የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መልካም ምኞት ትንቢት አይደለም

 “የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፡- በመካከላችሁ ያሉት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፥ እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ ። በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና እኔም አልላክኋቸውም ።” ኤር. 29፡8-9
“ታገኛላችሁ ፣ ይሳካላችኋል” የሚሉ ትምህርቶች “የአፍሪካ ወንጌል” በመባል ይጠራሉ ። የድሀን ሕዝብ ጆሮና ቀልቡን ለመሳብ ታገኛለህ ፣ ይሳካልሃል የሚሉ ስብከት መሰሎች የተለመዱ ናቸው ። እግዚአብሔር እንደሚሰጥ ፣ እርሱ የሥጋና የነፍስ ተንከባካቢ አንደሆነ እናምናለን ። ሰው ግን እርሱን ማመን ያለበት ስለ ህልውናው ፣ ስለ ክብሩ ፣ ስለ እግዚአብሔርነቱ እንጂ ስለ እጁ ስጦታ መሆን የለበትም ። ሃይማኖት ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ግንኙነት እንጂ ከስጦታው ጋር ያለ ግንኙነት አይደለም ። ስጦታው ከሰጪው ጋር የመተባበራችን ውጤት ነው ። የተጨነቀና የማያውቅ ሕዝብ ለሐሰተኛ አስተማሪዎች ተላልፎ ይሰጣል ። አሳልፎ የሚሰጠውም የገዛ ጭንቀቱና አለማወቁ ነው ። ሐሰተኛ አስተማሪዎች የሕዝቡን የስሜት ጣቢያ እየፈለጉ የሚናገሩ እንጂ እንደ እግዚአብሔር ቃል የሚናገሩ አይደሉም ። አገልግሎትም የሚለካው በተከታዩ ብዛት ሳይሆን ያለ ተከታይም እውነት ከሆነ ብቻ ነው ። በተከታይ ብዛት የቡድሀና የሂንዱ እምነት ብዙ አማኞች አሉት ። ቊጥር የመጠን መለኪያ እንጂ የእውነት መለኪያ አይደለም ። የሐሰት መምህራን ጥንትም ነበሩ ። ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ኀዘነተኞች አጽናኝ መስለው በመግባት ወራሽ የሚሆኑ ፣ ለተጨነቁት ሰዎች ነገ ታገኛለህ እያሉ ዛሬ በእጃቸው ያለውን የሚቀሙ ያኔም ነበሩ ። አዲስ ኃጢአትም አዲስ ጽድቅም ዛሬ የለም ።
“የቸገረው ርጉዝ ያገባል ፣ የባሰበት እመጫት” ይባላል ። አብዛኛው ወገን ከጥንቱ ጀምሮ የሚወዳጀው እነዚህን የሐሰት አስተማሪዎችና ትንቢት ተናጋሪዎች ነው ። ሰው በተፈጥሮው ስለ ነገ የማወቅ ጥማት አለው ። ይህ ከእንስሳት ልዩ የሚያደርገው ተፈጥሮው ነው ። እንስሳት ስለ ነገ የማወቅ ምንም ጉጉት የላቸውም ። ሰው ስለ ቀጣዩ የማወቅ ጉጉቱ በካርታ እንዲጠነቁል ፣ ኮከብ እንዲቆጥር ፣ ጠንቋይ ቤት እንዲሄድ ፣ አዋቂ የሚባሉትን እንዲጠይቅ ፣ ነቢያት የሚባሉትንና ያውቃሉ ተብለው የሚወራላቸውን ደጅ እንዲጠና ያደርገዋል ። የአገራችን ሰው ግን፡- “ጠንቋይ ቤት መሄድ ለወሬ መቸኮል ነው” ይላል ። ሁሉም ነገር በጊዜው ሲሆን ይታወቃልና ። ከቀኑ በፊት መስማት ልማትም ጥፋትም አለው ። ሐሰተኛ ነቢያትም ሕዝቡ ምን ይፈልጋል ? የሚለውን ያጠኑ ፣ በብልጠትም በሥነ ልቡና ጨዋታም የዳበሩና ልምድ ያላቸው ናቸው ። “የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” እንዲሉ ሲያፈጥጡ ውሸት እንደሆነ ልቡ እያወቀ ሰው ይቀበላቸዋል ። በዚህም ብዙ ኑሮዎች ይፈርሳሉ ። አገኛለሁ ብለው ያገኙትን ይጥላሉ ። በመንፈሳዊ ቤት ካሉ የቁማር ጨዋታዎች አንዱ ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች የሚጫወቱት ነው ።
የእስራኤል ልጆች የባቢሎን ምርኮ ገና በጠዋቱ አስጨንቋቸዋል ፣ ገና ሰባ ዓመት እንደሚቀራቸው ቢሰሙም መቀበል አልፈለጉም ። ምክንያቱም የሐሰት ነቢያት በሕዝቡ ፊት ባለ ሞገስ የሚሆኑት እውነተኞቹን ካስጠሉና ካቃለሉ በኋላ ነው ። እውነተኛ አስተማሪ የነበረውን ነቢይ ኤርምያስን በጎ ከአፉ የማይወጣ ፣ ሟርተኛ ነው ብለው በሕዝብ ዘንድ አስጠልተውት ነበር ። “ሊውል ያሰበ ሆድ በጠዋት ይርበዋል” እንዲሉ ገና በጠዋቱ ወደ አገራችን እንመለሳለን ይሉ ነበር ። ይህንንም የሚያራግቡላቸው በመካከላቸው የነበሩት በአጉል ተስፋ እንደ ፊኛ ያሳበጡአቸው ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ነበሩ ። “የውሸታም እንባ ባቄላ ባቄላ ያህላል” እንዲሉ ሐሰተኛ አስተማሪዎች በእንባ የሚያታልሉ ናቸው ። ስለዚህ በቀላሉ ስስ ልብ ያላቸውን ወገኖች ይማርካሉ ። ለማንም ሰው ደግ አውራ ደግ ይመጣል የሚል አስተሳሰብ አለውና እነዚህ ሰዎች በቀላሉ ተቀባይነት ያገኛሉ ። ደግ የሚመጣው ግን ደግ ሲኖሩ ነው ።
“እንኳን እህል ውኃ በበላሁ እንቆቆ ፣ አገሬ ገብቼ ሰውነቴ ታውቆ” የሚል ስንኝ አለ ። ከአገሩ የወጣ ሰው የአገሩ ክፉ አይታየውም ። ናፍቆት ጠላትን ሳይቀር ያስናፍቃል ። ብዙ እስረኞች ጠላቴ ናፈቀኝ ይላሉ ። ትልልቅ ሰዎች ውጭ አገር ሁነው ወደ አገር ቤት ደውለው የሚጠይቁት ነገር ናፍቆትን ይገልጣል ። ፀሐይ የምሞቅባት ድንጋይ ደህና ነች ይላሉ ። ይህ ናፍቆት ነው ። ናፍቆት ድንጋይን ሳይቀር ያስናፍቃል ። ታዲያ ከአገራቸው ርቀው የኢየሩሳሌም ጎዳናና ድንጋይ ሳይቀር የናፈቃቸውን እስራኤላውያንን የሚያስቱ የሐሰት ነቢያት ነበሩ ። በነቢዩ በኤርምያስ የተላለፈው መልእክት ግን እነዚህን በመስማት እንዳይስቱ ነው ። ሰው በጥሩ መማር ካልቻለ በጥሩ መቀጣት አለበት ። ቅጣቱም ትምህርት ነውና ። በባቢሎን በጅራፍ እየተማሩ ያሉት በአገራቸው በቃል መማር ስላልቻሉ ነበር ። ተማሪ ለራሱ ደውሎ ከትምህርት ቤት መውጣት ቢችል ኑሮ ብላችሁ አስቡ ። ሁለት ሰዓት ገብቶ ሁለት ተኩል ይደውል ነበር ። የሚወጣው ግን ሥልጣን ካለው ክፍል ሲደወልለት ብቻ ነው ። የመከራ ተማሪም ለራሱ ደውሎ መውጣት አይችልም ። ሲደወልለት ብቻ ይወጣል ። በእውነት እግዚአብሔር ምድራዊውን ችግር ያመጣው ዘላለማዊውን መከራ እንድናመልጥ ነው ። በሽታም በላያችን ላይ በየቀኑ ከሚበቅለውን የኃጢአት አረም ሊከላከልልን የተሰጠን ሊሆን ይችላል ። ራሳችንን ነጻ ሆነን ማየት ከባድ ነው ። ልጓም የሌላት በቅሎ ገደል ትሰዳለች ፣ መከራ የሌለበት ሥጋም ገሀነም ይከታል ።
“በመካከላችሁ ያሉት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፥ እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ ። በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና እኔም አልላክኋቸውም ።” አይጦች አብረውን ይኖራሉ ፣ የምንወደውን ነገር ያሳጡናል ። አብረውን ስለሚኖሩ መድኃኒት መሞከሪያ ይሆናሉ ። መድኃኒት ግን አይሆኑም ። የሐሰት አስተማሪዎችም ሁልጊዜ የሚኖሩት ሰው መካከል ነው ። ዓላማቸው ሰው ማትረፍ በመሆኑ ሊመንኑ አይችሉም ። ብቅ ጥልቅ እያሉ ሊኖሩ ይችላሉ ። ከሰው ግን ተለይተው መኖር አይችሉም ። ሙቀት የሚወዱና የድህነት ብርድ የሚያስፈራቸው ናቸው ። ሰው የስህተትን ትምህርት ሲመርጥ ገንዘብ ወይም ክብር እያስጨነቀው እንደሆነ እንረዳለን ። ድህነት ክፋቱ ወደ ነፍስም ወደ ቤተ ክርስቲያንም ይመጣል ። ድሀ አእምሮ ካለንም ወርቅ አንጠግብም ። ድህነት ተሰናብቶን ቢሄድም ቢመጣስ እያልን እንሰጋለን ። “እባብ ያየ በልጥ ይደነብራል” እንዲሉ ።
ምዋርተኞች ለእኛ መልካም እየተናገሩ ጠላትን በርግማን የሚገለብጡ ናቸው ። ሰይጣንን አድራሻ ያደረጉ ተግሣጾች ይሰማሉ ። በቀጥታ ወደ ሰይጣን መጸለይስ ይቻላል ወይ ? ይውደም ይወጋ የሚሉ ደርግ ጥሎት የሄደው መፈክሮች በመንፈሳዊ ቦታ በየቀኑ ሥራ ላይ ናቸው ። እግዚአብሔርን የማይፈራ ሕዝብ ሰይጣንን በመፍራት ተወጥሯል ። ሰይጣንን የምቃወመው ለእግዚአብሔር በመገዛት እንጂ የርግማን ቃሎች በማውረድ አይደለም ። ለነገሩ ሰይጣንና ጠላት በሚል ስም የምንወጋው ጎረቤቶቻችንን ነው ። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል።”  ያዕ. 4፡7-8 ።ዲያብሎስን የምንቃወመው ለእግዚአብሔር በመገዛት ነው ።
“እናንተም የምታልሙትን ሕልም አትስሙ” ይላል ። ዛሬ እንዲህ ታየኝ ፣ እንዲህ አቃዠኝ የሚሉ ነገሮች በመያዝ ብዙ ውሳኔ የሚወስኑ ወገኖች ነበሩ ።ዛሬ ግን እንኳን በሕልም ያዩት በውን ያዩትም እየጠፋ ነው ። የሚጸናው ምዋርትም ሕልምም አይደለም የሚጸናው በነቢዩ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ነው ። ቃሉ ለጆሮ አይጥምም ። ለባቢሎናውያን ተገዙ የሚል ነበር ። ሕዝቡ ነቢዩን እንደ ባንዳ እያዩት ነበር ። ነገር ግን ባቢሎናውያንን ያመጣው የራሳቸው አለመመለስ መሆኑን አላስተዋሉም ። የእገዚአብሔርን ቃል በስሜታችን ምላስ ካጣጣምነው ነገር ይበላሻል ። ቃሉን በእውነትነቱ ብቻ በመቀበል ባይጥመንም ልናከብረው ይገባል ። የሚደንቀው ሕዝቡም የሚወደው የሚዘርፈውን መሆኑ ነው ። ለእውነተኛ አገልጋዮች ቊራሽ መስጠት እስከማይችል እጁ ተቆልፏል ። ሐሰተኞችን ሲቀልብ ግን ይኮራል ።
በምድር እንስሳትና በሰማይ አእዋፋት መካከል ትልቅ ጦርነት ተነሣ ። ጦርነቱን የምድሩ እንስሳት ሲያሸንፉ የሌሊት ወፍ በርቱ እኔ የእናንተ ወገን ነኝ ፣ እዩት ጥርሴን ትላለች ። ሥጋ በል ናትና ያምኗታል ። ጦርነቱን የሰማይ አእዋፋት ሲያሸንፉ በርቱ የእናንተ ወገን ነኝ ፣ እዩት ክንፎቼን ትላለች ። ጦርነቱ አብቅቶ ሰላምና እርቅ ወረደ ። በዚህ ጊዜ የሌሊት ወፍ ከማን ወገን ትሁን በዚህ ምክንያት በሌሊት መብረር ጀመረች ይባላል ። ዳር ላይ ቁሞ ብቅ ጥልቅ እያሉ መኖር ክርስትናን ያደክማል ። ከሊቃውንትም ከትንቢት ተናጋሪዎችም ወገን ነኝ እያሉ መኖር አንድ ቀን ብቻ ያስቀራል   ። እግዚአብሔር ሲናገር የሌሎችን ምዋርት ብቻ ሳይሆን የራሳችንን ሕልምም ማመን አይገባም ።
አምላኬ ሆይ አንተ ታየኛለህ ። ምርጫዬም በፊትህ ነው ። ዳቦ የያዝኩ መስሎኝ ድንጋይ እንዳልነክስ ፣ አንተን ያገለገልሁ መስሎኝ ለስህተት ነገር ተላልፌ እንዳልሰጥ እባክህ ጠብቀኝ ። ኑሮዬ ግራ ሲያጋባኝ የግራ መንገድ እንዳልመርጥ ፣ ስጨነቅ አጠገቤ ያገኘሁትን እንዳልይዝ የትዕግሥትን ልብ አድለኝ ። ካላሰቡበት የዋሉትን መልስ ። የቀኙን መንገድ ለሕዝብህ አሳይ ።በታላቁ እረኝነትህ ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 9
ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ ተጻፈ አዲስ አበባ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ