የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መሐሪዬ እግዚአብሔር

 “ተራሮች ይፈልሳሉ፥ ኮረብቶችም ይወገዳሉ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አይፈልስም የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም፥ ይላል መሐሪሽ እግዚአብሔር” ኢሳ. 54፡10 ።
ከፍ ያለው ተራራ ፣ ዓይንን የገዛው ኮረብታ ፣ ከሸለቆዎች በላይ ፣ ከምድርም የላቀው ፣ ከፊት ሲያዩት ፍርሃት ፣ ከኋላ ሲያዩት ተረት የሆነው ያ ተራራ ይፈልሳል ። የተመኩበት ትልቅ ሰው ራሱን የሚያስጠጋበት ያጣል ። አገር ይሰጥ የነበረው መቃብር ያጣል ። አለሁ ሲል የነበረው ዳግም ላይነሣ ይወድቃል ። ንግሥናውን አጥቶ እንደገና የተመለሰ ንጉሥ በታሪክ ጥቂት ነው ። ክብሩ ለጊዜው ፣ ውድቀቱ ለዘላለም ነው ። የዓይን ሁሉ ማረፊያ ፣ የጆሮ ሁሉ ዜና የነበሩት እንዳልነበር ይሆናሉ ። ሲሰወሩ የነበሩ አይመስሉም ። ስንቱን እንዳላንቀጠቀጡ ታሪካቸው የልጅ ማስተማሪያ ይሆናል ። ተራሮች ሲሰወሩ በዘላለም ተራሮች የምታበራው ግሩም እግዚአብሔር አንተ ግን ድንቅ ነህ ። የለም ያሉህ ዛሬ የሉም ፤ አንተ ግን ትኖራለህ ። ክደው ያስካዱህ መቃብራቸው ጠፍቷል ፤ አንተ ግን በአርአያም መንበርህ ትወደሳለህ ። ሥልጣንህ ሥጋት የለውምና የለም ሲሉህ መልስ አልሰጠህም ። ስንቱ ጎበዝ ደከመው ፣ ስንቱ ቆንጆ ረገፈ ፣ ስንቱ አዋቂ አበደ ። አንተ ግን በማይደፈር ግርማ ትኖራለህ ። ለነገ ያሉት ለዕለት አይበቃም ። ይኖራል ያሉት ዕለቱን ያልቃል ። ባሰቡት ቀርቶ ባላሰቡት ይዋላል ። አንተ ግን በጌትነት ዙፋንህ ፣ ከልካይ በሌለው አሳብህ ፣ ሁሉን በሚችለው ባሕርይህ ትኖራለህ ። የተሸከምከን እግዚአብሔር በትከሻህ ላይ ደልዳላ መስክ የሰጠኸን ጌታ ፣ ሥጋህን ደምህን በልተን የተሸከምንህ አምላክ ተመስገን እንልሃለን ።
ተራራ ሲሰወር ያስደነግጣል ። ግዙፉ ሲያንስ ፣ ዓይን የሚሞላው ዓይን ፈልጎ ሲያጣው ፣ ዙሪያውን ያስጨነቀው መድረሻ ሲያጣ ግራ ያጋባል ። ዓለም እንዲህ ነው ። ተራሮች የሚሰወሩበት ፣ ኮረብቶች የሚጠፉበት ነው ። ቋሚ ነገር የሌለበት ሁሉም ተለዋዋጭ ነው ። ተረኛ እንጂ ዘላቂ ትልቅ ዓለም የላትም ። ነገሥታት ያልፋሉ ፣ ጀግኖች ተገንዘው ይቀበራሉ ። አንተ ግን የማለፍ ሥርዓትን እየመራህ ትኖራለህ ። ተራሮች ሲሰወሩ ኮረብቶች ሲወገዱ ልቤ የደነገጠው ዓይኔ ስላያቸው ነው ። እባክህን ጌታዬ ማመኔን ባንተው አድርገው ።
ከዛሬ ጀምሮ ለዘላለም የእኔ ተራራ ቸርነትህ ነው ። ቸርነትህ ሲሸከመኝ  የማይከብደው ፣ ሲሰጠኝ የማይሰለች ፣ ሲሰፍርልኝ የማይታዘብ ነው ። የገንዘብ ቁልል ይሰወራል ። የሹም ወዳጅም ያበቃል ። አንተ ግን ጽኑ ነህ ።በተዘጋው በኩል በር ትከፍታለህ ። የማይወገደው የሰላም ቃል ኪዳንህ ከእኔ ጋር ይሁን ። መሐሪዬ እግዚአብሔር ተመስገን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ