የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መቃብር ያልያዘው እውነት – ክፍል 2

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ—- ረቡዕ ጥቅምት ፲፫ / ፳፻፮ ዓ/ም
መቃብር ያልቻለው
በዘመናት ሁሉ መቃብር አሸናፊ ሆኖ ኖሯል፡፡ ብዙ ነገሥትን ከነክብራቸው፣ ብዙ ጠቢባንን ከነጥበባቸው ውጦ አስቀርቷል፡፡ ነገሥታት ከሞት በኋላ ተነሥተው መግዛት፣ ጠቢባንም ከሞት በኋላ መጠበብ አልቻሉም፡፡ የኃይላቸውን ድካም፣ የጥበባቸውን ሞኝነት መቃብር አሳይቷቸዋል፡፡ ለዚህ ዓለም ኑሮአችን ሞት የድንበር ድንጋይ፣ የማይለፍ ወሰን ነው፡፡ ትልቁም ትንሹም ለዚህ የኑሮ ሥርዓት በእኩልነት ይገዛል፡፡ 5500 ዘመን መቃብር ይዞ ያስቀራቸው ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ መቃብር እንደ ሌሎቹ አስቀረዋለሁ ብላ የያዘችው ነገር ግን አቅቷት በሦስተኛው ቀን የተፋችው ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እርሱ መቃብር ያልያዘው እውነት ነው፡፡
የምንወዳቸውን፣ የምናከብራቸውን፣ መንገድ የመሩንን፣ የሕይወትን ሆሄ ያስጠኑንን ከሞት በኋላ አግኝተን ፍቅራችንን ብንገልጥላቸው ደስ ባለን ነበር፤ ነገር ግን አልቻልንም፡፡ ከሞት በኋላ ያገኘነው እስከ ዓለም ፍጻሜ አብሮን እንደሚኖር ቃል የገባልን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው (ማቴ.28፡20)፡፡ ሞት ያሳቀቃቸው፣ ወዳጆቻቸውን የነጠቀባቸው ይህን አሸናፊ ማን ያሸንፈዋል? ይላሉ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ግን ለሞት ሞትን የከፈለው ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በመነሣቱ ለሞትም ሞት እንዳለው ተገለጠ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ገዳዩን ገደለው፡፡ ከመቃብር አፋፍ፣ ከሲኦል ደጃፍ ላይ ቆመን፡«ሞት ሆይ  መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ?» (1ቆሮ.15፡55) ብለን ለመዘመር ያስቻለን የክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡
የሞቱትን ወዳጆቻችንን ከሞት ተነሥተው ብናገኛቸው በጣም እንወዳቸው ነበር፡፡ በጣም እንሳሳላቸው ነበር፡፡ የሞት ድንበር አጠገብ፣ የመቃብር አፋፍ ላይ ደርሰው የተመለሱትን ወዳጆቻችንን እንኳ «የሞት ትራፊ ወዳጄ፣ የእንደገና ልጄ ነው አትዩብኝ» እንላለን፡፡ ወደ ሞት ጉዞ ጀምረው የተመለሱትን በጣም እንወዳቸዋለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም በጣም እንወደው ዘንድ ከሞት የተነሣ ወዳጃችን ነው፡፡ በጣም እንንከባከበው ዘንድ፣ የቤችንን ወንበር ሳይሆን የልባችንን ዙፋን እንለቅለት ዘንድ ከሞት የተነሣው ወዳጃችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ትንሣኤን ሞት ይቀድመዋል፡፡ ሞት ባልተነገረበት ትንሣኤ አይነገርም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞተ፣ በሦስተኛውም ቀን ተነሣ (1ቆሮ.15፡3-4)፡፡ እኛም የትንሣኤውን ክብር ለመካፈል መሞት ያስፈልገናል፡፡ የሥጋ ሞት ሳይሆን ለእኔነታችን መሞት ያስፈልገናል፡፡ የሥጋን ሞት የምንሞተው በፈቃዳችን ሳይሆን በግድ ነው፡፡ በፈቃዳችን የምንሞትበት ረቂቅ ሞት እኔነታችንን መቅበር ነው፡፡ ክብሬ፣ ስሜ፣ ዘሬ፣ ቋንቋዬ፣ ችሎዬ፣ ብቃቴ፣ ዝናዬ፣ ሥልጣኔ ለምንለው ነገር መሞት ያስፈልጋል፡፡
አንድ በመንፈሳዊ ሕይወት የማልጠብቀው ወጣት ቀስቱን ወደ ራሱ እያመለከተ ሲናገር «ምስጋና ሁሉ ወደ እኔ ሲመጣ ሳይነካኝ ወደ ላይ አስተላልፈዋለሁ» አለኝ፡፡ ከዚህ ወጣት ሁለት ነገሮችን ተማርኩኝ፡
1እግዚአብሔር ከማይጠበቁት የማይጠበቅ እውነት እንዳለው፡እግዚአብሔር እንኳን በሰው በእንስሳትና በግዑዛን ሳይቀር ይጠቀማል፡፡ ነቢይን የገሰጸው በአህያ ነው (ዘኁ.22፡31-35)፡፡ በለዓም የገንዘብ ፍቅሩ አሳውሮት የተመዘዘውን ሰይፍ አላይ ሲል ከእንስሳዋም ሲያንስ እግዚአብሔር አህያይቱን በሰው ቋንቋ አናገራት፡፡ የቢታንያ ድንጋዮችም ሰው ለምስጋና ዝም ቢል እንዝም እንደማይሉ ተናገረ (ሉቃ.19፡40)፡፡ ሌሊት ሌባ ሲገባ ውሻው ይጮኻል፡፡ የውሻው ጩኸት አትስረቅ የሚል ነው፡፡ ሰው የተባለው ሲሰርቅ ውሻ መጮኹ ይገርማል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በማይጠበቁት ሰዎችም እውነትን እንደሚያስተላልፍ ተማርኩ፡፡
2ሰዎች የምስጋናን አድራሻ ተሳስተው ወደ እኛ ሲያመጡ ለምስጋናው ባለቤት መሸኘት እንደሚያስፈልግ ተማርኩ፡፡ የብርታታችን ምሥጢሩ እግዚአብሔር ነውና ምስጋናን እንደ ኒሻን መደርደር፣ እንደ ማዕረግ በትከሻችን ላይ አኑሮ መንጎማለል የስርቆት ወንጀል ነው፡፡ ራሳችንን ማድነቅ ብቻ ሳይሆን ሰዎች ሲያደንቁንም ውጠን ማስቀረት አልተፈቀደልንም፡፡ ምስጋና፣ ክብር፣ ለእግዚአብሔር ነው፡፡ እኛ የጀመርነው ምን አለ? እኛ የፈፀምነውስ ምን አለ? መጀመሪያ ሳይኖርበት ሁሉን የጀመረ፣ መጨረሻ ሳይኖርበት ሁሉን የፈጸመ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ምስጋና ሁሉ ለእርሱ ይገባል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ለእኔነት መሞትን ይጠይቃል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ሞተ?
(ይቀጥላል)
መቃብር ያልያዘው እውነትመጽሐፍ
በዲ/ አሸናፊ መኰንን
የመጀመሪያ እትም ሚያዝያ 2000 /
አድራሻ፡ 0911 39 3521/0911 67 8251
 ...  62552
 አዲስ አበባ.

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።