የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መልካም ዕድል

የዲያቆን አሸናፊ መኮንን ገጽ ረቡዕ የካቲት 2፭ 2007 ዓ.ም.
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ሲመላለስ ራሱን የሚያስጠጋበት ጎጆ፣ የሚጸልይበት ልዩ ስፍራ አልነበረውም፡፡ በየጫካው ማደርና መጸለይ ልማዱ ነበር፡፡ ስለ እኛ ሲል የመረጠው ድህነት ልክ አልነበረውም፡፡ እኛ ከሰው ማነስ ያስጨንቀናለ፤ እርሱ ግን ከሰማይ አእዋፋት ከምድር ቀበሮች ያነሰ ኑሮ ኖሯል /ማቴ. 8፡20/፡፡  እርሱ ሞቱ ብቻ ሳይሆን ኑሮውም ቤዛችን ነበር፡፡ ስለ እኛ ድሃ ካልሆነ እኛ በመለኮት ብልጥግና መሞላት አንችልም፡፡ አብዛኛዎቹ የአደባባይ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ ነበሩ፡፡ በራቸውን ከፍተው የሚያስተናግዱት ግን ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚያ ጥቂቶች መካከል ማርታና ማርያም ተጠቃሾች ናቸው፡፡
“ሲሄዱም እርሱ ወደ አንዲት መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤትዋ ተቀበለችው” /ሉቃ. 10፡38/፡፡ እርሱ በመንደራችን ያልፋል፣ ወደ ቤታችን የሚገባው ግን ስንከፍትለት ብቻ ነው፡፡ በመንደራችን ለማለፍ አያስፈቅድም፡፡ ወደ ቤታችን ለመግባት ግን ፈቃዳችንን ይጠይቃል፡፡ ወዳጅን የምንቀበለው በሌላ ቤት ሳይሆን በራሳችን ቤት ነው፡፡ መቀበል በርን መክፈት፣ ጓዳን ማሳየት፣ ማስተናገድ ነው፡፡ ፈሪሳዊው ስምዖን ጌታን እቤቱ ተቀብሎታል፡፡ ግን ቤቱ የተቀበለው ታዋቂ የሆነውን ጌታ በመጋበዝ ለዝነኛነት ነው፡፡ ስለዚህ በቤቱ ጋብዞ ምንም አላደረገለትም፡፡ ለአንድ ተራ እንግዳ የሚቀርበውን ነገር እንኳ አላደረገለትም፡፡ ያቺ ኃጢአተኛ ሴት ግን ያለ ቤቷ ጌታን አስተናገደችው፡፡ ቤቱ የስምዖን ነው፡፡ በዕንባዋና በሽቱዋ ግን እግሩን ያጠበችው ኃጢአተኛዋ ሴት ናት፡፡ ስምዖን ቤቱን ያቺ ሴት ራሷን አቀረበች፡፡ ስምዖን ጋብዞ ታዘበው ያቺ ሴት ግን ኃጢአቷን ተናዘዘችለት /ሉቃ. 7፡36-50/፡፡ እርሱ የሚከብረው በሳሎናችን ሳይሆን በልባችን ነው፡፡ ማርታ ለጌታ በሯም ልቧም ክፍት ነበረ፡፡ ከፍትፍቱ ፊቱ እንዲሉ ፍትፍቱም ፊቱም ሁሉም አልቀረባትም፡፡
ይህች ማርታ፡- “ማርያም የምትባል እህት ነበረቻት፣ እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች” /ሉቃ. 10፡39/፡፡ ማርያም ምንም እንኳ ጌታ ትልቅ እንግዳዋ ቢሆንም ለጌታ ከመስጠቷ በፊት ከእርሱ መቀበልን ፈልጋለች፡፡ ከምትሰጠው የሚሰጣት በልጦባት እግሩ ሥር ተቀምጣ ነበር፡፡ ለጌታ አደባባዩም ሆነ ቤቱ ሁሉም ለእርሱ ቃሉን ማወጂያ ነው፡፡ አገልግሎቱ ባለበት ቦታና ጊዜ ሁሉ ይቀጥል ነበር እንጂ በጊዜና በቦታ የተገደበ አልነበረም፡፡ ማርያም የቃሉን መጽናናት ትፈልግ ነበር፡፡ ያለ ቃሉ ሕይወት እንደሌላት ታውቅ ነበር፡፡ ትላንትን ለመርሳት ዛሬን ለመጋፈጥ፣ ነገን ለመናፈቅ ቃሉን ትሻ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የትላንት ካሣ፣ የዛሬ አቅም፣ የነገ ተስፋ ነው፡፡


“ማርታ ግን አገልግሎት ስለበዛባት ባከነች፤ ቀርባም፡- ጌታ ሆይ፣ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አያገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት” አለችው፡፡
ማርታ ለጌታና ለደቀ መዛሙርቱ ማዕድ ለማቅረብ ከፍ ዝቅ ትል ነበር፡፡ ቃሉ ግን አልተቻትም፡፡ አገልግሎት እንደ ነበር ይናገራል፡፡ አገልግሎት አገልጋዮችን መደገፍም ነው፡፡ ለሚያስተምሩት ማዕድ ማሰናዳትም አገልግሎት ነው፡፡ አገልግሎት መስበክ፣ መዘመር ብቻ አይደለም፡፡ የማይታይ ደጀን መሆንም አገልግሎት ነው፡፡ ማርታ ግን ብቻዋን ባከነች፡፡ በየዓይነቱ ምግቡን ለማቅረብ ስትጣደፍ ጊዜውና አቅሟ አልበቃ አላት፡፡ ማርታ ግን በቤቷ እንግዳ ሆኖ ታየቻት፤ ስለዚህ ማርያምን ጌታ ጋ ከሰሰቻት፡፡ በብዙ አገልግሎት መድከም መልካም ቢሆንም ካልተጠነቀቁ ግን ከሳሽ ያደርጋል፡፡ የሌሎችን አለማገልገል ያሳያል፡፡ ይህንን ሐሜትም ለጌታ እንድንናገር ያደርጋል፡፡ ማገልገል የሌሎችን አለማገልገል ካሳየ ፍቅር አልባ ያደርጋል፡፡ ጌታንም፡- “አያገድህምን?” አለችው፡፡ ኤልያስ ብቻዬን ቀረሁ እንዳለ ጉዳዩ ወደ ጌታ መጣ፡፡ አገልግሎት ውጤታማ የሚሆነው ሲጠባበቁ አይደለም፡፡ የቻሉትን በጸጋ ድጋፍ ተወጥቶ ማለፍ ነው፡፡ ፉክክርና መጠባበቅ ካለ አገልግሎት አይጓዝም፡፡ እግዚአብሔር በአንድ ሙሴ አንድ ሚሊየን ሕዝብን ነጻ አውጥቷል፡፡ አንድ የቆረጠ እልፍ ሥራ ይሠራል፡፡
ጌታ ለማርታ አዘነላት፡፡ ማርታ ይህን ቃል ስትናገር ጉባዔው ተፈቷል፡፡ የሚማሩት ትምህርቱ ተቋርጦባቸዋል፡፡ ስንካሰስ ጉባዔ ይፈታል፡፡ ምእመናን ይጎዳሉ፡፡ ምግብ ለማቅረብ ጠርተናቸው ነገር ተመጋቢ ሆነው ይታመማሉ፡፡ አዎ የማዕድ አገልግሎት የቃሉን አገልግሎት እንዳያደናቅፍ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያት ሰባት ዲያቆናትን የሾሙበት ምሥጢር ይህ ነው /የሐዋ. 6፡2/፡፡ ዛሬም በአሠራር ተይዘን ለማገልገል ጊዜ እንዳናጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ጌታ ማርታን፡- “ማርታ፣ ማርታ በብዙ ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፣ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም” /ሉቃ.10፤41-42/፡፡
 ማርታ ጭንቀቷ ለምሳ ብቻ አይደለም፡፡ ጭንቀቷ ለዓመት ቀለብ ይመስላል፡፡ ጉዳዩ ትንሽ ጭንቀቷ ግን ትልቅ ነበር፡፡ በርግጥም የሚያስፈልገው ምን ያህል ነው? አሁን የሚያስፈልገውስ ምንድነው? የሚያስፈልገን ብዙ ወዳጅ ብዙ ንብረት አይደለም፡፡ ጥቂት ነገር ነው፡፡ ሕይወትን በዕለት ብንኖር የሚያስፈልገው ጥቂት ነው፡፡ መጨነቅ፣ መታወክ፣ መበጥበጥ፣ መተራመስ፣ እንቅልፍ ማጣት ለምንድነው? ብዙ ብንሰበስብ ብዙ አንበላም፡፡ ብዙ ሰው ብናውቅም ብዙ ወዳጅ አይደለም፡፡ ብዙ ብንወልድም ጠቃሚው አንድ ነው፡፡ ብዙ ብናውቅም አንዱን ለመፈጸም ነው የምንታገለው፡፡ የሚያስፈልገው አንድ ወይም ጥቂት ነው፡፡
 ቤታችን ላስገባናቸው ወዳጆቻችንና የትዳር አጋሮቻችን ብዙ ለማቅረብ እንፈልጋለን፡፡ ወደ ቤታችን የመጡት ግን በመጀመሪያ እኛን ለማግኘት ነው፡፡ እኛን የሚተካ፣ ፍቅራችንን የሚበልጥ ግብዣ የለም፡፡ ጥቂቱ ነገር በፍቅር ብዙ ነው፡፡ እኛ ግን የምንታወከው በብዙ ነው፡፡ ላስደስት ስንል እንደክማለን፡፡ ስንደሰት ግን እናስደስታለን፡፡
 ልብ አድርጉ! ጌታ ማርታን አልነቀፈም፡፡ የማርታ አገልግሎትም ያስፈልጋል፡፡ ማዕድ ግን ሁሉን አይተካም፡፡ ለአገልጋዮች ጠብ እርግፍ የሚሉ ቃሉን ግን መስማት አይችሉም፡፡ ቤታቸውን ለእግዚአብሔር ሰዎች ለቀዋል በዚህ ብቻም ረክተው ተቀምጠዋል፡፡
“ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም” ያ መልካም ዕድል ከጌታ እግር ሥር ተቀምጦ ቃሉን መማር ነው፡፡ ዕድል ሁሉ ፈልጎን የሚመጣ ነው፣ ይህኛው ዕድል ግን የምንመርጠው ነው፡፡ በዓለም ላይ ካሉት ድንቅ ገጠመኞች አንዱ ቃሉን ማግኘት ነው፡፡ አንዳንድ ጸጋዎች ይወሰዳሉ፡፡ ሰውዬው ስለ በደለ ሳይሆን ጊዜ አላቸው፡፡ “ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ” ይላልና /1ቆሮ. 13፡8/፡፡ ቃሉን የመስማት ዕድል ግን ለሚያከበሩት የማይወሰድ ዕድል ነው፡፡ እኛስ ይህንን ዕድል መርጠናል ወይስ በአጋጣሚ ነው ቃሉን የምንሰማው? በቤታችንስ ቃሉን እንሰማለን? ቃሉንስ እንደ ትልቅ ዕድል ቆጥረነዋል? በክብሩ እንድንይዘው እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ