የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መስቀሉ ዛሬም ተቀብሯል

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ!

“ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።” ገላ. 6፡14።

የሰው ልጅ ተፈጥሮ የመስቀል ቅርጽ ያለው ነው ። በራሱ ስህተት ወድቆ በመስቀል ሞት የዳነው የሰው ልጅ ጥንተ ተፈጥሮው የመስቀል ቅርጽ ይዟል ። ስድስት ክንፍ ያላቸው ካህናተ ሰማይ ሱራፌልም የመስቀል ቅርጽ ሠርተው “ቅዱስ ፣ ቅዱስ ፣ ቅዱስ” እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ ። ኢሳ. 6፡2። አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ሊሠዋበት የነበረው የሞሪያ ተራራ ጌታችን የተሰቀለበት የቀራንዮ ኮረብታ ነው ። በኅሊናው የሠዋውን ልጁን ይስሐቅን በሦስተኛው ቀን እንዳገኘው ፣ በእውነት የተሠዋው ክርስቶስም በሦስተኛው ቀን ተነሥቷል ። ዘፍ. 22፡2 ። መልከ ጼዴቅ ኅብስተ አኮቴት ፣ ጽዋዐ በረከት ይዞ አብርሃምን ሲቀበለው ክህነቱ ዘላለማዊ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን እንደሚቆርስ ፣ ደሙን እንደሚያፈስስ የሚያሳይ ነው ። ዘፍ. 14፡18። ባሕረ ኤርትራ የተከፈለበት የሙሴ በትር የመስቀሉ ምሳሌ ነው ። ጌታችን ባሕረ ሞትን በሞቱ ከፍሎታልና ። የለመለመች የአሮን በትርም ሕያው ሆኖ የሚያድነውን የክርስቶስን ቤዛነት የምትገልጽ ናት ። አንድ ጊዜ የተደረገው የአድዋ ድል ለሁል ጊዜውም የነጻነት መዝሙርና ትምክህት ከሆነ አንድ ጊዜ የተፈጸመው የጌታችን ሞትማ እንዴት የነጻነታችንና የድኅነታችን ምሥጢር አይሆንም! በደብተራ ኦሪት ወይም በሙሴ ድንኳን ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች መስቀሉንና ቤዛነቱን የሚተርኩ ነበሩ ። በመሠዊያው ላይ ፍሙ አይጠፋም ነበር ። የእግዚአብሔር ቍጣ እንደ ነደደ ማሳያ ነበር ። በመስቀሉ መሠዊያ ግን ፍቅር ላይጠፋ እንደ ጋመ ይኖራል ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቷል ። ሞቱ ሞታችንን ሻረው ። “እሾህን በእሾህ” እንዲሉ ሞትን በሞቱ ድል ነሣው ። አዳም ቢሞት በጥፋቱ በመሆኑ አላዳነንም ፤ ንጹሑ ክርስቶስ ግን ያለ ጥፋቱ በመሞቱ ድነናል ። ቤዛነት ንጹሕ መሆን ያሻዋልና ። ደግሞም ቤዛነት አምላክነት ያስፈልገዋል ። በፍጡር ዓለም አይድንምና ። መስቀል በቤተ አይሁድ የርግማን ምልክት ፣ በቤተ አሕዛብ የውርደት ሞት የሚከናወንበት ነበር ። ጌታችን የእኛን ርግማን ወሰደ ፣ ስለ እኛም በዓለም ፊት ተዋረደ ። ሮማውያን ዜጋቸው በመስቀል ሞት እንዲቀጣ አይፈቅዱም ነበር ። ሐዋርያው ጳውሎስ በሰይፍ የሞተው ሮማዊ ዜግነት ስለነበረው ነው ፤ ሐዋርያው ጴጥሮስ ግን በመስቀል ላይ የሞተው ሮማዊ ስላልሆነ ነው ። ጌታችን ግን በመስቀል ላይ በመሞት ውርደታችንን ተሸከመ ። በመስቀል ላይ ቅጣት መፈጸም የጀመሩት ቀድሞ ፋርሳውያን የዛሬዎቹ ኢራናውያን ቀጥሎ ሮማውያን ናቸው ። የመሬት አምላክ ብለው የሚጠሩት ኦርሙዝድ ወንጀለኛው መሬት ላይ ቅጣቱን ከተቀበለ ይረክሳል ብለው ያስቡ ነበር ። ጌታችን በመስቀል ላይ ሲሞት መሬታችንን ያረክሳል ተብሎ ነው ። መሬትን የፈጠረ ግን እርሱ ነው ። “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ” ተብሎ የተዘመረው በእርሱ ሞት ነው ።

መስቀል ጥልቅ ትርጉም ያለው ነው ። ቁጠባና ወሰን የሌለበት የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅር የተገለጠው በመስቀል ላይ ነው ። በዘባነ ኪሩቤል የሚገለጠው የክብር አምላክ ፣ በዘባነ መስቀል ላይ ሁኖ በፍቅር አብርቷል ። መስቀል እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለጠበት አደባባይ ፣ ደግሞም ንጉሣዊ ዙፋን ነው ። በኢየሩሳሌም ይነግሣል ብለው ሲጠብቁት እርሱ በኢየሩሳሌም ተሰቀለ ። እነርሱ ውርደት ቢሉትም ለፍቅር መሞት ግን ንግሥና ነበረ ። ገዳይ ነገሥታትን ሊዘልፍ የነገሥታት ንጉሥ በመስቀል ላይ ሞተ ። እርሱ በሰማይ ሠራዊት ቢኖረውም የሚጠብቃቸው እንጂ የሚጠብቁት አልነበሩም ። ብዙ አገልጋዮች ያሉት ክርስቶስ እኔ ልሙትላችሁ ብሎ ሞተ ። በሠራዊት ሞት የሚኖሩ ነገሥታት ባሉበት ዓለም ፣ ለሠራዊቱ የሞተ ንጉሥ ክርስቶስ በእውነት ድንቅ ነው ። መስቀል ቤዛነት ነው ። ሞት ስለሚገባው ሞት የማይገባው የተቀጣበት ነው ። መስቀል ወንጌል ነው ። ክርስቶስ በመሞቱ የተገኘ የምሥራች ነውና ። መስቀል የሌሎችን ችግር እንደ ራስ ቆጥሮ ዋጋ መክፈል ነው ። መስቀል መከራ ነው ። ለእውነትና ለወንጌል ዋጋ መክፈል ነው ። መስቀል የማያቋርጥ የመሥዋዕትነት ኑሮ በየቀኑ ስለ ክርስቶስ የመገደል ሕይወት ነው ። በመስቀል ማጌጥ ቀላል ነው ፣ መስቀልን መኖር ግን ከባድ ነው ። ለጠላት መማለድን የሚጠይቅ ነው ። መስቀል ሰላም ነው ። ሰማይና ምድር የታረቁበት ፣ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ነው ። መስቀሉ ዛሬም ተቀብሯል ። ክርስቲያን ራስ ወዳድ ሲሆን መስቀል ተቀብሯል ። የክርስቶስ የማዳን ሥራ መነገርና መተረክ ካቆመ መስቀሉ ተቀብሯል ። ሊሞቱ የተጠሩ አማንያን ሌላውን መግደል ከጀመሩ መስቀል ተቀብሯል ። ሰላም ጠፍቶ ሰው ሰውን ከበላ መስቀሉ ተቀብሯል ። ዓለማዊነት በእግዚአብሔር ቤት ከነገሠ ፣ ቤተ ክርስቲያን ግፍን ማውገዝ ከፈራች መስቀል ተቀብሯል ። እርስ በርስ መፈራረድና መካሰስ ከበዛ መስቀል ተቀብሯል ። በምእመናን መካከል በጎሣና በቋንቋ መለያየት ከመጣ መስቀል ተቀብሯል ። ዛሬም መስቀሉ ተቀብሯልና እናውጣው ።

ዕለተ ብርሃን 10

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 16 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ