የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሕግ የተሠራው

“ይኸውም፥ ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዓመፀኞችና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኵሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮችና ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለውሸተኞችም በውሸትም ለሚምሉ፥ የቡሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደ ተሰጠኝ ወንጌል የሆነውን ደኅና ትምህርት ለሚቃወም ለሌላ ነገር ሁሉ ሕግ እንደ ተሠራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሠራ ሲያውቅ ነው ።” 1ጢሞ. 1፡9-11
ሕግ የአታድርግ መመሪያ ነው ብለናል ። ሕጉ ስህተትን ሲያርቅ ፣ ትእዛዙ ደግሞ በጎ ሥራን ያበረታታል ። አትግደል ሕግ ነው ። ስጡ ይሰጣችኋል ግን ትእዛዝ ነው ። ሕግ ክልከላ በመሆኑ ጻድቃንን የሚመለከት አይደለም ። ጻድቃን ከክፉ ርቀው ፣ በበጎ ሥራ ጸንተው ፣ በትሩፋትም አጊጠው ይታያሉና ከሕጉ ርቀዋል ። የታዘዙትን ብቻ ሳይሆን ከታዘዙት በላይ ለመኖር ሽተዋል ። ሕጉ ለኃጢአተኞች ማስጠንቀቂያ እንዲሆን ተሰጥቷል ። ሐዋርያው የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ የሚወዱትን ፣ ከወንጌል ኦሪትን የመረጡትን እየመከረ ነው ። ሕጋውያን ባለመግደል የሚጽናኑ ናቸው ። ሌላውን በማዳን ግን የበረቱ አይደሉም ።

ሐዋርያው ሕጉ እነማንን አድራሻ እንዳደረገ ሲናገር፡- “ለበደለኞችና ለማይታዘዙ” ይላል ። በደለኞች ተደጋጋሚ ስህተት የሚፈጽሙ ናቸው ። ስህተት ሲደጋገም ልብን የማደንደንና ጽድቅ የመምሰል ጠባይ አለው ። ሰዎች የለመዱትን ነገር ክፉ ለማለት ይቸገራሉ ። የማይታዘዙ በጎ የማይሠሩ ማለት ነው ። እነዚህ ታካቾች ፣ የክርስቶስን መልክ ከመያዝ በጨዋነት ብቻ ለመኖር የሚፈልጉ ናቸው ። ወደ ማንም አልቀርብም ፣ የማንም ድጋፍም አያስፈልገኝም የሚሉ የማይታዘዙ ናቸው ። በደለኞች ክፉ የሚሠሩ ፣ የማይታዘዙ ደግሞ ደግ የማይሠሩ ናቸው ። ክፉ የመሥራትን ያህል መልካም አለመሥራትም ኃጢአት ነው ። የመጨረሻው ቀን ጥያቄ ፣ ብራብ አብልታችሁኛል ? የሚለው አንቀጽ ክፉ ስለ መሥራት ሳይሆን በጎ ስለ አለማድረግ ነው ።
ሐዋርያው ሕጉ የሚናገረው ወይም የተሠራው፡- “ለዓመፀኞችና ለኃጢአተኞች” ነው ይላል ። ዓመፅ አልገዛም የሚል እንቢታ ነው ። ኃጢአትም ለእግዚአብሔርና ለመንግሥቱ አልገዛም የሚል እንቢታ ነው ። ኃጢአትም መንገድ መሳት የሚል ትርጉም ያለው ነው ። ኃጢአት አክሳሪ በመሆኑ ማጣት ብለን ልንተረጕመው እንችላለን ። አዳምና ሔዋንን ጸጋ አሳጣቸው ፣ ቃየንን ዕረፍት አሳጣው ። ኃጢአት በውስጡ ምንም ትርፍ የለውም ። ሕጉ የተሠራው ኃጢአተኞች ራሳቸው የሚያዩበት መስተዋት እንዲሆን ነው ። መስተዋት ግን ቆሻሻን ያሳያል እንጂ አያነጻም ።
“ቅድስና ለሌላቸውና ለርኩሳን” ይላል ። ቅድስና ለእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው ። እስራኤል ከግብጽ ሲወጡ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ሁነዋል ። ቅድስና ከዓለም መውጣት ፣ ከዲያብሎስ ባርነት መላቀቅ ፣ እግዚአብሔርን በምድረ በዳው ዓለም መከተል ፣ በእረኝነት ሥር ማደር ነው ። ቅድስና ሁሉንም የሕይወት ክፍል የሚመለከት በመሆኑ አለባበስም ፣ የፀጉር አቆራረጥም ቅድስና ነው ። “ርኩሳን”የረከሱ ፣ የተከለከለ ነገር የነኩ ፣ ቆሻሻ ነክተው የቆሸሹ ማለት ነው ። ሰው ከኃጢአት ጋር አልተፈጠረም ። ቆሻሻ ነክቶ ግን የቆሸሸ ነው ። ኃጢአት የባሕርያችን ቢሆን ኑሮ መንጻት አንችልም ነበር ። ኃጢአት ግን ከጊዜ በኋላ ነጩን ልብሳችንን የነካ ጭቃ ነው ። ስለዚህ መቀደስ አልችልም አይባልም ። ላልተፈጠርንበት ነገር እየኖርን ለተፈጠርንበት ነገር አቅም የለኝም ማለት መዋሸት ነው ። ብዙ ታዛቢዎች ክርስቲያኖችን ሲወቅሱ በጎ ለመሥራት ደካማ ነን የሚሉ ኃጢአት ለመሥራት ግን አቅም የማያጡ ናቸው በማለት ነው ።
“አባትና እናትን ለሚገድሉ” ይላል ። ከአባትና ከእናታችን ሕይወት ተካፍለናል ። ሕይወት ለሰጡ ሞት መስጠት ከባድ ነው ። ኃጢአት ግን ወርቅ ላበደረ ጠጠር ፣ እህል ላበደረ አፈር የሚሰፍር ነው ። አባትና እናትን መግደል ብዙ ዓይነት ነው ። የወለዱትን የማይረዳ ፣ የማያከብር ፣ የማይጎበኝ ፣ የማያጽናና ፣ የማይጦር እርሱ ገዳይ ነው ። የአባትና የእናት ርግማን በልጅ የምንቀበለው ነውና ጠንቃቃ መሆን ይገባል ። አባትና እናትን የምንረዳው እንደ እኛ ስለሚያውቁ ፣ የእኛን ሃይማኖት ስለሚከተሉ አይደለም ። መርዳት መስፈርት የለውም ።
“ለነፍሰ ገዳዮችና ለሴሰኞች” ይላል ። ሕይወት መገኛዋ እግዚአብሔር ነውና የሰውን ሕይወት ማጥፋት እግዚአብሔርን ለማጥፋት መሞከር ነው ። በሕይወት ላይ ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር ነውና በሰው ሕይወት ላይ መወሰን የእግዚአብሔርን ሥልጣን መጋፋት ነው ። አንድ ሰውን ስንገድል ቤተሰቡን መግደልም ነው ። ሰውን በግፍ ከሥራ ማባረር ፣ ማስራብና መዝረፍ እርሱም መግደል ነው ። እግዚአብሔር ድንጋይን የፈጠረው የእኛን ቤት እንድንሠራበት እንጂ የእግዚአብሔር ቤት የሆነውን ሰውን እንድናፈርስበት አይደለም ። ቤት መሥሪያው ቤት ማፍረሻ ሁኗልና ወዮልን ።
ሴሰኞች የተባሉ ዝሙታቸው ማብቂያ የሌለው ሰዎች ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ኃጢአትን ጠግበው ለመተው ያስባሉ ፤ ኃጢአት ግን ወደው ካልተዉት አይጠገብም ። ሴሰኝነት ሲበረታ በሽታና የአእምሮ ብክነት ይበዛል ። አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናትም ይበረክታሉ ። ሰውን የሚያዋርደው ዝሙትና አፉ ነው ።
“ከወንድ ጋርም ለሚተኙ” ይላል ። እነዚህ ሰዶማውያን ናቸው ። ዝሙት ወደ ሴሰኝነት ያድጋል ፣ ሴሰኝነትም ወደ ሰዶማዊነት ያድጋል ። ከኃጢአት እርካታ የሚፈልጉ ሰዎች ሙከራቸው ተፈጥሮአቸውንና ጤናቸውን ፍጹም ወደሚጎዳ ኃጢአት ያደርሳቸዋል ። ሰዶማዊነት የተቀጣው በሎጥ ዘመን ወይም በሕገ ልቡና ዘመን ነው ። ይህ የሚያሳየን ሰዶማዊነት ከኅሊና ጋር እንኳ ግጭት እንዳለው ነው ።
“በሰዎችም ለሚነግዱ” ይላል ። በዛሬው ዘመን የሰው ንግድ በዝቷል ። በዚህ ምክንያት የሰውን ክብር ዝቅ ያደረጉ ወንጀለኞች በዝተዋል ። ብዙ ድሆች ፣ ሴቶችና ሕፃናት በዚህ ጉዳት ውስጥ ያልፋሉ ።
“ለውሸተኞችም” ይላል ። ውሸት ሱስ ነው ። ውሸት ሰዎች ለማምለጥ የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው ። ውሸት የንስሐ ጠላት ነው ። ውሸት ነገ ላይ የሚጠብቀን ቀጪ ነው ። በውሸትም ለሚምሉ” ይላል ። መሐላ የተፈቀደው ለቃል ኪዳን ነው ። ለእውነትም መሐላ ተከልክሏልና በውሸት መማል ፍጹም አይገባም ። በውሸት መማል የእግዚአብሔርን ቅዱስ ስም ለኃጢአታችን ካባ ማድረግ ወይም ተባባሪ ማድረግ ነው ።
“የቡሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደ ተሰጠኝ ወንጌል የሆነውን ደኅና ትምህርት ለሚቃወም ለሌላ ነገር ሁሉ ሕግ እንደ ተሠራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሠራ ሲያውቅ ነው” ይላል ። ትልቁ ኃጢአት ወንጌልን መቃወም ነው ። ሰው እውነተኛውን ወንጌል ሲቃወም ወደ ልዩ ወንጌል ያዘነብላል ። ወንጌል፡-
·        ቡሩክ እግዚአብሔርን የምናይበት መስተዋት ፣
·        ለሐዋርያትና ለአባቶች የተሰጠ መለኮታዊ አደራ ፣
·        ለፍጥረት ሁሉ የሚሆን የምሥራች ፣
·        ደህና ትምህርት ወይም ጤናማ ምግብ ነው ።
ክብር ምስጋና ላንተ ይሁን ።
1ጢሞቴዎስ /13/
ኅዳር 18 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ