እንኳን ለ2011 ዓ.ም የመስቀል በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ !
መስቀል የጣዖት አምልኮን አጠፋ። ለዓለም ሁሉ በማብራት ሁሉንም ሕዝብ ወደ አንዲቷ ቤተ ክርስቲያን በመሰብሰብ በፍቅር አንድ አደረጋቸው።
† መስቀል የሙታን ትንሣኤ ነው ።
† መስቀል ለክርስቲያኖች ተስፋ ነው ።
† መስቀል ለሽባው ምርኩዝ ነው ።
† መስቀል ለድሀው አጽናኝ ነው ።
† መስቀል የትዕቢተኛው መጥፊያ ነው ።
† መስቀል ተስፋ ለቆረጡ ተስፋ ነው ።
† መስቀል በባሕር ለሚጓዙ/ለመርከበኞች ምግብ ነው ።
† መስቀል ለአውታታዎች መሸሸጊያ ነው ።
† መስቀል ለድሀ አደጎች አባት ነው ።
† መስቀል ለኀዘነተኞች መጽናናት ነው ።
† መስቀል የሕፃናት ጠባቂ ነው ።
† መስቀል የሰው ልጅ ክብር ነው ።
† መስቀል የሽማግሌዎች አክሊል ነው ።
† መስቀል በጨለማ ለሚኖሩት ብርሃን ነው ።
† መስቀል ለባሮች ነጻነት ፣ ላልተማሩት ጥበብ ነው።
† መስቀል የነቢያት ስብከት ፣ የሐዋርያት የመንገድ ጓደኛ ነው ።
† መስቀል የልጃገረዶች ድንግልና ፣ የካህናት ደስታ ነው ።
† መስቀል የቤተ ክርስቲያን ብሎም የዓለም መሠረት ነው ።
† መስቀል የአብያተ ጣዖታት ውድመት ፣ የአይሁዳውያን ፈተና ነው።
† መስቀል የለምጻሞች መንጻት ፣ የደካሞች ብርታት ነው ።
† መስቀል ለተራቡ እንጀራ ፣ ለተጠሙ ምንጭ ነው ።
† መስቀል የመነኮሳት መልካም ተስፋ ፣ ለተራቆቱትም ልብስ ነው ።
በዚህ ቅዱስ መሣሪያ ጌታችን ክርስቶስ ሁሉንም ይውጥ የነበረውን የሲዖልን አንጀት አራቆተ በዲያብሎስ አፍ ያሉትን ብዙ ወጥመዶችም ዘጋ። መስቀልን ተመልክቶ ሞት ፈራ ፤ ከአዳም ጋር አብሮ ይዞ የነበረውን ሁሉን ፍጥረት ለቀቀ ። እግዚአብሔርን የተሸከሙ ሐዋርያት መስቀልን ታጥቀው የጠላትን ሁሉንም ኃይል ድል አደረጉ ፤ ሰውን ሁሉም በመረባቸው አጠመዱ። የተሰቀለውንም እንዲያመልኩ ሁሉንም አንድ ላይ ሰበሰቡ ። (ወታደሮች) በጦር መሣሪያ እንደሚታጠቁት የክርስቶስ ሰማዕታት የአሳዳጆችን ዕቅድ ሁሉ ድል አደረጉ ። በግልጽም መስቀል የተሸከመውን አምላክ ሰበኩ። ለክርስቶስ ብለው መስቀሉን ተሸክመው በዓለም ያለውን ሁሉንም ነገር ካዱ ፤ በበረሃና በተራራ በዋሻ ኖሩ ፣ ዓለምንም እንቢ አሉ ።
ነገር ግን ይህ የማይበገር የኦርቶዶክስ ግንብ ፣ የሰማያዊው ንጉሥ የድል መሣሪያ የሆነውን መስቀሉን ለማመስገን የተገባ ቋንቋ እንዴት ያለ ነው !? ኃያሉ ጌታ በመስቀል በቃላት የማይገለጥ በረከትን ለሰው ልጆች ሰጠ ።
ስለዚህ በግንባራችን ፣ በዓይናችን ፣ በአፋችንና በደረታችን ላይ ሕይወት የሚሰጠውን መስቀል እናስቀምጥ ። (እነዚህን አካሎቻችንን) የክርስቲያኖች የማይበገር መሣሪያ ፣ የአማኞች ተስፋና ብርሃን በሆነው በመስቀል እናስጊጣቸው ። በዚህ የኦርቶዶክስ እምነት ምርኩዝ ፣ አዳኝ በሆነውም በቤተ በክርስቲያን የምስጋና መሣሪያ ገነትን እንክፈት ። ለአንድ ሰዓትም ይሁን ለአንዲት ቅጽበት መስቀልን አንርሳ ፤ አሊያም ያለ መስቀል አንዳች አናድርግ ። ነገር ግን እንቅልፍ ስንተኛ ሆነ ስንነሣ ፣ ስንሠራ ሆነ ስንመገብ ወይም ስንተኛ ፣ መንገድ ስንጓዝም ሆነ በባሕር ስንሄድ አሊያም ወንዝ ስናቋርጥ የአካል ክፍሎቻችንን ሁሉ ሕይወት ሰጪ በሆነው መስቀል እናስጊጥ ። “ከሌሊት ግርማ ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር ፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን” (መዝ 90(91)፥5-6) አንፍራ ። ኦ! እናንተ ክርስቲያኖች ሁልጊዜ የክርስቶስን መስቀል እንደ ረዳትና አጋዥ ከጎናችሁ ከያዛችሁ የሚቃወመን ኃይል አይቶት ይርዳል ፤ ይሸሽማልና ። “ዲያብሎስ ወደ እናንተ አይመጣም፤ አንዳች መቅሰፍትም ወደ መኖሪያችሁ አይገባም ።”
ለዘላለሙ አሜን !