የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መለኮታዊ ምስጋና

“በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።” አፌ. 1፡13-14 ።

ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ለመታተም በክርስቶስ የመዋጀት ሥራ ማመን ያስፈልጋል ። ለማመንም መስማት ግድ ነው ፣ የሚሰሙትም ቃለ እግዚአብሔርን ፣ የድኅነት ወንጌልን ነው ። መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል የሚሰገድለት ፣ አካላዊና መለኮታዊ ነው ። ክርስትናን ከሌሎች ሃይማኖቶች ልዩ የሚያደርገው በሦስት አካላት በአንድ አምላክነት በተገለጠው እግዚአብሔር የሚያምን መሆኑ ነው ። በሦስት አካላት ተገለጠ ስንል እንደ አሕዛብ ብዙ አማልክትን እያነሣን አይደለም ። በአንድ አምላክነት ተገለጠ ስንልም እንደ አይሁድና እስልምና አንድ ገጽ እያልን አይደለም ። ሦስቱ አካላት በመለኮት አንድ ሁነው ለዘላለም ይኖራሉ ። ይህንንም በክርስትና ተቀበልነው እንጂ አልፈለሰፍነውም ።

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የአብና የወልድ ሕይወታቸው ፣ የፍጥረታትም የመገኘታቸውና የመንቀሳቀሳቸው ኃይል ነው ። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን መለኮታዊነት የሌለው ፍጡር የሚል እሳቤን እንደ አርዮስ ፣ አካል የሌለው ህፁፅ የሚል ኑፋቄን እንደ መቅዶንዮስ የሚያራምዱ መናፍቃንን ቤተ ክርስቲያን ታወግዛለች ። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አበውን በተስፋ ያስደሰተ ፣ ለነቢያት በትንቢት መነጽር የሺህ ዓመትን ክስተት የገለጠ ነው ። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በተፈጥሮ ክህሎት ተብሎ የሚጠራውን ጥበብ የሚሰጥ ፣ ለአማንያንም የአገልግሎት ጸጋን የሚናኝ ነው ። ስጦታው ብዙ ፣ መዝገበ ሙሉ ፣ ሀብቱ የማይጎድል ፣ የባሕርይ አምላክ ነው ። ከአብና ከወልድ ጋር የኖረው በጥገኝነት ሳይሆን በእኩያነት ፣ በዘመንም ሳያንስ በአቻነት ነው ። በክንድ ውስጥ ያለ ኃይል የራሱ አካል እንደሌለው እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው ሲባል የራሱ አካል የለውም ማለት አይደለም ። በአካል ልዩ ሁኖ በመለኮት ግን ከአብና ከወልድ ጋር አንድ ነው ። መንፈስ ቅዱስ ለሥጋና ለነፍስ ሕይወትና ፈውስ የሚሰጥ ነው ። ሁከትንም ገሥጾ ሰላምን ይሰጣል ፣ ልጅነትን አትሞ እስከ መንግሥተ ሰማያት ይመራል ። በጨለማ ውስጥ ብርሃንን ፣ በፍርሃት ውስጥም ተስፋን ያድላል ። በዚህም ቡሩክ መንፈስ ቅዱስ ይባላል ። ኃጢአትን ይቅር የሚል ፣ በአማካሪዎችና በካህናት አድሮ ኑዛዜን የሚሰማ አጽናኝ መንፈስ ነው ። በጭንቀት ውስጥ ለሚያልፉ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ጽኑ ረዳታቸው ነው ።

ኃያላንን ያስቻለ መንፈስ ነው ። እነዚህ ኃያላን ዓለምን የናቁ ናቸው ። ነገሥታት ዘውድን አስቀምጠው እንዲመንኑ ፣ ጻድቃን በገዳም ፣ ሰማዕታት በደም እንዲጸኑ ያደረገ ፣ ለደናግል ንጽሕናን ፣ ለጳጳሳት የቅን ፍርድን ያስተማረ መንፈስ ነው ። ይህን ቡሩክ መንፈስ የሚያገኙ ቃለ እግዚአብሔርን ሰምተው በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ናቸው ። ሐዋርያው ይህን ቅዱስ መንፈስ የተስፋ መንፈስ ይለዋል ። በብሉይ ኪዳን ክርስቶስ ይመጣል ብሎ ተስፋ የሰጠ ነው ። ተስፋ ያረጋጋል ። በጣዖት ቤት ከመቅበዝበዝ ፣ በፍርሃትም ከመጥፋት በተስፋ ያረጋጋቸው መንፈስ ቅዱስ ነው ። በክርስቶስ አምነው ብዙ መከራ እየተቀበሉ ያሉትን የዛሬ አማኞች መንፈስ ቅዱስ ያረጋጋል ። በፍርድ ቤት ሲነገር የምንሰማው የጥፋተኝነት ውሳኔና የቅጣት ውሳኔ የሚባል አለ ። ጥፋተኛ ነው አይደለም የሚለው በጥፋተኝነት ውሳኔ ይረጋገጣል ፣ ይህን ያህል ቅጣት ይገባዋል የሚለው ደግሞ በቅጣት ውሳኔ ይበየናል ። እንዲሁም አማኙ በክርስቶስ አምኗል ተብሎ የመጀመሪያ ብይን ይሰጠዋል ። እርሱም ድኅነቱን በተስፋ ይቀበላል ። ሁለተኛው ደግሞ መዳኑን የሚወርስበት የምጽአት ውሳኔ ይጠብቃል ። እስከዚያው ድረስ ምእመናንን በተስፋ የሚያጸናቸው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው ። አንድ ሰው ጥፋተኛ ነው አይደለም ተብሎ ውሳኔ በሚሰጥበት ቀን ታላቅ ፍርሃትና ተስፋ አለ ። እንዲሁም ያመነ አሁን በድኅነት ጥላ ውስጥ ሲሆን የማያምንም አሁን በኵነኔ ውስጥ ነው ። ምጽአት በጎችና ፍየሎች የሚለዩበት እንጂ በግና ፍየል የምንሆንበት አይደለም ።

ተስፋው የተሰጠው ወይም የተስፋው የበላይ ጠባቂ እውነት የሆነው ፣ የእውነት መንፈስ ተብሎም በተጠራው በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው ። ድኅነታችን በአምላክ እንደ ተፈጸመ ፣ ተስፋችንም አምላክ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ ይጠበቃል ። በአስተማማኝ እጅ ያለ በመሆኑ ደስታችን ወደር የለውም ። መንፈስ ቅዱስን ማኅተም ይለዋል ። ማኅተም ሥልጣናዊ ምልክት ነው ። ሰው ቢያውቅ ቢመራመር እንደ ደብዳቤ መጻፍ ነው ። ማኅተም ሲርፍበት ግን ያ ደብዳቤ ሥልጣን ይኖረዋል ። ማመንም ማኅተመ መንፈስ ቅዱስን የሚያስገኝ ነው ። ማኅተም ያለበት ዕቃ የተቆጠረና ለሌላ ግዳጅ የማይውል ነው ። እንዲሁም ማኅተመ መንፈስ ቅዱስ ያረፈበት ከቤተ እግዚአብሔር የማይወጣ ፣ የተቆጠረ ፣ ሲጠፋም ፈላጊና ተቆርቋሪ ያለው ነው ። መንፈስ ቅዱስ የርስታችን መያዣ ወይም ዐረቦን ነው ። ዐረቦኑን የሰጠ ሙሉውን ክፍያ እንደሚሰጥ መተማመኛ ነው ። ዐረቦኑ ዛሬ የምናገኛቸው ጸጋዎች ናቸው ። በእግዚአብሔር ቤት ያገኘነው ሰላምና ደስታም ዐረቦን ነው ። በሙላት የሚገኘው በላይኛው ማደሪያችን ነው ።

ክርስቶስ በደሙ ከሞት ግዛት ዋጀን ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ከዓመፃ ግዛት ይዋጀናል ። ሁሉም የተጠሩት የሰው ልጆች እስኪመጡ ድረስ መንፈስ ቅዱስ ይጠብቃል ። ወልድም ቢያድን ፣ መንፈስ ቅዱስም ቢዋጅ ለአንዲት መለኮታዊ ምስጋና ነው ። “ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።”

ቡሩክ እግዚአብሔር ሆይ ምስጋና ይድረስህ !

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /24

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ