የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሕዝቡ ሁሉ በሰላም ይደርሳል/2

“ይህንም ብታደርግ ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ ፥ መቆም ይቻልሃል ፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል።” ዘጸ. 18፡23 ።

ሙሴ በማግሥቱ ወደ ሥራው ገባ ። ከጥዋት እስከ ማታ ለሕዝቡ ሲፈርድ ዋለ ። ሙሴ በልቡ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ዋጋ እየከፈልኩ ነው ብሎ ያስብ ነበር ። ሕዝቡም ጎበዝ መሪ እያለ ያደንቀው ነበር ። ነገር ግን ፣ ነገር ሲዳኝ እርሱና ሕዝቡ ደክሟቸው ነበር ። ነገር አያልቅምና ወደ ምድረ ርስት የሚያደርጉት ጉዞ ተገቶ ነበር ። መሪው ራሱን ያደንቃል ፣ የምሠራው መልካም ነው ይላል ። ሕዝቡም ዕረፍት እኮ የለውም እያለ ያወድሰዋል ። እግዚአብሔር ያሰበላቸው በረከት ግን ማርፈድ ገጥሞታል ። ሕዝቡ ሁለት ዓይነት ጠላት ገጥሞታል ። አንደኛው የውስጥ ጠላት ነው ፣ እርሱም መሸካከም አለመቻል ነው ፤ ሁለተኛው የጉዞው እንቅፋት የሆኑት በመንገዳቸውና በዙሪያቸው ያሉ ሕዝቦች ናቸው ። የውስጥ ረብሻቸውን በዳኝነት ፣ የውጭውን በጦርነት ለመመከት ሙሴ ተወጥሮ ነበር ። እስራኤል ምን ያጣላቸዋል ? ሰው የሚጣለው በርስት ነው ። እስራኤል ትላንት ካደሩበት ዛሬ የማያድሩ መንገደኞች ናቸው ። በቤት እንዳይቀናኑ ቤታቸው ድንኳን ነው ። በእርሻ እንዳይጣሉ መና እየዘነበ የሚኖሩ ናቸው ። እኮ ታዲያ እስራኤል ዘነፍስ ክርስቲያኖች ምን ያጣላቸዋል ? አገራቸው በሰማይ ነው ። ሞት የሚባል ሠረገላ የሚጠብቁ መንገደኞች ናቸው ። በረከታቸው ክርስቶስ ነው ። “ከእኔ የሆነ ምንም ነገር የለም” እያሉ ሲዘምሩ ሲሰብኩ ውለው “የእኔ ፣ የእኔ” እያሉ መጣላታቸው ተገቢ ነውን ? እስራኤልን በምድረ በዳ ያስቀረው የጠላት ብዛት ሳይሆን የራሳቸው አለማመን ነው ። ከሺህ ጠላት ይልቅ አለማመን ትልቅ ባላጋራ ነው ። ጠላት ቢያዘገይ እንጂ ማስቀረት አይችልም ። ጠላት ግን ባላስቀራቸውም ላዘግያቸው ብሎ መዋጋቱን አይተውም ።

ዮቶር የምድያም ካህን ነው ። የራሱ ሀገረ ስብከት ነበረው ። የተሰጠውን ድርሻ የለየና የጸና ነው ። እርሱ አንድ ሙሴ ላይ አርባ ዓመት ደከመ ፣ ሙሴ ለሚሊየን ሕዝብ ታዳጊ ሆነ ። በየቤቱ አንድ ልጅ የወለዱ ልጃቸው አሥራ ሁለት ትወልዳለች ። የአንድ እናት የአሥራ ሁለት አያት ትሆናለች ። “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ሲባል አንድ ሰው የመላው ዓለም ብርሃን ይሆናል ማለት አይደለም ። የእኛ ዓለም የምንኖርበት አካባቢ ነው ። በሀገረ ስብከታችን ፣ በሥራ ቦታችን ፣ በደብራችን ብርሃን መሆን ይገባናል ። ሁሉን ልያዝ ማለት ግን የተሰጠንን ጸጋ ያስወስዳል ። ቦታን ፣ ዘመንን ማወቅ የመንፈሳዊ ሰው ግዳጅ ነው ። “ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ” ይላል /የሐዋ. 13 ፡ 36/ ። ያለ ዘመናችን ምውት ነን ፣ በዘመናችን ግን መብራት ነን ። በራሳችን ዘመን እንጂ በአባቶችና በልጆቻችን ዘመን ማገልገል አንችልም ። ጊዜ ለእያንዳንዱ ሰው የተሰጠ ግላዊ መክሊት ነው ። ማንቀላፋት አይቀርም ፣ የሰዎችንና የራስን አሳብ አገልግሎ ማንቀላፋት ፣ ጊዜ ለሰጠው ርእስ ጮኹ ማለፍ ነውር ነው ።

የምድያም ካህን ዮቶር ቀድሞም ቢሆን የሙሴ መምህር ነበርና አሁንም የሙሴን ተግባር መልካም አይደለም ብሎ ነቀፈ ። እውነተኛ መምህር ነበርና ፊት አይቶ ፣ ጉቦ በልቶ የማያደላ ነበር ። ዛሬ አባቶችን የሚመክሩ መምህራኖች ፣ መሪዎችን መንገድ የሚያሳዩ የቀድሞ አስተማሪዎች ይገኙ ይሆን ? ቡራኬውንም ቼኩንም ሲይዙ ፣ አገሩንም አጥቢያውንም ካልጨበጥሁ ሲሉ የቀድሞ መምህራን በጥብዓት “ይህ ማባከን ነው” ሊሉ ይገባል ። “የድሀ ጉልበት በጎመን ዘር ያልቃል” እንዲሉ ሁሉን ካልከወንሁ ማለትም ጉልበት ጨራሽ ነው ። ዮቶር ኢትዮጵያዊን ስናስብ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ሥርዓተ አምልኮትንና ሥርዓተ መንግሥትን የሚያስተምሩ ነበሩ ። ይህ ታሪክ ያለው ከዛሬ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ዓመት በፊት ነው ። ከ3600 ዓመታት በኋላ ግን የት ነው ያለነው ? ብለን መጠየቅ ያስፈልገናል ።

ሙሴ ካህን ነበረ ፣ ፈራጅ ነበረ ፣ አስተማሪ ነበረ ። ይህን ሁሉ ጠቅልሎ መያዙ ታታሪ አላሰኘውም ። ትጋት የሚመስሉ መክነፎች ፣ ትዕግሥት የሚመስሉ መስነፎች አሉ ። መልካም አይደለም ተባለለት ። በዚሁ ከቀጠለ እርሱም ደክሞት ያለ ጊዜው ይሞታል ። መኖር እያለ መሞት ጽድቅ አይደለም ። ሕዝቡም ዝሎና ደክሞ በምድረ በዳ ይቀራል ። የእግዚአብሔርም አሳብ ሳይፈጸም ይቀራል ። ሙሴ እግዚአብሔርን ያገለገለ እየመሰለው የእግዚአብሔርን ሥራ እያጓተተ ነበር ። አባ ጠቅል መሆኑ መልካም አልነበረም ። ክፉ ስለነበረ ሳይሆን ስሱ ስለነበረ ፣ እንዳይበላሽ ስለሚሰጋም ነው ። የሚደንቀው ይህን ታሪክ የጻፈው ራሱ ሙሴ ነው ። ሙሴ ትሑት ነዋ ! የዛሬ ሰባኪዎችና መሪዎች ብንሆን ጡት አልጠባሁም ፣ መምህር አላስተማረኝም ብለን ስለ ራሳችን እንጽፍ ነበር ። ወንበሩን ስንይዘው አማልክትነት ይሰማናልና ። ሙሴ ብቻውን ሊያደርገው የማይቻለውን ነገር ብቻውን ጀመረ ። ጅማሬው ግን ፍጻሜ ያለው አልነበረም ። መሪ ለራሱም ጊዜ ያስፈልገዋል ። የቤተሰብ ግዴታም አለበት ። መሪ ለራሱ ጊዜ ከሌለው ትርፍና ኪሣራውን ማስላት አይችልም ። ለቤተሰቡ ጊዜ ከሌለው በፍቅር አይታደስም ።

ይቀጥላል

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ