የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሕዝቡ ሁሉ በሰላም ይደርሳል

“ይህንም ብታደርግ ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ ፥ መቆም ይቻልሃል ፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል።” ዘጸ. 18፡23 ።

ሙሴ ኢትዮጵያዊውን ካህን ፣ ዮቶርን ዳግም ሲገናኝ እንደ ቀድሞ ሌጣና በግ ጠባቂ ሁኖ ሳይሆን ሚሊየን ሕዝብ እየመራ ነበር ። ሙሴ ትልቅ የነበረ ፣ ወደ ታች የወረደ ፣ አሁን ደግሞ የእግዚአብሔር ክብር ያከበረው ሰው ነበር ። ከፍታና ዝቅታን ያላየ ሊመራ ይቸገራል ። ስደተኛ ንጉሥ ፣ ንጉሥም ስደተኛ ይሆናል ። የዓለም ታሪክ የምንለው ይኸው ነው ። ሙሴ ከፈርዖን ፊት በተሰደደ ጊዜ እግዚአብሔር መጠጊያ የሰጠው ካህን በነበረው በዮቶር ቤት ነው ። ዮቶር በዚያ ምድረ በዳ ላይ የሚኖረው ለተራ ነገር ሳይሆን ሕዝብን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ለመምራት ነበር ። ኢትዮጵያውያውን በሕገ ልቡናም እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ፣ ከራሳቸው አልፎ ሩቅ ያለውን ሕዝብ ለማስተማር የሚተጉ ነበሩ ። ሕገ ኦሪትን የተቀበለው ሙሴ በሕገ ልቡና ከዮቶር ጋር ያመልክ ነበር ። ዮቶር ሙሴ ታላቅ መሪ ሁኖ ሲመጣ አልተደነቀም ። ምክንያቱም እግዚአብሔር በእርሱ የሚሠራውን ያውቅ ነበርና ። ምንም እንኳ ዮቶር ለሙሴ አማት ቢሆንም አንዱን አምላክ በማምለክ ግን ተስማምተው ነበር ። ከሥጋ ዝምድና የመንፈስ ዝምድና ይበልጣልና ። እግዚአብሔር ከፈርዖን ቤት ይልቅ ሙሴን በምድረ በዳ ላይ አስተማረው ። ምድረ በዳ የእግዚአብሔር ትምህርት ቤት ነው ። አርባ ዓመት በምድረ በዳ የተማረው ሙሴ አርባ ዓመት ሕዝቡን በምድረ በዳ መራ ። እግዚአብሔር ለሙሴ በልጅነት ዘመኑ እናቱን መምህር አደረገለት ። ከቤተ መንግሥት በተሰደደ ጊዜ ደግሞ ዮቶርን ካህን አደረገለት ።

ይህ ሙሴ ከዮቶር ቤት ከበግ ጥበቃ ላይ የነጻነት መሪ እንዲሆን አምላካዊ ጥሪ ደረሰው ። ሙሴ ዓለምን ንቆ ፣ አልጋ ወራሽነትን ተጸይፎ ፣ እግዚአብሔር ከሌለበት ቤተ መንግሥት እግዚአብሔር ያለበትን ምድረ በዳ መርጦ የመነነ ሰው ነበር ። አርባ ዓመት በቤተ መንግሥት ፣ አርባ ዓመት በስደት ፣ አርባ ዓመት በመሪነት የቆየ ሲሆን ቤተ መንግሥት ያልነበረው ፣ በጉዞ ላይ የመራ ፣ አርባ ዓመትም የተጓዘ ብቸኛው መሪ ነው ። ሙሴ ሕዝቡን በታላቅ ረድኤት እየመራ ከግብጽ ምድር ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ በደረሰ ጊዜ አማቱ ዮቶር ሙሴን ለማግኘት መጣ ። ለእስራኤል ነጻነት ለመጠየቅ ወደ ፈርዖን በሄደ ጊዜ ሚስቱንና ልጆቹን ወደ ዮቶር መልሶ ነበርና ዮቶርም ሊያስረክበው ተዘጋጀ ። ሰማዕትነት አማራጭ ከጠፋ የሚገባበት ነው ፣ ሁሉ ከሚሞትም ሌላውን ማትረፍ ጥበብ ነው ። ሲፓራ የተባለችው የሙሴ ሚስት ለዮቶር የአካሉ ክፋይ ፣ ለሙሴ ግን አካሉ ነበረችና አባትዋ ሊመልሳት ተዘጋጀ ። ትዳር አካልነት እንጂ ሽርክና አይደለም ።

ከሙሴ ጋር በተገናኙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ሥራ አወሩ ። ጊዜን ጣዕም ያለው የሚያደርገው ነገረ እግዚአብሔር ሲወራበት ነው ። የዓለም ነገር ያታክታል ፣ የሰው ነገር ልቡናን ያሻክራል ፣ የኃጢአት ነገር ክብርን ይነካል ። ነገረ ክርስቶስ ግን ጣዕም ይሰጣል ። ዮቶርና ሙሴ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ ። የሚቃጠል መሥዋዕት በሕግ የሚደነገገው ገና ቢሆንም በሕገ ልቡና ግን ነበረ ። መሥዋዕቱ የሚናገረው “ሁለንተናችን ላንተ ለአምላካችን ይሁን” ብሎ ነው ። የሚቃጠል መሥዋዕት ከመሥዋዕቶች ተረፍ/ትራፊ የለውም ። ራሱን ለሰጠን ክርስቶስ ራሳችንን/ሁለንተናችንን መስጠት ይገባናል ። ሙሴና ዮቶር ነገረ እግዚአብሔርን አወሩ ። መሥዋዕትን አሳረጉ ። ነገረ እግዚአብሔር ወይም ቲዎሎጂ በአምልኮት ካልታሰረ እንደ ተቆላ ገብስ የማያፈራ ነው ። አምልኮት የሌለበት ትምህርተ እግዚአብሔር እንደ አጠቃላይ ግንዛቤ የሚሆን ፣ ብዙዎችን በቤተ ክእግዚአብሔር የሚኖሩ ከሀድያን የሚያደርግ ነው ። የሚገርመው እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን ባይፈሩም የሚበሉት እንጀራ ግን እግአብሔርን የሚፈራ ሕዝብ የሰጠውን ነው ።
ይቀጥላል

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ