የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መልክህ እንዳይሰወረኝ

የታመመን አልጋ አንጥፈህለት የምትፈውስ ፣ የሞተን አልቅሰህለት የምታሥነሣ ፣ ያዘነን አጽናንተህ ማቁን የምትቀድ ፣ በጎዳና የወደቀውን አብረህ አድረህ ቤት የምትሰጥ ፣ የፈራውን አይዞህ ብለህ ማዕበሉን የምትገሥጽ ፣  መንገደኛውን አብረህ ተጉዘህ መድረሻው ላይ የምትቀበል ፣ ከታሰረው ጋር አብረህ ታስረህ ወደ ቤተ መንግሥት የምትወስድ ፤ ርኅራኄን አስቀድመህ ኃይልህን የምታስከትል አንተ ነህ ። አልጋ አንጣፊዬ ፣ አላቃሼ ፣ አጽናኜ ፣ የበረሃ ጓዴ ፣ ያስፈራኝን ያስፈራኸው ፣ የእስር ቤት ዘመዴ አንተ ነህ ። አልጋ ሳታነጥፍ እንኳን አልፈወስከኝ ። ሳታለቅስልኝ እንኳን አላሥነሣኸኝ ። አብረኸኝ ከምኩራብ ሳትወጣ እንኳን አልመለስከኝ ። ቀኑም ያንተ ነው ፤ ሌሊቱም ያንተ ነው እናመሰግንሃለን ።
ወደ ጥፋት የተሳበውን ተላላ የምትመክር ፣ ወደ ዓመፅ የሚያዘግመውን ሞኝ ቀጥተህ የምትመልስ ፣ ወደ ሞት የሚበረውን መንገድ ዘግተህ የምታቆም ፣ ወደ ሲዖል የሚፋጠነውን በሽታ ሰጥተህ የምታሳርፍ አንተ ነህ ። ዛሬ የታሰረው ወገን ሞት በእስር እንደ ተለወጠለት ምነው ባወቀ ! የታመመው ሲዖል በሕመም እንደተቀየረለት ምነው በገባው ! አንተ በምሕረቱ ብቻ ሳይሆን በመዓቱም ትምርበታለህ ። የእኔ የድሀው ወዳጅ ሌሊትን ቀን ማድረግ ልማድህ የሆነ በእኔ ትዕግሥት የዘገየህ ቢመስለኝም ባንተ ሰዓት ግን አላረፈድክም ። ባላይህም ታየኛለህ ። በስውር እጅህ ትመግበኛለህ ። ጽርሐ አርያም ሳስስህ ቤቴን ሞልተሃል ። በሩቅ ስፈልግህ በልቤ ተገኝተሃል ። ሁሉ በሁሉ ነህ ምስጋና ይገባሃል ።
የተራራቁትን የምታገናኝ ድልድይ ፣ ግንቡን አፍርሰህ ሰላምን የምትሰጥ መሰላል አንተ ነህ ። ሰማይና ምድር ተጣልተው አንዱን ለመሸምገል ሲሄዱ ከአንዱ ይርቃሉ ። ሰማይና ምድርን በአንዴ ያገናኘህ መሰላል የሥጋዌው ባለ ምሥጢር መድኃኔ ዓለም እናመሰግንሃለን ። እኔ አንዴ ሰጥቼ ሁለተኛ ለመስጠት እቸገራለሁ ። አንተ ግን ይህን ሁሉ ወፈ ሰማይ ሳትደክም ትመግበዋለህ ። እኔ አንድን ሰው ለመሸከም አቅም የለኝም ፤ አንተ ግን ሁሉን በትዕግሥትህ ታሳድረዋለህ ። የከደንከውን ማን ይከፍተዋል ? የከፈትከውንስ ማን ይዘጋዋል ?
ባለ ዝናው ፣ ስመ ጥር ጌታዬ በጉድለቴ ላይ ገናንነትህ ይገለጥ ። ያንተ የፍቅር ነጋሪት ሲሰማ ሥጋ ለባሽ ፀጥ ይበል ፣ የሞት ማስደንገጥም ይወገድ ፣ የበሽታ ጉልበትም ይሰበር ፣ የተደባለቀ የሰው ቋንቋ ይጥራ ። ተስፋ ቆርጦ የሚመለሰው ባለበት ይቁም ።
ጌታዬ ሆይ በማጣቴ ላመሰግንህ ገና ነኝ ፤ በማግኘቴ እንዳመሰግንህ እርዳኝ ። ጠላቴን ለመውደድ አልለምንህም ። ወዳጄን እንድወደው እርዳኝ ። በበረትም በዙፋንም አንተ ፣ አንተ ነህ ። ሰማይና ምድር የማይችሉህ በድንግል እናትህ ማኅፀን የተወሰንክም አንተ ነህ ። ነውሬን ልትከድን በመስቀል የተራቆትህ ፣ የተራቆትከውም የምታለብሰውም አንተ ነህ ። አንተ ራስህም የጽድቅ ሸማ ነህ ። ባለጠጋ ቢያለብስ ደግ ይባላል ። አንተ ግን ከደግ በላይ ልብስ ነህ ። እስክመጣ ምስጋናዬን ልላክልህ ። ይህን ትመስላለህ እያልሁ በቃላት ሥዕል መሳሌ እንዳያደክመኝ ፣ ከናፍቆት ብዛትም መልክ እንዳይሰወረኝ እባክህ ቶሎ ናልኝ ። ልመናዬን በብሩህ ገጽ ፣ በብርሃን ፊት ተቀበልልኝ ።
የነግህ ምስጋና /10
መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ