“ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው ።” 1ጢሞ. 3፡1 ።
ጌታችን የእርሱ የሆኑትን ሲጠራ ስለሚጠብቃቸው ክብር ሳይሆን ስለሚገጥማቸው መከራ በመጀመሪያ ተናግሯል ። ክርስትና ራስን ካልካድን እግዚአብሔርን ማመን እንደማንችል ያስረግጥልናል ። ማመን በውስጡ ክህደት አለው ። እግዚአብሔርን ስናምን ራሳችንን ክደናል ማለት ነው ። ራሱንም የሚያምን እግዚአብሔርን ይክዳል ። የክርስትናው መርሕ ከዓለም ይለያል ። ዓለም ለማግኘት ማግኘት የሚል መርሕ አለው ፤ ክርስትና ግን ለማግኘት ማጣት ግዴታ ነው ። አምላካችን በነፍሳችን እንጂ በጊዜያችን ተወራርደን የምናመልከው አይደለም ። ስለ እርሱ የሚጎዳንን ኃጢአት ሳይሆን የሚጠቅመንን ነገር ካልተውን ገና አልወደድነውም ማለት ነው ። ወደ እርሱ የሚመጡ ራሳቸውን መካድና መስቀሉን ለመሸከም ትከሻውን ማስፋት ይኖርባቸዋል ። ራሱን ላልካደ ሰው መስቀል ከባድ ነው ። ራሱን ያልካደ ሰው የስሙ ነገር ያስጨንቀዋል ፣ መስቀል ደግሞ ስምን ማጣት ነው ። ራሱን ያልካደ ሰው ከሰው ማነስ ይጨንቀዋል ፣ መስቀል ደግሞ ውርደትን መታገሥ ነው ። ራሱን ያልካደ ሰው ለሰው መኖር ይከብደዋል ፣ መስቀል ደግሞ ስለ ሌሎች ራስን መስጠት ነው ። ራሱን ያልካደ ወገናዊነትን ማሸነፍ ይሳነዋል ፣ መስቀል ደግሞ ሁሉንም በእግዚአብሔር ዓይን ማየት ነው ። ራሱን ያልካደ ምን አገኛለሁ ? ይላል ፣ መስቀል ደግሞ ምን አጣለሁ ? ይላል ። ራሱን ያልካደ ሌሎችን ማገልገል ጥያቄ ይሆንበታል ፣ መስቀል ደግሞ ለሁሉ ሎሌ ሁን ይላል ።
የአገልግሎት ሕይወት ለሚቀልዱና አማራጭ ላጡ ሰዎች በጣም ቀላል ነው ።በእውነት ለሚያገለግሉ ግን ራስን መካድና መስቀሉን መሸከም የሚጠይቅ ነው ። ክርስቶስ መስቀልና ክብር ነው ። በቀራንዮ ካልገባን የጎልጎታን ክብር ማግኘት አንችልም ። ወራሽ የሚወርሰው ትርፍን ብቻ ሳይሆን ዕዳንም ነው ። ከክርስቶስ የምንወርሰውም ክብርን ብቻ ሳይሆን መከራንም ነው ። ስለ ድኅነት ያለውን ሙሉ ዋጋ ክርስቶስ ከፍሏል ፣ ስለ ወንጌል የሚከፈለው ዋጋ ግን ገና ይቀራል ። ወንጌል የማትታሰር ብትሆንም ልጆቿን ግን ለእስራት ታበቃለች ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “ወዳጄ ልቤ” በሚለው መጽሐፋቸው ስለ ወንጌል እንዳሉት፡-
ይዤሽ ወደ ሰማይ ፣
ይዤሽ ወደ ላይ ፣
አንቺ አጋዳይ ።
ሌላው ሰው ሙያቸው ተወድዶ በወንጌል ማመናቸው ተጠልቶ ወኅኒ በወረዱ ጊዜ፡-
“ለፍቼም አልቀረሁ እንደ አገልግሎቴ ፣
ግምጃ ሱሪ እግረ ሙቅ ፣ ወኅኒ ቤት ግዛቴ” ብለዋል ። እኚህ ሰው በሞቱ ጊዜም እህታቸው፡-
“ገዝግዘው ነዝንዘው ጣሉት እንደ ዝኆን ፣
ያው ወደቀላቸው ይበሉት እንደሆን ፤”
በማለት የኀዘን ቅኔ ተቀኝተዋል ።
በዚያ ዘመን ኤጲስ ቆጶስ ለመሆን የሚፈልግ ይሾም ነበር ። ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ዘመን ጀምሮ እስከ 313 ዓ.ም. ድረስ በታላቅ መከራ ውስጥ ነበረች ። መከራው ሲመጣ መጀመሪያ ሰማዕት የሚሆነው ኤጲስ ቆጶሱ ነበር ። ስለዚህ ብዙዎች ይህን መዓርግ ይሸሹ ነበረ ። በዚህ ምክንያት ሐዋርያው “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ” አለ ። የፈለገ ሁሉ ግን አይሾምም ነበረ ። ሐዋርያው መስፈርቱን ቀጥሎ ይዘረዝራል ። ቆስጠንጢኖስ የሃይማኖትን ነጻነት ካወጀ በኋላ ብዙም ሳይርቅ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን መፍላት ጀመሩ ። መናፍቅነት በተቦጨቀ ጥቅስ ቢመጣም ሁለት ነገሮችን መጠማትም ያመጣዋል ። የመጀመሪያው የክብር ጥማት ሲሆን ሁለተኛው የገንዘብ ጥማት ነው ። ከነጻነት ዘመን በኋላም ጵጵስና እንደ መኳንንት የሚፈርዱበት ፣ እንደ መሳፍንት ጌታ የሚሆኑበት የምድራዊ ሥልጣንና ገንዘብ መንገድ እየሆነ መጣ ። ብዙ ቡሩካን አባቶች ቢነሡም በተቃራኒው ወደ ኑፋቄና ወደ መሳፍንትነት ያደሉ ብዙዎች ነበሩ ። በመከራው ዘመን ያልነበሩ መናፍቃን በደንብ መፍላት የጀመሩት መከራው ሲያልፍ ነው ። መከራውን ሲሸሹ የነበሩ አሁን ነጻነት ሲመጣ ጳጳስ ለመሆን የሚፈልጉ ሆነ ። ጣልያን አምስቱን ዓመታት በኢትዮጵያውያን ላይ የመከራ እሳት ሲያዘንብ የሚበዛው ሸሽቶና ባንዳ ሁኖ ነበር ። ነጻነት ሲመለስ ሁሉም አለሁ ብሎ መጣ ። በዚህ ጊዜ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ እንዲህ ብለው ገጠሙ፡-
የጌሾው ወቀጣ ማንም ሰው ሳይመጣ ፣
የመጠጡ ለታ ከየጎራው ወጣ ፤
ዛሬ ጵጵስና የሚፈልግ ቢባል የማይፈልግ የለም ። ያለው መከራ ሳይሆን ምቾት ነውና ። መስቀል ወዳጆቹ ትንሽ ናቸው ፣ ምቾት ግን የሚበዙ ወዳጆች አሉት ። የቤተ ክርስቲያንን ሹመት ለማግኘት ዛሬ ታላቅ ተጋድሎ አለ ። በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሰው ለጵጵስና ታጩ ይባላል ። መታጨታቸውን አንድ ሰው ሲነግራቸው ጠጅ ማስጣል ጀመሩ ። ጉዳዩ ቫቲካን ሲሰማ “ሳይሾም ጠጅ ያስጣለ ቢሾም ምን ሊያደርግ ነው?” ተብሎ ሹመቱ ቀረ ። በእኛም ገና መሾማቸውን ሳያውቁት ቆብ ሲያሰፉ የኖሩ ብዙ ጊዜም የተበላሸባቸው አሉ ። ሹሙኝ ብሎ የሚሾም በቅን ሊፈርድ አይችልም ። እበቃለሁ ብሎ ማሰብም ትዕቢት ነው ። የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን 59ኛው ሊቀ ጳጳሳት አባ መቃርስ መንኵሶ ወደ እናቱ ሲመጣ እናቱ በታላቅ እልልታ ተቀበለችው ። ጳጳስ ሁኖ ሲመጣ ግን በልቅሶ ተቀበለችው ። “ምነው እናቴ” ብሎ ቢጠይቃት፡- “እስከ ዛሬ ትጠየቅ የነበረው ስለ ራስህ ኃጢአት ነበር ፣ አሁን ግን የብዙዎች ዕዳ በእጅህ አለ” አለችው ይባላል ። ጵጵስና ተጠያቂነት ያለበት አደራም ክብርም ነው ። ሹሙኝ ብለው ጉቦ የሚሰጡ ፣ ለእጅ አውጪዎች የሚያጎርሱ እሳት እንደሚሸከሙ ቢያውቁ አያደርጉትም ነበር ። ሹመት ከእግዚአብሔር ተቆርጦ ከመጣ የምንቀበለው እንጂ ለምነን የምንገባበት ሊሆን አይገባም ።
ጳጳስ ወይም ኤጲስ ቆጶስ ተመሳሳይ ትርጉም ሲኖረው የቤተ ክርስቲያን ጠባቂ ማለት ነው ። ቄሱ አጥቢያ ሲያስተዳድር ጳጳሱ ደግሞ አውራጃን ያስተዳድራል ። ቤተ ክርስቲያን አዳጊ የሆኑ የክህነት መዓርጋት አሏት ። መዓርጋት መኖራቸው ብስለትና መሠረት እየያዙ ለማደግ በጣም ይጠቅማል ። ቤተ ክርስቲያንንም ለሁለት ሺህ ዓመታት ይዞ የቆየው ይህ በየዕድሜውና ብስለቱ የሚሰጠው መዓርግ ነው ። በቤተ ክርስቲያን ሰባት መዓርጋት አሉ፡-
1- ሊቃነ ጳጳሳት
2- ጳጳሳት
3- ኤጲስ ቆጶሳት
4- ቀሳውስት
5- ዲያቆናት
6- አናጉንስጢስ /አንባቢዎች/
7- መዘምራን ይባላሉ ።
“ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው ።” /1ጢሞ. 3፡1 ።/ “የሚለው ቃል የታመነ ነው” ይላል ። ይህ ቃል በሌላ ስፍራ አልተጻፈም ። ልክ እንደዚህ ቃል፡- “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ” የሚለውም ቃል በወንጌል አልተገለጠም ። /የሐዋ. 20፡35 ።/ ይህ የሚያሳየን ያልተጻፈልን ብዙ የጌታ ትምህርት እንዳለ ነው ። ለመዳናችን የሚበቃው ግን ተጽፏል ። መልካምን ሥራ ይመኛል ይላል ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ማገልገል ትልቅ ሥራ ነው ። ምናልባት አገልጋይ ነኝ ፣ ዲያቆን ነኝ ለማለት ካፈርን ትልቅ ሥራ መሆኑን መረዳት አለብን ። ነቢዩ ዮናስ በዚያች ጭንቅ ሰዓት ሥራህ ምንድነው ? ሲሉት ባሕርና የብሱን የፈጠረውን እግዚአብሔርን አመልካለሁ ነው ብሏል ። /ዮናስ 1፡9 ።/
ሳይገባን እናገለግልህ ዘንድ የመረጥከን ጌታ ስምህ ይቀደስ ።
1ጢሞቴዎስ 32
ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.