የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መስፈርት ይኑረን

 “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል ፤ የማይነቀፍ” 1ጢሞ. 3፡2
አንድ አባት፡- “መስፈርት ከሌለው አገርና ዘመን አድነኝ ብለህ ጸልይ” ብለውኛል ። ይህ ምክር ከአሥራ አራት ዓመት በላይ ይሆነዋል ። እኚህ አባት በመቀጠል፡- “መስፈርት ቢኖር ኖሮ እኛ ተቀምጠን እውነተኞች አይባረሩም ነበር” ብለዋል ። መስፈርት የሌለው ሕይወት ከባድ ነው ። መስፈርት የሌላቸው ርግቦቹን ሸኝተው ነጣቂዎቹን ይዘው ተቀምጠዋል ። የሚወዷቸውን ገፍተው ከሚጠሉአቸው ጋር ተጣብቀዋል ። መስፈርት የሌላቸው ከማን ጋር መዋል እንዳለባቸው አላወቁምና ገንዘባቸውን ፣ ክብራቸውን ፣ ሰላማቸውን አጥተዋል ። መስፈርት የሌላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን እግዚአብሔር ላለው ሰው ሳይሆን ገንዘብ ላለው ሰው ሸጠዋል ። እግዚአብሔር ላለው ይሰጣል ፣ ገንዘብ ላለው ይሸጣልና ። እነዚህ ወገኖች ትልቅ ቤት ትልቅ ጉድ እንዳለበት አላወቁም ። መስፈርት የሌላቸው ማኅበራት ሃይማኖት ትልቅ ርእስ ፣ ሰማይና ምድር የማይችለው ትልቅ አሳብ ያለበት መሆኑን ሳያውቁ የነጠላ ቁጨት ውስጥ ከትተውታል ። መስፈርት ከሌለ ዶግማና ቀኖናን መለየት ያቅታል ። ዶግማውን እንደ ቀኖና ፣ ቀኖናውን እንደ ዶግማ ፤ የፈቃዱን እንደ ግድ ፣ የግዱን እንደ ፈቃድ መያዝ ይጀመራል ። መስፈርት የሌላት ቤተ ክርስቲያን ወንጌል የያዙትን ገፍታ ሽጉጥ የያዙትን ታስቀራለች ። ሐዋርያው ወጥቶ ካድሬው ይሰነብታል ። አስተማሪው ወጥቶ ሕዝብ አጫዋች ይቀራል ። መስፈርት በሌላት አገር ሚኒስትሩን ካድሬ ያዘዋል ። ሊቁ ተሳዳቢ ተብሎ እንደ እብድ ይቆጠራል ፣  በተቃራኒ አዝማሪ ይገናል ። መስፈርት የሌላት አገር ልጆችዋ ላይ በር ቆልፋ ባዕዳንን ታቅፋለች ። መስፈርት የሌለው ዘመን ደፋርን ሊቅ ፣ ለፍላፊን ፖለቲከኛ ያደርጋል ። መስፈርት የሌለው አገልጋይ ጸሎተኞቹን ምእመናን ገፍቶ ባለጠጎችን ያቅፋል ። መስፈርት የሌለው ምእመን ዋጋ የሚከፍሉለትን አገልጋዮች ንቆ ቆዳውን በቁሙ የሚገሸልጡትን አራጆች ይከተላል ።

አዎ መስፈርት ቢኖረን ኑሮ የሚያከብሩንን ትሑታን ፣ የሚቆረሱልንን አፍቃሪያን ገፍተን አንሄድም ነበር ። መስፈርት ቢኖረን ኑሮ ጓደኛዬ ማነው? ብለን እኩያ ከመፈለግ ጓደኛ ልሆንለት የሚገባኝ ማን ነው ? ብለን የተጎዱትን እንፈልግ ነበር ። መስፈርት ቢኖረን ኑሮ የልጃችንን ዓለም አጥብበን በዘረኝነት አናሳድገውም ነበር ። መስፈርት ቢኖረን እግዚአብሔር ያለው ሁሉም አለው ብለን የእግዚአብሔርን ሰው እናከብር ነበር ። መስፈርት ቢኖረን ሊቃውንቱን አስቀምጠን እኛ አናወራም ነበር ። የሲኖዶስን ግብር ሰርቀን እኛ አናወግዝም ነበር ። መስፈርት ቢኖረን ከጊዜ ጋር አድመን እውነተኞችን ወኅኒ አንጥልም ነበር ። መስፈርት ቢኖረን ወንጌልን ከወንጀል እንለይ ነበር ። መስፈርት ቢኖረን ለሚያላግጡ እየከፈልን የሚያስተምሩትን አናስርብም ነበር ። መስፈርት ቢኖረን የፈረንጅን ሊቅ እየከፈልን የእኛን ሊቅ የአገሩን በር አንቆልፍበትም ነበር ። መስፈርት ቢኖረን ትሑቱን ልምጥምጥ ፣ አፍቃሪውን ምስኪን ፣ ታጋሹን ፈሪ ፣ ደጉን ሞኝ አንለውም ነበር ። መስፈርት ቢኖረን እንኳን ወንጌል የሥልጣኔ ፀሐይ ያልነካቸው ሰዎች አዋቂ ፣ ነቢይ ፣ ፈዋሽ እንሁን ሲሉን እናስተውል ነበር ። መስፈርት ቢኖረን ከሚያከብሩን መምህራን ወጥተን ፣ ዝናቸውን ለመካብ ዝናችንን ወደሚያፈርሱት ፣ የቪድዮ ነጋዴዎች አንሄድም ነበር ። የመገለጥን አምላክ የማጋለጥ አምላክ ወዳደረጉትን የምንነጕደው መስፈርት ስለሌለን ነው ።
መስፈርት የሌለው ሕይወት ሁልጊዜ ፍለጋ ላይ ነው ። መስፈርት የሌለው ወላጅነት ልጁን ዘመናዊነት አስጨብጦ መንፈሳዊነትን ያራቁታል ። መስፈርት የሌለው ማኅበር የተደባዳቢ ቡድን ይሆናል ። መስፈርት የሌለው አገር ጃርት ያበቅላል ። መስፈርት እስኪኖረን ገና ዋጋ እንከፍላለን ። አገር መለኪያ ከሌላት ወርቁም አይጠቅማት ።
ሐዋርያው ጳውሎስ መስፈርት እያስቀመጠ ነው ። ኤጲስ ቆጶስ የሚሆን ሊኖረው ስለሚገባ ብቃት ይናገራል ። እነዚህም በአጭሩ ለማስተማር እውቀት ፣ ለመምራት ሕይወት ያስፈልገዋል እያለ ነው ። እውቀትም ምግባርም የሌለው ከሆነ ከራሱ አልፎ የእግዚአብሔርን ቤት ያሰድባል ። አንድ አባት ሲናገሩ፡- “ላልተማረ ሰው ክህነት መስጠት ለእብድ ሰይፍ መስጠት ነው” ብለዋል ። ላልተማረ ክህነት ሕዝብን ፍጅ ብሎ ሰይፍ ማቀበል ነው ። “ከመጠምጠም ትምህርት ይቅደም” የሚባለው ለዚህ ነው ። ሐዋርያው ይህ መስፈርት ያስቀመጠው ምእመናን አገልጋዮችን እንዲለኩበት ፣ ይህ ይጎድላቸዋል እያሉ እንዲነቅፉበት አይደለም ። በእግዚአብሔር ቤት ሁሉም የራሱን ግዳጅ መወጣት አለበት ።
የመጀመሪያው መስፈርት የማይነቀፍ መሆን አለበት ። ባለፈው ዘመኑ ያልበደለ ወይም ነቀፋ ያለው ሥራ ያልሠራ ማለት አይደለም ። ያ ከሆነማ ጴጥሮስም ክዷል ፣ ጳውሎስም ቤተ ክርስቲያን አፍርሷል ። ንስሐ የገባና አሁን ባለው ቁመና የሚታይ ግድፈት የሌለበት ማለት ነው ። የማይታማ ማለት አይደለም ። የማይታማ ሰው አይደለም የማይታማ ግንብ የለም ። በርግጥም እንደ ቃሉ ለመኖር የሚጥር ሰው መሆን ይገባዋል ። ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ከሙያ ይልቅ ለቅድስና ያደላ ነውና ። በተለያዩ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ብሉያትን ሐዲሳትን በሙያ ደረጃ የሚያስተምሩ ፣ እነርሱ ግን የማያምኑ ሙስሊሞች አሉ ። የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ግን ሕይወቱ የቀና መሆን አለበት ። ያ ካልሆነ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዘንድ ነቀፋ ይደርስባታል ። የምእመናን ህልውናም አደጋ ውስጥ ይወድቃል ።
እግዚአብሔር ያግዘን ።
1ጢሞቴዎስ 34
ጥር 7 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ