የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ልደታ ለማርያም

ድንግል ሆይ ! ያንቺ መወለድ በእውነት ድንቅ ነው ! በዘር በሩካቤ ፣ በሕግ በሥርዓት ተወለድሽ ። ወላጆችሽ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበርና ከእግዚአብሔር ለምነው አገኙሽ ። የእግዚአብሔር እንድትሆኚ ፣ ለእግዚአብሔር ሊሰጡሽ አንቺን መውለድ ተመኙ ። የእግዚአብሔር እናት እንደምትሆኚ ፣ ፈጣሪን እንደምትወልጂ ያውቁ ይሆን ? እንበለ ዘርዐ ብእሲ እንደምትወልጂ ተገንዝበው ይሆን ?

ከገቦ አዳም ሔዋን ተገኘች ፣ አንቺ ግን ከኢያቄምና ከሐና ተወለድሽ ። ሔዋን አቤልና ቃየን የሚባሉ ደግና ክፉ ልጆች ወለደች ። አንቺ ግን ኃጥአንን በቸርነቱ የሚያጸድቀውን ወለድሽ ። ቤተ መቅደስ ሳለሽ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱሽ ። የፊተኛው መቅደስ ክብር ሲያበቃ ያንቺ ክብር ግን ላያልፍ ይኖራል ። የሚጠሉሽ ሊያጠፉሽ አልቻሉም ። ኑሮሽ ብዙ ስጋት ፣ ስለ ልጅሽ ብዙ ጭንቀት ነበረው ። ያለ ወንድ ዘር ስንጸንሺ ጭንቀት ነበረ ። በልጅሽ ምክንያት የቤተ ልሔም ሕፃናት ሲያልቁ ነፍስሽ ተጠብባ ነበር ። የግብጽን በረሃ ልጅሽን ታቅፈሽ ስታቋርጪ ፣ አገር አልባ ሁነሽ በምድረ አሕዛብ ስትቀመጪ ፣ በልጅሽ ብዙዎች ሲሰናከሉ ፣ ደቀ መዛሙርቱ ሲከዱት ፣ ዓለም ተባብሮ ሲሰቅለው አንቺ በዚህ ሁሉ ውስጥ መስቀልን ተሸክመሽ ታለቅሺ ነበር ። እኛ የአምላክ ተከታይ ሁነን ለምን ጎደለብን እንላለን ። አንቺ ግን የአምላክ እናት ወላዲተ አምላክ ሁነሽ ሁሉን ስታጪ አልተከፋሽም ። አሳብሽ ለአንድ ቀን ምድራዊ አይደለምና ። እኛ ድንግል በሥጋ ብንሆን እንመኛለን ። አንቺ የደናግል መመኪያ ግን ፣ ድንግል በሥጋ ፣ ድንግል በሕሊና ነሽ ። ደናግል ደረቅ ዛፍ ነን እንዳይሉ ድንግል የሆንሽው አንቺ አምላክን ወለድሽ ። ከሐዋርያት ይልቅ የሰበክሽ ፣ ከሰማዕታት ይልቅ መከራ የተቀበልሽ ድንግል ሆይ ፣ ያንቺ ልደት የተባረከች ናት ።

ለእኛ ለምንወድሽ በረከትሽ ይድረሰን !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ