የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መልከ ብዙ ፣ ፍሬ ባዶ

“በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል ።” /ዮሐ. 15፡7 ።/

እግዚአብሔር እንዲህ አለ፡-

ልጄ ሆይ ፣ የምትውለው በከንቱ ወሬ ፣ የምታድረው ከዓለም ጋር ነው ። የምትኖረው እኔን ከሚያሳዝኑ ሰዎች ጋር ግፋቸውን አወዳሽ ሆነህ ነው ። የምትስቀው ድሀን ለሚበድሉ ፣ ፍርድ ለሚያጓድሉ ጨካኞች ነው  ። አንተን ካልነካህ ዓለም ቢደባለቅ ፣ ደም እንደ ጅረት ቢፈስስ ፣ የእልቂት ዜና ቢሰማ ግድ የለህም ። በቅጡ ሳትታጠቅ የምትሮጠው የኃጢአት ጓደኞችህ ሲጠሩህ ነው ። ከምታውቀው ሰው ጋር ተኮራርፈህ ከማታውቀው ሰው ጋር ስታወራ ፣ የልብህን ስትጫወት ትውላለህ ። ከሚታየው ዓለም ወጥተህ መንፈስ ሆነሃል ፣ መናፍስትን ረቂቃን ወዳጆችንም አበጅተሃል ። የሚያውቁህ እንዳይታዘቡህ ፈርተህ ከማያውቁህ ዘንድ ተራቁተሃል ። ዓለምን ሁሉ ጠቅልለህ ፍትወት ማሰሪያ ውስጥ ከተሃል ። ሁሉን ስለ እኔ መተዉ ሲገባህ ሁሉን ስለ ሥጋ ፈቃድህ ታደርጋለህ ። ለመጸለይ የሥራህን ጫና ታወራለህ ፣ ከሥራ ወጥተህ እስከ እኩለ ሌሊት ግን ከንቱ ነገርን ታስሳለህ ። ቃሌን ለመስማት ዋጋ መክፈልን ትጠየፋለህ ፣ ሕሊናን ለሚያቆሽሽ ነገር ግን ገንዘብህን ትረጫለህ ።

ልጄ ሆይ ፣ የአበባ እርሻ መልክ እንጂ ፍሬ የለውም ፣ የዘመኑ ሰውም ለላዩ እንጂ ለውስጡ የማይጨነቅ ነው ። ነፍሱን በሥጋው የለወጠ ፣ ነጭ ልብን ትቶ ነጭ ልብስን ያፈቀረ ፣ ከእግዚአብሔር መንግሥት ይልቅ ለፀጉሩ የሚጨነቅ ነው ። ፒኮክ ሰው ሲያያት ክንፏን ትዘረጋለች ፣ እዩኝ እዩኝ ትላለች ። አንተም ታይተው የጠፉትን ማሰብ አቅቶህ እኔ ብቻ ርእስ ልሁን ብለህ ትጨነቃለህ ። ዓለም ተረኛ እንጂ ቋሚ ወዳጅ እንደሌላት ረስተሃል ። የበላዮችህን እየናቅህ የበታቾችህን የምታከብር ይመስልሃል ። የበታችህን ያከበርከው እንዲሞትልህ እንዲሳደብልህ እንጂ እንድትሞትለትና እንድትሰደብለት አይደለም ። እናትህን እየናቅህ እጮኛህን ታወድሳለህ ፣ መምህርህን እንቢ እያልህ ፣ ጓደኞችህን ትታዘዛለህ ። 

ልጄ ሆይ ፣ በውስጥህ ያለው ምነድነው  ቃሌ ሳይሆን ቂም ነው ። ፍቅር ሳይሆን በቀል ነው ። ደግነት ሳይሆን ብድር መመላለስ ነው ። በማታስፈልግበት ቦታ በግድ ተገኝተሃል ፣ በምታስፈልግበት ቦታ ደግሞ ጠፍተሃል ። የሚለምኑህን ትተህ ለማይለምኑህ ተገኝተሃል ። ከሌለው እየወሰድህ ላለው ሰጥተሃል ። በቤትህ ያለው የእኔ ቃል አይደለም ፣ ስለዚህ ቤትህ የጭቅጭቅ መድረክ ሁኗል ። እንከን ፈላጊ ሁነህ  ፣ ለደጅ እየሳቅህ ለቤተሰብህ አኩርፈሃል ። የተስፋ ቃላቴን በልብህ ማስቀመጥ እንቢ ብለህ ዓለም ስጋቷን ሞልታብሃለች ። ኃጢአትን እየደፈርህ በሽታን ትፈራለህ ። መግቢያ እንዳበጀም አንዳንዴ በእልህ ብሞትስ ትላለህ ። የምትናገረውን ስለምትሰማ እኔ የምነግርህን እየሰማህ አይደለም ። እኔ ካንተ ጋር ነኝ ፣ አንተ ግን ከእኔ ጋር አይደለህም ። አንተ በልቤ ውስጥ አለህ ፣ እኔ ግን ባንተ  ልብ ውስጥ የለሁም ። ከልብህ አባረኸኝ ፣ በአፍህ ትፈልገኛለህ ።

ልጄ ሆይ ፣ እኔን እንደ መሰላል መወጣጫ አድርገኸኝ ፣ የደረስህ ሲመስልህ ገፈተርከኝ ። ለመውረድም እንደማስፈልግህ ዘንግተሃል ። ይህችን ቀን ስለ እምነትህ ሳይሆን ስለ ታማኝነቴ ሰጥቼሃለሁ ። በእኔ ብትኖር በሁለንተናህ ብታከብረኝ በነገር ሁሉ ብትታመነኝ ፣  እውነት እውነት ብዬ የነገርኩህን አማን አማን ብለህ ብትቀበለኝ መሥዋዕትህ ሥሙር ፣ ልመናህ ግዳጅ ፈጻሚ ይሆን ነበር ።

ምእመኑም እንዲህ አለ፡-

ጌታዬ ሆይ ከሩቅ እየፈለግሁህ  ከልቤ አገኝሃለሁ ። እየለፈለፍኩ የሚያውቅልኝ አጥቼ አንተ ግን ዝምታዬን ታነበዋለህ ። የምከተላቸው እየሸሹኝ አንተ ግን ትከተለኛለህ ። ለመክሰር ባልንጀሮቼን ስፈልግ አንተ ግን መልካም ማትረፊያ ልትሆነኝ ትፈልገኛለህ ። የመሰለኝን ነገር አምነዋለሁ ፣ ግጥምጥሞሽን እንደ ሐቅ አየዋለሁ ፣ ግምቴን እከተለዋለሁ ። አእምሮዬ ከቀናነት ርቋል ። ፍቅርን ማስመሰል ፣ ደግነትን ልፍስፍስነት ይለዋል ። የችግረኞች ወዳጅ ፣ የድሀ አደጎች አሳዳጊ ፣ የሙት ልጆች ሰብሳቢ ፣ የባልቴቷ ደጋፊ አልሆንኩም ። ልቤም እንደ አፌ በሆነልህ ብዬ እመኛለሁ ። ቀትር የጨለመባቸውን እያየሁ የማይመሽብኝ ይመስለኛል ። የታመሙትን እያየሁ የማልታመም አድርጌ ራሴን እቆጥረዋለሁ ። ሕያው ሰላምህን ፣ ከሙት ኃጢአት መካከል የምፈልግ ከንቱ ሰው ነኝ ። ቁራጭ ሥጋ የሆነው ሰው ከዳኝ እያልኩ ምሉዕ በኩለሄ የሆንከውን አምላክ ማስታወስ ዘንግቼአለሁ ።

አምላኬ ሆይ ፣ ሰዎችን ወደ ቤትህ እየጠራሁ እኔ እንዳልወጣ ፣ እያሳመንኩ እኔ እንዳልክድ ፣ ሱባዔ እያዘዝኩ እኔ ዋዛ ፈዛዛ ነገር እንዳልከፍት እፈራለሁ ። የዓለም ወሬ እሬት ፣ ያንተ ቃል ማር ይሁንልኝ ። የተበደለ ይካስ የሚለው ፍርድ አልባነቴ ይወገድ ። የሞተን ትቼ ገዳይን ማጽናናቴ ከእኔ ይራቅ ። ላሸነፈ ክፉ ሳይሆን ለተሸነፈ ደግ ምስክር አድርገኝ ። ፍትሕን ንቄ ሰላምን መፈለግ ከንቱ መሆኑን አስተምረኝ ። አንተ ከእኔ ጋር ስላለህ አመሰግንሃለሁ ፣ ደስታዬ ሙሉ እንዲሆን እኔም ካንተ ጋር ልሁን ። በልብህ ስፍራ ስላገኘሁ አወድስሃለሁ ፣ እባክህን በእኔም ልብ አንተ ንገሥበት ። አንተም ፣ ቃልህም ፣ መልስህም ከእኔ ጋር ለዘላለም ይኑሩ ። አሜን ።

የፍቅር ጥሪ /1
ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ