፊት ስንበርር የቆመው ነገር ወደ ኋላ እየበረረ ይመስለናል ። የቆመው ነገር እንዳለ ነው ፣ እኛ ስለምንጓዝ ግን የሄደ ይመስለናል ። ስለ ከዱኝ ከዳኋቸው ፣ ስለ ተናገሩኝ መለስኩላቸው የሚያሰኘን መታወክ ነው ። የከዳነውም የተናገርነውም ግን እኛ ነን ። ከመጠን በላይ የትክክለኛነት ስሜት ሲሰማን መታወክ ውስጥ ነን ማለት ነው ። ስንታወክ ንግግር ብቻ ሳይሆን ዝምታም ቃል አውጥቶ ሲናገረን ይሰማናል ። የልባችን ትርታ እንደሚፈለጥ ድንጋይ እንሰማዋለን ፣ ቀጭ ቀጭ የሚለው ሰዓትም ማንም ባይሰማውም እኛ እንደ ጥይት ድምፅ እንሰማዋለን ። ነቅቶ መዋል ነቅቶ ማደር እርሱ መታወክ ነው ። የብዙ ውጫዊ ጦርነቶች መንስኤው ይህ ውስጣዊ ጦርነት ነው ። መታወክ የሰዎችን መልካምነት እንዳናይ ፣ ያደረግንላቸውን እንጂ ያደረጉልንን እንዳናይ ግርዶሽ ይሆንብናል ። እኔ ፣ እኔ የሚል ንግግር መታወክ የሚወልደው ነው ። እግዚአብሔር ያደረገልንን እንዳንቆጥር ፣ በምናመሰግንበት ዘመን እንድናማርር የሚያደርግ በአጠቃላይ የአመል ድሀ የሚያደርገን መታወክ ነው ። ከገንዘብ ድህነት ስንላቀቅ የአመል ድሀ መሆናችን ያሳዝናል ። ሌላው ከሚቀጣን ራሳችንን የቀጣነው ይበዛል ። መታወክ ውስጣዊ ጅራፍ ነው ። የምንፈልገውን አናውቀውምና በመታወክ ውስጥ የምንፈልገውን አናገኘውም ። መታወክ ንግግራችንን ጎምዛዛ ያደርገዋል ፣ አሳብችንን መግለጥ ስለሚያዳግተን በቍጣ ማውራት እንጀምራለን ። ከግድግዳ ጋር ፣ ከእንስሳ ጋር እንደ በለዓም ማውራት እንጀምራለን ። የማይካድ ነገር ለእኛ ብቻ የሚሰማን አሉታዊ ድምፅ አለ ። ማንም አይወድህም ፣ ስለ ሙያህና አገልግሎትህ እንጂ ፈላጊ የለህም የሚል ድምፅ ከሰይጣን ይመጣል ። ለስላሳ ግን የሚያሻክር ድምፅ ነው ። በሰላም ቀን አስበን ስንናገር ፣ በመታወክ ቀን ተናግረን እናስባለን ።

የእኔ ነው ብለን የያዝነው ሲከዳን ፣ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር ተነሥተን ሲያቅተን መታወክ ውስጥ እንገባለን ። ልጆቻችን አቅም ባጡ ዘመን እሺ ይሉንና አቅም ሲያገኙ እምቢ ሲሉን ዓለም ይጨልምብናል ። የእኔ ብቻ ብለን የያዝነው ነገር የሌሎችም መሆኑን ስናውቅ መታወክ ውስጥ እንገባለን ። የተጨበጡ ስጋቶች ሐኪም ቤት ያለው ወዳጃችን ፣ እስር ቤት ቀጠሮ እየጠበቀ ያለው አጋራችን የመታወክ ምክንያታችን ናቸው ። ያልተጨበጠው ስጋት ደግሞ ጤነኛ ወዳጆቻችንን በአሳብ እየገደልን ያን ቀን ምን እሆናለሁ ብለን ስናስብ መታወክ ውስጥ እንገባለን ። አገር ቢበጠበጥ ፣ ረሀብ ቢነሣ ፣ የዘር ፍጅት ቢጀምር የት እሄዳለሁ ? በማለት መታወክ እንጀምራለን ። የሰማናቸው የሐኪም ቤት ውጤቶች የምንገምታቸው የላብራቶሪ ውጤቶች እነዚህ ሁሉ ታውከን ሌላውንም እንድናውክ ያደርጉናል ።
የነገ ኑሮዬ እንዴት ነው ብለን ስናስብ ፣ ያለ ጡረታ ከመሥሪያ ቤታችን መውጣታችን ፣ የራሳችን ቤት አለመሥራታችን እነዚህ ነገሮች የሁከት ማዕበል ሁነው በነፍሳችን ላይ ማጓራት ይጀምራሉ ። እግዚአብሔር የነገረንን ነገር በጆሮአችን ፣ ሰይጣን የሚያንሾካሹክብንን ድምፅ በልባችን ስንሰማ መታወክ ዘመዳችን ይሆናል ። እንቅልፋችን እየታጎለ ከነገ እየተበደርን መኖር እንጀምራለን ። ብቻዬን ነኝ የሚለውን አስደሳች ዜማ ማንጎራጎርና ለራሳችን ማልቀስ ትልቁ የመታወክ ግብዓታችን ነው ። ለምን እንዳመንን ፣ ለምን ቤተ ክርስቲያን እንደምንሄድ አለማወቅ ፣ ብዙ የሃይማኖት ደጆችን መርገጥ ፣ አንዴ ኦርቶዶክስ ሌላ ጊዜ ሌላ ስንሆን ይህ በራሱ መታወክን ይወልዳል ። መታወክ ያንቀዠቅዣል ፣ የሃይማኖት ቅልውጥ ውስጥ ይወስዳል ፣ ሄደንም መርካት ሲያቅተን ሁሉም ጋ ሰው ሰው ሲሸተን እንደገና ያላመንበትን ነገር መኖር ፣ ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል እልህ መታወክ ውስጥ እንገባለን ። መታወክ እየጸና ሲመጣ ድብርት ውስጥ ይከተንና ለምንም የማንደነቅ ፣ ቦምብ ቢፈነዳ የማንደነግጥ ድንዙዝ ሰዎች ያደርገናል ።
ወዴት እንደሚሄድ የማያውቅ ሰው ፣ በነፍሱ አድራሻ ያጣ ወገን መታወኩ ቅጥ የለውም ። የራሱን መንገድ ማስመር የሰለቸው ፣ ሰዎችን ያሳመነበት ዲስኩሩ ራሱን ማሳመን ሲያቅተው መታወክ ይጀምራል ። በእርሱ ውሸት ሰዎች ተኝተው እርሱ ግን ነቅቶ ያድራል ። መንገዱን አለማግኘት ብዙ ዋጋ ያስከፍላል ። መንገዱን ስናገኝ ገንዘብም ፣ ጉልበትም ፣ ጊዜም ፣ ፍርሃትም ይድናል ። እውነቱ የቱ ነው በማለት የሃይማኖት ውዝግብ ውስጥ የገባ ፣ መሐል መንገድ ላይ ቆሞ የዛሬን ለሁለት ሰንጥቀኝ የሚል በርግጥም መታወክ ውስጥ እየዋኘ ነው ። እግዚአብሔር ያላሸከመው ሸክም ረድኤተ መንፈስ ቅዱስ የለውምና ይህ ሰው ይጎብጣል ። ሕይወትና ኑሮ የተምታቱበት ፣ ኑሮን አስቀድሞ ሕይወትን መጎተት የሚፈልግ ፣ ፈረሱና ጋሪው ቦታ ተለዋውጠዋልና መታወኩ አይደንቅም ። መንታ መንገድ ያለ የሚመስለው ፣ ባሻው መንገድ እግዚአብሔርን ለማግኘት ተነሥቶ ከዘላለሙ አሳብ ጋር ይጣላልና ይታወካል ።
የመታወክ መድኃኒቱ ምንድነው ?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- ““ልባችሁ አይታወክ ፤ በእግዚአብሔር እመኑ ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ” አለ ። ጌታችን ልባችሁ አይታወክ ያለው የታወከ ሰው ልብሱ ሽቅርቅር ፣ ጨዋታው ደማቅ ፣ ችግር የለም የሚለው ድምፁ የማያቋርጥ ነው ። መታወኩን ሰው እንዳያውቅበት ቅባት ዘቅዝቆ የሚቀባ ፣ ልብስ አማርጦ የሚለብስ ነው ። ሰዎችም እያዩት እርሱማ ምን አለበት ? ይላሉ ። ከልብስና ከቤት ዘልቆ የሚያይ ጌታ ብቻ ነው ። ስለዚህ ልባችሁ አይታወክ አለ ። መርከብ ማዕበልን የምትሰጋው ወደቡ ላይ አይደለም ፣ በሰማይም ፈተና የለም ። መርከቧ ከማዕበሉ ለመዳን መልሕቋን መጣል ወይም ወደቡ ላይ መድረስ አለባት ። ከመታወክ የምንድነውም በመልሕቁ በእምነት ነው ። እኛን የሚሸከም መልሕቅ ቅድስት ሥላሴን ማመን ብቻ ነው ። አለማመን መታወክን ይወልዳል ። ስለዚህ በመታወካችን ያወክናቸውን ይቅርታ እንጠይቅ ። ኃጢአትም ሰላም ይነሣልና ያሳዘናቸውን በጉልበታችን ሂደን ማሩኝ እንበል ። ሰውን እያሳዘኑ እግዚአብሔርን ማስደሰት አይቻልም ። የታዘነበት ሰው ቢጸልይም ወደ ተዘጋ ሰማይ የሚጸልይ ነው ። መኖሪያችን የዘላለም አምላክ ነው ። እግዚአብሔር ገንዘብም ሥልጣኔም እንደማያኖር ለማሳወቅ ቆርጦ የወጣበት ዘመን ነው ። ሁሉንም ነገር እንድንቆጣጠር ሁነን አልተፈጠርንም ፣ አያስፈልገንምም ። ስለዚህ ነገሮች አመለጡኝ ከሚል ሁከት እንውጣ ። እምነት የራስን ስህተት ፣ የእግዚአብሔርን ተቀባይነት ማመን ነውና ፈጥነን ንስሐ እንግባ ። ባለቤቱ የልብ አውቃ ነውና “ልባችሁ አይታወክ” ይለናል ። እልፎች ከእኛ ጋር ከሚኖሩ እርሱ ከእኛ ጋር ካለ በቂ ነው ። የሰማዩ ፈርሶ የምድሩን ብናንጽ አሁንም እንደ ፈረሰ ነው ።
ጸሎት
ጌታዬ ሆይ በሞትና በሕይወት መካከል ነፍሴን ያፈናትን መታወክ በቃልህ ሥልጣን ዛሬ ድል ንሣልኝ ። በሁሉ ላይ የበላይ መሆኔ ሳይሆን ሁሉን ለማገልገል ዝቅ ማለቴ ሰላም እንደሚሰጠኝ እባክህ ንገረኝ ። አንተ እያለኸኝ ይህን ባጣ ከሚል ድንጋጤ መልሰኝ ። ነፍሴ በእጅህ ናትና መልሰህ ለእኔ አትስጠኝ ። የሰላም ምክንያት እንጂ ለሌሎች የሁከት ምክንያት ከመሆን ጠብቀኝ ። ምንም ነገር ጥያቄ እንዳይሆንብኝ የዘላለም መልሴ አንተ ከእኔ ጋር ሁን ። በተመሰገነው መንግሥትህ ለዘላለሙ አሜን ።
የመስቀሉ ገጽ 3
ሚያዝያ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ያጋሩ