የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሖረ ኢየሱስ – ኢየሱስ ሄደ

ጌታችን ሄደ ። የሄደው ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ነው ። የሄደው ወደ ዮሐንስ ነው (ማቴ. 3 ፡ 13) ። ገሊላ ልምላሜ የማይለያት ፣ ጠለ በረከት የሚያረሰርሳት ውብ አውራጃ ናት ። ጌታችን ከዚህች ለምለምና ነፋሻ ግዛት ወደ ዮርዳኖስ ሄደ ። ዮርዳኖስ ከላይ ከገሊላ ከአርሞን ተራራ ተነሥቶ በሙት ባሕር ጉዞውን የሚፈጽም ወንዝ ነው ። ጌታችን ጥብርያዶስ ካለው ጅረት አልተጠመቀም ። የምድር ዝቅተኛ ስፍራ በሆነው በአሞንና በእስራኤል ድንበር ላይ ባለው በዮርዳኖስ ጅረት ተጠመቀ ። እስራኤል በተሻገሩበት ፣ የተስፋውን ምድር በወረሱበት በዮርዳኖስ ተጠመቀ ። መናኙ ዮሐንስ በሚያጠምቅበት ፣ ዓለምን የናቁ ሰዎች በሚመጡበት በዮርዳኖስ ተጠመቀ ። አሞን ያልነው ዛሬ የጆርዳን ግዛት ነዋሪዎች ናቸው ። የዮርዳኖስ ወንዝ ሁለቱን አገሮች የሚለይ ተፈጥሮአዊ ድንበር ነው ። የዮርዳኖስን ወንዝ መሐሉን በገመድ ተካፍለው ይጠቀሙበታል ። ጌታችን የሚመሠርተው ጥምቀት ከሥጋዊ ልደት አውጥቶ መንፈሳዊ ልደት የሚሰጥ ነውና መንፈሳዊ ድንበር ነው ። የተጠመቀ ሰው አሮጌውን ቤተሰብ ትቶ አዲሱን ቤተሰብ ይቀላቀላል ። ይህም የማይጠፋ ዘር ተብሎ ተጠርቷል (1ጴጥ. 1 ፡ 23) ። በሚጠፋ ዘር ሲሟገት የሚውል ወደ ጥምቀት ጸጋው መመለስ አለበት ። የማይጠፋውን ዘር የተቀበለ ክርስቲያን ፣ በሚጠፋ ዘር ራሱን አያቧድንም ።

ጌታችን እስራኤል በተሻገሩበት ወንዝ ተጠመቀ (ኢያ. 3 ፡ 1) ። የግብጽ ኑሮ ማብቂያ ፣ የከነዓን ኑሮ መጀመሪያ ነበር ። አገር ያልነበራቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ አገር የሆኑት ዮርዳኖስን ሲሻገሩ ነው ። ጥምቀት መሻገር ነው ። መሻገር ለጨለማው ኑሮ ጀርባ እየሰጡ ፣ ለብርሃን ዓለም ፊትን መስጠት ነው ። መሻገር ኃጢአትንና ግፍን መተው ፣ ከወንድነት አማኝነትን ማዳበር ነው ። መሻገር የትላንቱ ትላንት አልፏል ብሎ ከአጉል ጸጸት መውጣት ፣ ይቅርታንም መለማመድ ነው ። ጥምቀትን ስናከብር ተሻግሬአለሁ ወይ ? ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል ። ከሱስ ፣ ከዝሙት ተሻግሬአለሁ ወይ ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል ።

ጌታችን መናኙ ዮሐንስ በሚያጠምቅበት በዮርዳኖስ ወንዝ ፣ በጌልጌላ ሸለቆ ተገኘ ። ጌልጌላ ሸለፈት የተወገደባት ፣ አዲስ ትውልድ የተገዘረባት ስፍራ ናት (ኢያ. 5 ፡ 2) ። ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነበር ። በግዝረት ውስጥ የአካል መቆረጥ ፣ የደም መፍሰስ አለ ። ግዝረት ትንሽ ሞት ነው ። ጥምቀትም ከክርስቶስ ሞት ጋር መተባበር ነው (ሮሜ. 6 ፡ 4) ። ውኃው ውስጥ ጠልቀን ስንወጣ ሞትን ለቅጽበት እናየዋለን ። ጌታችን ምሳሌው ጌልጌላ ማዶ እየታየው በዮርዳኖስ ተጠመቀ ፣ ጥምቀታችንን ባረከ ። ንጉሥ መንገዱን መርቆ ሲከፍት ከዚያ በኋላ አእላፋት ያልፉበታል ። በጥምቀት መንገድ ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላ እያለፍን ነው ። ዮሐንስ መናኔ ንብረት ነበር ። በበረሃ ንስሐን የሚሰብክ ነበር ። ጌታችን ወደ ዮሐንስ በመሄድ ምናኔን አከበረ ። መናኝም እንደሚወድድ ገለጠ ። የከተማው መናኝ ፣ የበረሃውን መናኝ ጎበኘ ።

ሖረ ኢየሱስ – ኢየሱስ ሄደ ። መሄድ ያስፈልጋል ። ንጉሥ አማጺ እስኪመጣ አልሄድም ይላል ። ባል ሚስቴ ይቅርታ እስክትጠይቀኝ አልሔድም ይላል ። ለበጎ ነገር ቀዳሚ መሆን ፣ በተሰማን ሰዓት መልካሙን ማድረግ ለዓለም ዕረፍት ያመጣል ። የጥምቀት ዝማሬ ትልቅ መልእክት አለው ። ወረደ ወልድ – ወልድ ከሰማያት ወረደ የሚል አንዱ ነው ። መውረድ ያስፈልጋል ። ከሰማያት ርቀት እርሱ ከወረደ ፣ ከሹመት ወንበር ወረድ ብሎ ሕዝብን ማየት ይገባል ። ሕዝብን ማየት የመጡበትን ስፍራ ፣ የትላንት ማንነታችንን ማየት ነው ። መሪ ከሕዝብ እንጂ ሕዝብ ከመሪ አይወጣምና ። ሁሉም ተፈራርቶ ከተቀመጠ ፣ ካልመጣ አልሄድም ካለ ተቆራርጠን መቅረታችን ነው ። ሰይጣን ከሁሉም በላይ አጀንዳው የሚፈጸምለት በሰዎች መለያየት ነው ። ጥምቀት አንድነት ነው ። አንድነትም በመሄድ የሚገኝ ነው ። ይህንን መሄድ ለመግለጥ ነው ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ወደ ባሕረ ጥምቀት የሚጓዙት ። ወልድ ከመንበሩ ወርዶ ወደ ዮርዳኖስ መሄዱን ለማሳየት ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ትተጋለች ። መልእክቱ እናንተም ሂዱ የሚል ነው።

የጥምቀት በዓልን ባየሁ ጊዜ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ያጽናልን ፣ ወንጌልን በእጅ ለመዳሰስ ያበቃችንን ፣ የነገረ መለኮት ማማ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ፣ ማንነቴ የተዋቀረባትን ቤተ ልሔም ይጠብቅልን ብዬ ሽቅብ ለመመረቅ ፈለግሁ !

አግዙኝ !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም.

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።