የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሐዲስ ተፈጥሮ

“ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና ፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም ፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም ። እኛ ፍጥረቱ ነንና ፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን ። ኤፌ. 2፡8-10።

ብዙ ልጆች ቤተሰባቸው እንዴት እያኖራቸው እንዳለ አያውቁም ። ብዙ መሪዎች እንዴት አገሩን እየመሩት እንደሆነ ሕዝብ አያውቅላቸውም ። ብዙ አገልጋዮች እንዴት ባለ ትግል እያለፉ መሆኑን ምእመናን አይረዱላቸውም ። ብዙ ወዳጆች ለፍቅር የከፈሉት ዋጋ የሚወዱአቸው ሰዎች አልተገነዘቡላቸውም ። አድሮ የምንገናኘው ፣ ከርሞ እንኳን አደረሰህ የምንባባለው ፣ ዘርተን የምናጭደው ፣ ወልደን የምንስመው ፣ ዘምተን በድል የምንመለሰው ፣ ተናግረን የምናሳምነው ፣ ጽፈን የምናጽናናው በምንና በማን መሆኑን ገና የተገነዘብን አይመስልም ። “ማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ” እንዲሉ በቸርነቱ ቁሞ ቸርነቱን አለማመስገን ትልቅ ዕዳ ነው ። በዚህ መከረኛ ዓለም እንኳ የምኖረው በቸርነቱ ነው ። በተድላው ዓለም ፣ በማያልፈው መንግሥት የምንኖረው ከቸርነቱ ውጭ በምንም ሊሆን አይችልም ። በእጃችን ጨብጠነው ላምልጥ ፣ ላምጥ በሚለው ዓለም ቸርነቱ ዋስ ከሆነን ፤ ንጋቱ ምሽት ፣ ክብሩ ውርደት ፣ ልቀቱ ማነስ በሌለበት ዓለም የምንኖረው በቸርነቱ ነው ። የእስራኤል ልጆች በበረሃ ሲጓዙ ከፊት ደመና ከኋላ ዓምደ ብርሃን ይንከባከባቸው ነበር ። ዓምደ ብርሃኑ በእስራኤል አንጻር ብርሃን ሲሆን በጠላቶቻቸው አንጻር ደግሞ የእሳት ቅጥር ነበረ ። እስራኤል እንዳይፈሩ ብርሃን ሲታያቸው ጠላቶቻቸው ደግሞ እንዲፈሩ እሳት ይታያቸዋል ። እንዲሁም በበረሃው ዓለም ላይ የሚመራን ብሩህ ደመና መንፈስ ቅዱስ ነው ። ክርስቶስ ለእኛ ብርሃን ፣ የሚጠሉን እንዳይቀርቡን የእሳት ቅጥራችን ነው ። ቸርነቱንም ስናስብ በእርሱ አንጻር የመከራው እሳት ሲሆን በእኛ አንጻር ግን የጸጋው ብርሃን የሚታይበት ነው ። ቸርነት ማለት ነጻ ማለት ሳይሆን እኛ በጸጋ እንድንቀበለው ውድ ዋጋ የተከፈለበት ማለት ነው ።

የሰው ጉልበት ሊያመጣው ያልቻለውን ሞተ ክርስቶስ ሲያመጣው ፣ የእኛ ሩጫ ያላስገኘውን የክርስቶስ ሕማም ሲመልሰው “ስለ ቸርነት ስጦታህ ተመስገን ፣ ከእኔ ጉልበት ድካም የመሰለው ሞትህ ፣ ከእኔ ሩጫም ሕመምህ ዋጋ አለው” ከማለት ውጭ ምንም ልንል አንችልም ። የነበረንን መለሰልን ። በእርሱ አግኝተን የነበርነውን በራሳችን አጣን ፣ እንደገና በእርሱ መለሰልን ። በዚህም ገነትና ቀራንዮ ሲናበቡ ይኖራሉ ። በእርሱ ባለጸጎች በራሳችን ፍጹም ድሆች ነን ። መልአክ ቢወድቅ መልአክ አልሆነም ፣ ሰው ቢወድቅ ግን ሰው ሁኖ አዳነን ። በአምላክነቱ ብቻ ሳይሆን በሰውነቱ ፣ በሰውነቱ ብቻ ሳይሆን በአምላክነቱ ፤ በብርታቱ ብቻ ሳይሆን በሕማሙ ፣ በሕማሙ ብቻ ሳይሆን በትንሣኤው ድኅነትን ፈጸመልን ። አለመቻሉን አምኖ በእግዚአብሔር መቻል ሲያምን እምነቱ ሁለት ክፍል አለው ። ፍጹም ኃጢአተኛ ነኝ ፣ ፍጹም መድኃኒት አለኝ የሚል እምነት ይኖረዋል ።

ትምክሕት መዘናጋትን ይፈጥራል ። ችሎታዬ ፣ ጉልበቴ ፣ መክሊቴ የሚል የልብ እብጠት ከጸሎት ያርቃል ። ሰው የሚጸልየው ያጣውን ለማግኘትም ነው ። ትዕቢት ግን አግኝተኸዋል የሚል ድምፅ ስላለው ከጸሎት ያርቃል ። በማንጸልይበት ነገር ደግሞ አጥር የሌለው ቤት ነንና ጠላት በቀላሉ ይደፍረናል ። እግዚአብሔር ስለሚያልፈው ዓለም ፣ የሚያልፍ ትምክሕትን ለራሱ መውረስ ፈለገ ። ምክንያቱም በኃይለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ስንል እርሱ ይዋጋልናል ፣ በኃይለ ከበደ ወአስቻለው ስንል ደግሞ አጋንንት ይዋጉናል ። በእገዚአብሔር መመካት በሙሉ ጥበቃው ሥር መሆን ነው ። ጉልበት ቢመኩበት ይዝላል ፣ ዘመድ ቢመኩበት ይክዳል ፣ ገንዘብ ቢመኩበት ያልቃል ። የሚያልፈውን ትምክሕት ለእግዚአብሔር መስጠት ያለብን ከሆነ ስለማያልፈው የዘላለም ሕይወት መመካት በእግዚአብሔር ብቻ ነው ። ትዕቢተኛ ሰው ዲያብሎስ ላይ ያደረ ነው ። የተሰቀለውን ክርስቶስ ትሕትና ረግጦ መሄድ ዲያብሎስ ላይ ማደር ነው ።

ጸጋ ፣ እምነትና መዳን ተከታታይ ሁነው ተጠቅሰዋል ። በጸጋ ውስጥ የክርስቶስ ሰው መሆን ፣ ለቤዛ ዓለም መሰቀል ይታያል ። በእምነት ውስጥ የሰው ምላሽ ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ፣ በጎ ምግባር ይታተታሉ ። በመዳን ውስጥ አዲሱ ዓለምና ቤተሰብ ያበራሉ ። አዎ ጸጋው ተትረፍርፎ ተቀምጧል ። እምነት ግን እየዘገነ ይወስዳል ። ድኅነትም አማኙን ሊያከብር ካባ ይዞ ቁሟል ። እስከ ዕለተ ምጽአት ክርስቶስ እንደ ታረደ በግ ሁኖ ቁሟል ። ሥጋውና ደሙ ይፈተታል ። ሰዎች አምነውበት እንዲድኑ ጥሪ ያቀርባል ። ከምጽአት በኋላ ግን ፍርድ ረግቶ ዘላለም ይጠባል ።

ጠንካራ ሰዎች አሉ ። ከማንም ምንም የማያልፍባቸው ፣ የራሳቸውን መልቀቅ የሚችሉ ቸርነት የሞላባቸው ደጎችን እናውቃለን ። ምግባራቸው ብቻውን ያለ ክርስቶስ ሊያድናቸው አይችልም ። ይህ ሁሉ ደግነት ያለ እምነት መሠረት የሌለው ቤት ነው ። ስለሚያደርጉት ነገር ብናደንቃቸውም ፣ የተደረገላቸውን ነገር ማወቅ አለባቸው ። በሚያደርጉት ነገር እኛ ስንደሰት እነርሱ ግን ሊደሰቱ የሚችሉት ክርስቶስ ያደረገላቸውን ነገር በማመን ነው ። ልብ አድርጉ ከሀድያንና በእኛ መካከል ያለው ልዩነት የበጎ ምግባር ሳይሆን የቀና ሃይማኖት ጉዳይ ነው ። እምነት በእግዚአብሔር የጌትነቱ ክብር ፣ የበጎነቱ ግብር ማመን ነው ። የጌትነቱ ክብር ሥላሴነቱ ፣ አዳኝነቱ ሲሆን የበጎነቱ ግብር ደግሞ የደግነት ደግነት የሆነው ነፍሱን በቀራንዮ ስለ እኛ መስጠቱ ነው ።

ቆጥረን የማንጨርሰውን ጸጋ በትንሹ እምነታችን እንቀበለው ዘንድ ፈቀደልን ። በእንባችን መጠን ሳይሆን በመመለሳችን ብቻ ይቅርታ አደረገልን ። ከፍልስፍና የሚነሣ የከሀድያን በጎነት አለ ። ብዙ ከሀድያን መናኝ ይመስላሉ ። እኛ የእነርሱን ያህል ዓለምን አልናቅንም ። አረማውያንም በምጽዋት ከእኛ ይበልጣሉ ። የእኛ ምግባር ግን መነሻው እምነት ሊሆን ይገባዋል ። አንድ ማሽን ከሰው በላይ ሲሠራ ይውላል ። ምስጋና ሳይፈልግም ሥራውን ይቀጥላል ። እግዚአብሔር አምላክ ሕይወት ሳያገኙ እንደ ሮቦት የሚሠሩለት ሰዎችን አልፈጠረም ። የፍቅሩና የአዳኝነቱ ምርኮኞችን ለበጎ ምግባር ጠራቸው ። ይህም እንደገና በክርስቶስ ሐዲስ ፍጥረት መሆን ነው ። በመጀመሪያው ተፈጥሮ ከሚታየው አፈርና ከማይታየው መንፈስ ቅዱስ ተወልደን ነበር ። በዳግም ልደትም ከሚታየው ውኃና ከማይታየው መንፈስ ቅዱስ እንወለዳለን ። የፈጠረን እንደ ገና ፈጠረን ። ልብ አድርጉ ከአፈር መፈጠር ከውኃ መፈጠር ነው ። ከሥጋዊ አካላችን የሚበዛው ውኃ ነው ፣ ከምድር አካልም የሚበዛው ውኃ ነው ። አዳም ከውኃ ተፈጠረ ፣ በዳግም ልደትም ከውኃውና ከመንፈሱ ልጅነትን አገኘ ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ያጋሩ