“እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።” ናሆም 1፡3 ።
በተዘጋው መንገድ የምትሰጥ ፣ በጦርነት ውስጥም ልብን በሰላም የምትጠብቅ ፣ የሚያሳልፉ ቀኖችን የምታሳልፍ ፣ አበቃልኝ ያሉትን እንደገና የምታስጀምር ፣ በትቢያ የወደቁትን የምታነሣ ፣ ማቅ የለበሱትን ወርቅ የምታለብስ ፣ ዋጋ የላቸውም የተባሉትን ባለ ዋጋ የምታደርግ ፣ ሁሉም ነገር ጨለመብኝ ለሚሉት ንጋት የምትሰጥ ፤ ስትሰጥ የማትሰስት ፣ ስታፈቅር የማትጠላ ፣ ስትገኝ የማትታጣ የሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ አመሰግንሃለሁ ። በባሕር የሚቀብረውን ወጀብ ፣ ያለ ረዳት የሚያስቀረውን ማዕበል ፣ ወደብ ፈላጊውን መሐል ባሕር ላይ የሚያስቀረውን መዓት የምትገሥጽ ፣ መርገጫ ላጣ መሬት የምትሰጥ ፣ ዕረፍት ላጣ ዕረፍት የምትሆን ፣ አቅጣጫ ለጠፋው መንገድ የምታመላክት አንተ ነህ ። ካፒቴን የለቀቃትን መርከብ መርተህ የምታደርስ ፣ ሁሉ ራሱን ሲያድን ደካሞችን በብልሃትህ የምትሰውር ፣ አቅም ያለው ሲሞት አቅም የሌላቸውን ሕፃናትና አረጋውያን የምትታደግ ፣ ነቅተንም ተኝተንም የምትጠብቀን አንተ ቡሩክ ነህ ። መደሰቻው ባሕር ማልቀሻ ፣ ማለፊያው ባሕር መስጠሚያ ሲሆን የተጨነቀችን ነፍስ አድነህ የምስጋና ዘመን የምትጨምር አንተ ነህ ። የስንብት ደብዳቤ የሚጽፈውን ዳግመኛ በምድር ላይ አልረግጥም የሚለውን ደብዳቤውን ሰርዘህ ፣ ሞቱን ገድለህለት እንደገና የምታኖረው አንተ ነህ ። ቅዱስ መባልህ ግብርህ ልዩ ስለሆነ ፣ ሥራህም ስለማይመረመር ነው ።
መነሻ መድረሻው እስኪጠፋው በማዕበል የተጨነቀውን የምታድን ፣ የመንገድ መሪ ሰጥተህ የብዙዎች አባት የምታደርግ አንተ ነህ ። የየብሱ አምላክ የባሕሩም አምላክ ነህ ። በየብስ በባሕር መርዳት ትችላለህ ። ዛሬም አልደከመህም ፣ ዛሬም ሕያው ሁነህ ትሠራለህ ።
ከባሕሩ ወጀብ ብቻ ሳይሆን ከየብሱ ዐውሎ ነፋስ የምታድን አንተ ነህ ። ሰውን ሁሉ የሚያቀለውን ፣ ትቢያ በዓይን የሚጨምረውን ፣ መሬትን የሚያውከውን ብርቱውን ነፋስ የምትገሥጽ አንተ ነህ ። የሚንገዳገደውን የምታጸና ፣ ምን ልያዝ ለሚለው ምሰሶ የምትሆን አንተ ነህ ። የታወከውን መንደር የምታረጋጋ ፣ የፈረሱ ትዳሮችን የምትሠራ አንተ ነህ ። ከሃሊነትህ መመኪያችን ፣ ፍቅርህ ጥላችን ፣ በረከትህ ሙላታችን ፣ ቃልህ መሪያችን ይሁንልህ ። በብዙ የረዳኸን ልጆችህ ምስጋና ይዘን መጥተናል ተቀበለን ። አሁንም በወጀብና በዐውሎ ውስጥ መንገድ አለህ ፤ ደመናንም ትቢያ አድርገህ በከፍታ ትራመዳለህ ። ለችሎታህ ምስጋና ይሁን ። የሚሰማም ሁሉ አሜን ይበል ።