የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሕዝቡ ሁሉ በሰላም ይደርሳል/3

“ይህንም ብታደርግ ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ ፥ መቆም ይቻልሃል ፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል።” ዘጸ. 18፡23 ።

“የሙሴም አማት በሕዝቡ ያደረገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፡- ይህ በሕዝቡ የምታደርገው ምንድር ነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በዙሪያህ ቆመው ሳሉ አንተ ብቻህን ስለ ምን ተቀምጠሃል? አለው ።” ከዚህ ንግግር ውስጥ የምናወጣቸው ቁም ነገሮች አሉ ። የመጀመሪያው ልጅና ተማሪ ፣ ለወላጅና ለመምህራቸው ሁልጊዜም ልጅና ተማሪ ናቸው ። ልጅ ንጉሥ ሊሆን ይችላል ፣ ልጅነት እንደ ቢሮ ሥራ ዕድገት የሚያሳይ ሳይሆን ቋሚ ፍቅር ነው ። ተማሪም ያስተማሪው የሁልጊዜ ልጅ ነው ። ደቀ መዝሙር ምንም ልቆ ቢማር መምህሩ ዘንድ ግን ተማሪ ነው ። ዮቶር የምድያም ምድር ፈራጅ ነው ። ሙሴ ግን የታላቅ ሕዝብ መሪ ነው ። ዮቶር ግን አሁንም እንደ ተማሪነቱ ሊያስተምረው ሊመክረው ተነሣ ። ሙሴን ልዩ የሚያደርገው በትሕትና ሰምቶ መፈጸሙ ነው ። በትሕትና ሰምተው በትዕቢት የሚለግሙ አሉ ። እሺ ብለው የሚያባርሩ አሉ ። ከፊት ለፊት መልአካዊ መልስ ሰጥተው በጀርባ ሰይጣናዊ ተግባር የሚፈጽሙ አያሌ ናቸው ። ሙሴ ግን ትሑት ነበርና ሁሉም የሕይወት ቁመና ይታየኛል ብሎ አያስብም ነበር ። በትሕትና ተማረ ፣ በፍቅር ሥራውን አከፋፈለ ። መሪ የሁልጊዜ ተማሪ ከሆነ አስደናቂ ተግባር ይፈጽማል ። ጨርሼዋለሁ የሚባል እውቀት በዓለም ላይ የለም ።

የእስራኤል ቋሚው ጉዳይ መካሰስ ፣ አላሳልፍ ያለው ጠላት ሳይሆን ተስፋይቷ አገር ናት ። ስለሚያልፈው ሳይሆን ስለጸናው ፣ ስለ ሥጋዊነትና ሰይጣናዊ ግብሮች ሳይሆን ስለ መለኮታዊ አሳብ ማሰብ ተገቢ ነው ። የእኛም ተስፋችን ሀገረ ሕይወት ፣ ርስተ መንግሥተ ሰማያት ናት ። ቋሚውን ስናስብ ጊዜያዊውን ጥል ክርክር እንዲሁም ጠላት እንረሳዋለን ።

ዮቶር ከተናገረው ውስጥ ሁለተኛው ቁምነገር ሙሴ ለሕዝቡ ያደረገለት የሚመስለውን ተግባር ካህኑ ግን በሕዝቡ የምታደርገው ምንድነው ? አለው ። ጽድቅ የመሰለውን ተግባር በደል ነው አለው ። መሪው ራሱን ጎድቶ ሕዝብንም ከጎዳ ምንም ጥቅም የለውም ። ለታሪኩ ተጨንቆ የዛሬውን ትውልድ ከረሳ አስፈሪ ነው ። አንዳንድ ጊዜ ለሕዝቡ ያደረግንለት የሚመስለን ፣ ነገር ግን ያደረግንበት ነገር ይኖራል ። ለልጆቻችን ያደረግንላቸው የሚመስለን ያደረግንባቸው ነገር ሊኖር ይችላል ። ድርሻቸውን ሳያውቁ እንደ በሽተኛ ሁሉ እየተደረገላቸው ያደጉ ልጆች ፣ አፈር አይንካችሁ የተባሉት ምስኪኖች ፣ እንደ ጌጥ ዕቃ ተወልውለው የሚኖሩ ሚስቶች እየበደልናቸው እንጂ እየጠቀምናቸው አይደለም ። ሁሉም ድርሻ ሊሰጠው በዚያ መሠረት ሊመሰገንና ሊወቀስ ይገባዋል ።

ሕዝቡም ቆሞ ውሏል ፣ ሙሴም ተቀምጦ ውሏል ። ይህ ድካም ነበር ። ሙሴም በቅርቡ እግሮቹ መንቀሳቀስ የማይችሉ ሰው ይሆናል ። ሕዝቡም በመቆም ብዛት ፣ ዳኝነት ዘገየብኝ በማለት ምሬት ውስጥ ይገባል ። በፈርዖን ግዛት ቀኑን በሙሉ ቆሞ ይሠራ የነበረው ፣ አሁን ደግሞ ቀኑን በሙሉ ዕረፍት አጥቶ ይውላል ። የዘገየ ፍርድም የቅጣት ያህል ይሆንበታል ።

አባቶችና መሪዎች ድርሻን ማከፋፈል የሚፈሩት ትዕቢተኛ ስለሆኑ ላይሆን ይችላል ። ሙሴ እጅግ ትሑት ፣ በምድር ከሚኖሩ ሰዎች ይልቅ የዋህ ነበር ። ለመሪነትም ያበቃው ነገር ለሕዝቡ ቁጭት ያለው መሆኑ ነው ። ደግሞም ትሑትና የአገልጋይነት ስሜት መላበሱ ነው ። እውቀቱ ከኀዘኔታ ጋር የተዋቀረ የዋህ ሰው ነበር ። ሙሴም ሆነ ሌሎች መሪዎች ሁሉን ነገር ራሳቸው ይዘው የሚጨነቁት በተለያየ ምክንያት ነው ። የመጀመሪያው ማከፋፈል እንደሚቻል በመርሳት ነው ። እናት ልጇን በወለደች ሰሞን ለሰው መስጠት ትፈራለች ። የእርስዋ እናት እንኳ ልጁን ስትይዝ “እማዬ ቀስ ብለሽ” ትላለች ። “አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ” እንዲሉ አዲስ ሲኮን አለማወቅና ስስት ይይዛል ። ድርሻን ለሌሎች ማከፋፈል አለመፈለግ እጅግ ባለሙያነት የሚወልደውም ነው ። ባለሙያ ሰዎች ሌላው የሠራው ስለማይጥማቸው ሁሉንም ራሴ ካልሠራሁት ይላሉ ። ሌሎች እንዲሠሩ ስንፈልግ እንዲሳሳቱ መፍቀድ አለብን ። የኪሣራ በጀት የሌለው ሰው ሥራን ማከፋፈል አይችልም ።

ድርሻን ለሌሎች ያለ መስጠት ችግር አንዳንድ ጊዜ ትዕቢት ሊሆን ይችላል ። ፈላጭ ቆራጭነት ስሜት ውስጥ የገባ ሰው ሁሉን ካልወጠወጥሁ ይላል ። ሁለት ድስት የጣደች አንዱ እንደሚያርባት ፣ ያረረውን ስታላቅቅ ደኅናው እንደሚያርባት የታወቀ ነው ። ስለዚህ ለሌሎች እውቀትን ማካፈል ፣ የምንሠራውን ማሳየት ፣ እኛ ቆመን ማለማመድ ፣ ሲሳሳቱ ማድነቅና በርቱ ማለት ይገባናል ። በመጨረሻ ጥቅሙ ለእኛው ነውና ። “አህያ በወለደች ታርፋለች” እንዲሉ ። የተወለደውም ክህነት በክብሩ ፣ ንግሥና በአገሩ ይጽናልን ይላል ። ካህን በመንበሩ ፣ ንጉሥ በዙፋኑ ሲኖር ሰላም ይሆናል ።

ይቀጥላል

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ