የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መንገድ አለው/ ክፍል ሁለት

                                                                                 ረቡዕ ሐምሌ ፰/ ፳፻፯ ዓ/ም

“አሁንም ያዕቆብ ሆይ÷ የፈጠረህ÷ እስራኤልም ሆይ÷ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል”   (ኢሳ.43 ÷1)
እግዚአብሔር  የሚናገር አምላክ ነው፡፡ የአሕዛብ ጣዖታት አፍ አላቸው አይናገሩም፡፡ እግዚአብሔር ግን ለልጆቹ ቃል አለው፡፡ የማጽናናት ቃል፣ የሰላም ቃል፣ የፈውስ ቃል አለው፡፡ እግዚአብሔር ሕያው ነው፡፡ ከምንልበት ነገር አንዱ የሚናገር አምላክ በመሆኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር  ለጥቂት ሰዎች፣ ለባለጠጎችና ለዕውቀት ሰዎች ሳይሆን ለሕዝብ ሁሉ ይገደዋል፡፡ በአንድ አውሮፕላን ውስጥ ሁለት መቶ መንገደኞች ቢኖሩ አንድ እውቅ ሰው በመካከላቸው ቢኖርና አደጋ ቢደርስ ሲነገር የሚውለው ስለ አንዱ ታዋቂ ሰው ነው፡፡ ዓለም የምትናገረው ለጥቂት ሰዎች ነው፡፡ የዓለም መርህም ብዙዎች ለጥቂቶች የሚኖሩበት እንጂ ጥቂቶች ለብዙዎች የሚኖሩበት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁሉን በእኩል ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር አይናገርልንም ነገር ግን ይናገረናል፡፡
“ያዕቆብ ሆይ”  “እስራኤልም ሆይ” እነዚህ ሁለት ስያሜዎች የይስሐቅ ልጅ ስያሜዎች ናቸው፡፡ ያዕቆብ በሌላ ጊዜ እስራኤል ይባላል፡፡ 12ቱ ልጆቹ እስራኤልን የመሠረቱ የነገድ አባቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ዘሮቻቸውና አገራቸው በያዕቆብ ስም እስራኤል ሌላ ጊዜም ያዕቆብ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ያዕቆብ ታሪኩን ስናየው የኑሮ አሳብ እጅግ የታከተው፣ በአቋራጭ መንገዶችም የደከመ ሰው ነው፡፡ ዘሩም በእርሱ መንገድ የሄዱ ይመስላል፣ እግዚአብሔር ግን ከኑሮ ፍርሃትም ያድናል፡፡ እግዚአብሔር መንግሥት ነውና ዋስትና ይሰጣል፡፡ የመኖር ዋስትናችን በጌታችን እጅ ነው፡፡ ታዲያ የሚያስፈራው በሰው እጅ ያለ ነገር ነው፤ በእግዚአብሔር እጅ ያለ ዋስትናው የፀና ነው፡፡

እግዚአብሔር የማጽናናት ቃል አለው፡፡ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን የምሥራች ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ጌታችን በተወለደ ጊዜ በመላእክት የታወጀው አዋጅ፡- “እነሆ÷ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ” የሚል ነው (ሉቃ. 2÷10)፡፡ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን የምሥራች የያዘ ንጉሥ በዓለም ላይ የለም፡፡ ንጉሥን ደህናው ሲጠላው ባለጌው ያመሰግነዋል፤ ጨዋው ሲመርቀው ሌባው ያማርረዋል፡፡ እስከ ዛሬ ሁሉን የሚያካትት ደስታ ባንድ ጊዜ አልተገኘም፡፡ የካንሰር መድኃኒት ቢገኝ ሁሉን የሚያካትት ደስታ አይደለም፡፡ በልቼ ብሞት ይሻለኛል የሚል ረሀብተኛ አለ፡፡ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን የምሥራች የተወለደው ሕፃን ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሁሉ ደስታ ነው፡፡ ደስታም እርሱ ብቻ ነው፡፡  

ስለ እኛ እኛ ከምንናገረው የሠራን ቢናገር ይሻላል፡፡ በዚህ ክፍል ላይ፡- “አሁንም ያዕቆብ ሆይ÷ የፈጠረህ እስራኤልም ሆይ÷ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” (ኢሳ. 43÷1)፡፡ የፈጠረህ፣ የሠራህ ይላል፡፡ የሰው ልጅ በዚህ ዓለም ላይ ወላጆች እንጂ ሠሪዎች የሉትም፡፡ ሠሪው አንዱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ፈጣሪም የሰማዩ አምላክ ነው፡፡ መልእክቱ እየመጣ ያለው ሰው ከታነፀበት ከዋናው ተቋም ነው፡፡
አንድን ዕቃ እንደ ምሳሌ ብንወስድ ዕቃው ሠሪ አለው፣ ቀጥሎ ሻጭ አለው፤ በሦስተኛ ደረጃ ገዥ አለው፡፡ ስለ ዕቃው ምንነት በደንብ መናገር የሚችለው ሠሪው ነው፡፡ ነጋዴው ግን ያ ዕቃ ከእጁ እንዲወጣለት የሚናገረው ሐሰተኛ መረጃ ነው፡፡ ገዥውም በጥንቃቄ ይጠቀምበታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የእኛ ሠሪ፣ በማዳን የእኛ ገዥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእጄ በወጡ የሚለን ነጋዴ አይደለም፤ ከማኅፀን እስከ ሽበት ሲሸከመን የማይሰለቸው ነው፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ፡- “እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ÷ የእስራኤልም ቤት ቅሬታ ሁሉ÷ ከሆድ ያነሣኋችሁ ከማኅፀንም የተሸከምኳችሁ ስሙኝ፡- እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ እኔም አነሣለሁ፤ እኔ እሸከማለሁ እኔ አድናለሁ” ብሏል (ኢሳ. 46÷3-4)፡፡
ዛሬ ለመጽናናት የሚሆን መልእክት እየመጣ ያለው ከሚያውቀን ወይም ከሚወደን አይደለም፡፡ ከሠራን የራሱም እንድንሆን በደሙ ከገዛን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ ሠሪ አለንና ከየት እንደመጣን እናውቃለን፡፡ ትጠቅማላችሁ ብሎ ገዝቶናልና ዋጋ አለን፡፡ ያልሠራን ሰይጣን መነሻና መድረሻ የለህም ይለናል፡፡ ያልገዛን ጠላት ዋጋ የላችሁም ይለናል፡፡ እኛ ግን ልናደምጥ የሚገባን የፈጣሪያችንንና የገዢያችንን ድምፅ ብቻ ነው፡፡
ብዙ ምሁራን፣ ጠቢባን፣ ሐኪሞች፣ አሳዳጊዎቻችን ስለ እኛ የተናገሩት መልካም ላይሆን እንደውም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በኋላ ዋጋ የላችሁም፣ አትረቡም፣ የእናንተ ጉዳይ መፍትሔ የለውም ብለው በቁማችን ቀብረውን ይሆናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሊናገሩ የሚችሉት ይህን ብቻ ነው፡፡ ሠሪያችን ግን የሞተውን ወደ ሕይወት፣ የሌለውንም ወደ መኖር አመጣዋለሁ ይለናል (ሮሜ. 4÷ 16-17)፡፡ አካላችንን መጠገን ብቻ ሳይሆን እንደ አልዓዛር ከመቃብር ሊያወጣን ይችላል፡፡ ትምህርታችንን መግለጽ ብቻ ሳይሆን ማንም ያልደረሰበትን አዲስ ዕውቀትን ሊሰጠን ይችላል፡፡ የከዱንን የሚመስሉ ከእነርሱም የሚልቁ በነፍሳቸው ያጌጡ ትሑታንን ያመጣልናል፡፡ ከተሠራንበት ተቋም የሚመጣው ድምፅ ይህ ነው፡፡ ሌላው ድምፅ የመንገደኛ ድምፅ ነው፡፡ የሞት ድምፅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ለሕይወት ይናገረናል፡፡ ቢመሽም እንደገና በእርሱ ቀትር ይሆናል፡፡ ክረምትን በበጋ፣ ሌሊትን በቀን መለወጥ እግዚአብሔር ይችላል፡፡ በፍጹም ተስፋ የለሽ ድምፆችን በመስማት ሰይጣንን ደስ ልናሰኝ አይገባንም፡፡ የምሥራች ተወልዶልናል፡፡
እግዚአብሔር ተናገረ ማለት አደረገ ማለት ነው፡፡ የሰዎች ንግግር የተግባር ምትክ ሊሆን ይችላል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን የተግባሩ መያዣ ነው፡፡ እግዚአብሔር  በምንም አይያዝም ኃያል ነውና፤ እግዚአብሔር ግን በቃሉ ይያዛል፡፡ እርሱ የተናገረውን ሊፈጽመው ይተጋል፡፡ የተናገረው ከሚቀር ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል፡፡ የሰጠውን ተስፋ ለማጠፍ ማንነታችንን አያይም፣ በራሱ ፍቅር ላይ ተመሥርቶ ወዶናልና፡፡ ተስፋውን ለማጠፍ አይቆጭም፤ እግዚአብሔር አይጎድልበትምና፡፡ ተስፋውን ለመፈጸም አቅም አነሰኝ አይልም፣ ለእርሱ የሚርቅ ዳርቻ የለምና፡፡ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፡፡ ታማኙ ጌታ፡- “ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ÷ አንተ የእኔ ነህ፡፡ በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ÷ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም÷ ነበልባሉም አይፈጅህም” ይለናል (ኢሳ. 43÷1-2)፡፡
                                                 – ይቀጥላል-

 

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ