መርፌውና ክሩ በጣም የተቃረኑ ናቸው። ነገር ግን በጣም የተዋደዱና የተፈላለጉ ናቸው። ክሩ ልፍስፍስ በራሱ እንኳ መቆም የማይችል ነው። ጥሶ ለማለፍም አይሞክረውም። መርፌው ላይ ሲታሰር ግን ውስብስቡን መንገድ እየጣለ፣ ከፊት ያለውን እየወጋ በመጨረሻ ብቅ ይላል። መርፌው ብቅ ሲል የታዘለችዋ ክርም እንደ ጎበዝ ብቅ ትላለች። ደካማዋ ክር ከመርፌው ጋር በመታሰርዋ አለመቻልዋ መቻል አግኝቶ የተቀደደውን ትሰፋለች። የተበተነውን ትሰበስባለች።
ልክ እንደ ክሩ እኛም ደካማዎች፣ ሳንጀምር የሚደክመን ልፍስፍሶች፣ ውስብስቡን መንገድ መጓዝ የማይቻለን መንገድ ቀሪዎች ነን። በክርስቶስ ላይ ስንታሰር ግን እንጸናለን። ጥሰን የምንወጣ ከፊታችን ያለውን ሁሉ የማንፈራ፣ የነገን ስጋት ያሸነፍን እንሆናለን። መግለጥ የማይቻለውን ውስብስቡን መንገድ አልፈን በመርፌው ጀርባ ላይ ሆነን ብቅ እንላለን። ዋናው አለመቻላችን አይደለም። በመርፌው ላይ ማለት በክርስቶስ ላይ በእምነት መታሰራችን ነው። መርፌው ከፊት ለፊት የሚዋጋ ሹል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስም ጠላትን ሁሉ ድል የሚነሣ ነው። “የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ላንተ ይብስብሃል” የተባለለት ነው /የሐዋ. 9፡5/። ዓለቱን እሰብራለሁ ብሎ ዓለቱን ቢወድቁበት ሰባሪው ዓለት ክርስቶስ ነው /ማቴ. 21፡44/። ዓለቱ ቢወድቁበትም ቢወድቅም ይሰብራል። ዛሬ እናጥፋህ ብለው ቢወድቁበት ይሰብራል፣ ነገ ደግሞ በደመና ሲመጣ ያላመኑት ላይ የሚወድቅ ዓለት ነው።
መርፌው ከኋላው ለስላሳና ደካማዋን ክር ለመሸከም አንድ ቀዳዳ ያለው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስም እኛን ለማስጠጋት አንድ በር ብቻ አለው። እርሱም እምነት ነው። እርሱ በጠላት ፊት ባለ ግርማ በእኛ ዘንድ ግን መጠጊያ ነው። በቅዳሴአችን፡- “የማይደፈር ግሩም ነው በእኛ ዘንድ ግን ትሑት ነው፣ የማይገኝ ልዑል ነው እኛ ግን አገኘነው ከእርሱም ጋር በላን ጠጣን” እያልን የምናመሰግነው ነው። ከሁሉ በላይ የሚሸከመን፣ የማይታለፉ ቀኖችን የሚያሳልፈን ነው። በሕይወት ጉዞአችን ላይ የሁለት ሰው ዱካ ስናገኝ ከጌታ ጋር የነበርንበት ነው፣ አንድ ዱካ ስናገኝ ግን ጌታ እኛን የተለየበት ሳይሆን ያንን ቦታ ማለፍ ስለማንችል ጌታ እኛን የተሸከመበት ስፍራ ነው። መርፌው በሚያልፍበት የሰው እጅ ካለ መርፌው ሲመጣ ወዲያው ተወግቶ ስፍራ ይለቃል። በመርፌው ፊት ውስብስብነትና የሰው እጅ አቅማቸው አይወራም። መርፌው የተንጠላጠለችውን ክር ጥሎ አይገባም። ጌታም ያመኑትን አይጥልም።
ክሯ መንገድ ላይ ስትቀር እዚያው ማስተካከል አትችልም። እንደገና ጉዞዋን መጀመር አለባት። ከጌታ ጋር ያለን ቋጠሮ ሲፈታ እንደገና በንስሐ መጀመር ይገባል። አንድ ሰው ረጅም ተራራን ሲወጣ ጫፉ ጠፍቶበት መባዘን ጀመረ። የተራራውን ጫፍ ማግኘት አቅቶት ሲጨነቅ አንድ ሰው መጣ። “እባክህ የዚህ ተራራ ጫፍ በየት በኩል ነው” አለው። ያ ሰውም፡- “መንገዱን ስለ ሳትህ የዚህን ተራራ ጫፍ ለማግኘት ከመጀመሪያው መጀመር አለብህ” አለው። ስንስት ከመጀመሪያው መጀመር አለብን። ከመጀመሪያው ለመጀመር አላውቅም ማለትን ይጠይቃል። ዛሬ ጫፉን ማግኘት አቅቶት ሁሉም የሚባዝነው ባለው ነገር ላይ ለመደረብ እንጂ ከመጀመሪያው ለመጀመር ስለማይፈልግ ነው። የዚህ ሁሉ ትርምስ መነሻው፡- “ጌታ ሆይ ግማሽ ሙሉ ነኝ ጨምርብኝ፣ እገሌ ፍጹም ባዶ ነው ስበርልኝ፣ የእኔ ህጸጽ የምግባር ነው የእገሌ የሃይማኖት ነው…” የሚለው አስተሳሰብ ነው። የመሻል መስፈርት መንፈሳዊ አይደለም። ዐስር ከገደለው አንድ የገደለው ይሻላል። መሻል ንጹሕነት አይደለም። የመሻል መጽናናት እስካልተወገደ ንስሐ አይመጣም። ለመጨረስ መጀመር ያስፈልጋል። መጀመሪያው ካልተገኘ መጨረሻው አይገኝም። ገና ከአስተሳሰባችን ከሳትን ከእግራችን ላይ መስተካከል አንችልም።
ዋናው የእኛ አቅም ደካማ መሆኑ አይደለም። ክሯ የተቀደደውን ለመስፋት፣ የተበተነውን ለመሰብሰብ ትልቁ ፈተናዋ አለመቻሏ አይደለም። በመርፌው ላይ ለመታሰር ፈቃደኛ መሆን፣ መርፌውን እያስቀደሙ ለመከተል፣ መርፌው በሄደበት ለመጓዝ መጨከን ያስፈልጋታል። ብዙ የተቀደደ ብልሽት ብዙ የተበተነ ወገን አለ። ይህን ለመስፋትና ለመሰብሰብ ክርስቶስን እያስቀደሙ መከተል ይገባል። እኛስ በክርስቶስ ላይ ታስረን ይሆን? መርፌውና ክሩ የተቃረኑ ቢሆኑም ይፈላለጋሉ። ማግኔት ተቃራኒውን እንደሚስብ ጌታም ኃጢአተኞችን በፍቅር ይስባል። አለመቻላችን በእርሱ መቻል ይጣሳል። የታሰርነው በአስተሳሰባችን ላይ ነው ወይስ በክርስቶስ?
እኔ የክርስቶስ ባሪያ