የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መንገድ አለው / ክፍል አምስት

ሰኞ ሐምሌ ፳ / ፳፻፯ ዓ/ም
“አንተ የእኔ ነህ”/ኢሳ. 43፡1/
አሁን በሆንነው ማንነት የመዘኑን፣ እንዲሁ እንደሆንን የምንቀር መስሏቸው የንቀት ቃል ያወረዱብንን ሰዎች ስናስብ ልባችን አንዳንድ ጊዜ በሀዘን ሌላ ጊዜ በደስታ ይነካል፡፡ የምናዝንበት ምክንያት እነዚህ ሰዎች በአሳላፊው ጊዜ በአደላዳዩ ንጉሥ፣ ጽዋ በሚሰጠው ጽዋ በሚነጥቀው የበላይ ጌታ እንዴት አላመኑም ብለን ነው፡፡ ልባችን በደስታ የሚሞላው ደግሞ እግዚአብሔር የንቀቱ ጽዋ ሲሞላ እንደሚሠራ በማመን ነው፡፡ አሁንም የሆንነው መጨረሻችን አይደለም፡፡ መጨረሻችን አላዋቂ፣ ምስኪንና ተስፈኛ መሆን አይደለም፡፡ ፍጻሜአችን በጌታ እጅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምኞታችንን ሳይሆን እርምጃችንን ይባርካልና ዛሬ መንቀሳቀስ እንጀምር፡፡ ጸሎት የጥረት ምትክ ሳይሆን የጥረት ኃይል መሆኑን ማሰብ አለብን፡፡ እግዚአብሔር ዋጋ የላችሁም ለተባሉ ሰዎች ዋጋ ይሆንላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ዋጋ የሆነላቸው ዋጋቸው አይዋዥቅም፣ እንደ ተወደዱ ይኖራሉ።
የሩቅ ዘመዳችን ሥልጣን ላይ ሲወጣ የራቀውን ዝምድና አቅርበን እርሱ እኮ ወንድሜ ነው እንላለን፡፡ ለምን? ቢባል ክብሩ ክብራችን እንደሆነ አስበን ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በድህነት ጨርቁ የተቀደደውን፣ መልኩ የተጨማደደውን የቅርብ ዘመዳችንን አላውቀውም ብለን እንክዳለን፡፡ የገዛ እናታቸውን የካዱ ስንት ትልልቅ ሰዎችን እናውቃለን፡፡ መምጫውን የረሳ ትልቅነት ትልቅነት ባይሆንም። እግዚአብሔር ግን አያፍርብንም፡፡ 

የለመድነው በማያስቀው ወሬ ለባለጠጎች መሳቅ፣ የድሆችን ቁምነገር ማጣጣል፣ ላለው ማጎብደድ ለሌለው ደግሞ የሚያውቀውን ድህነቱን ሳናሳውቀው መዋል ነው፡፡ ነገር ግን የሁላችንም መጨረሻ የአሁኑ አይደለም፣ ስለዚህ አሁን ያለው የመሰለው ያጣል፣ የሌለውም ያገኛል፡፡ እግዚአብሔር በዙፋኑ የተቀመጠው እንዲሁ ለጌጥ ሳይሆን ይህን ሊያደላድል ነው፡፡ 

የኢየሩሳሌም ነፋስ አሥራ ሁለት ነው እንደሚባለው የሰውም ጠባይ በቀኑ ውስጥ ተለዋዋጭ ነው፡፡ ሰውን በቤት አድራሻው ማግኘት ይቻል ይሆናል፣ ጠባዩ ግን አድራሻ የለውምና ማግኘት ይከብዳል፡፡ በዚህ ምክንያት ሰውን የእኔ ማለት ከሚያስፈሩ ነገሮች አንዱ ሆኗል፡፡ ይልቁንም ባለንበት ዘመን ሁሉም ነገር ለመለዋወጥ ይቸኩላልና ከወዳጅ ጋር ማርጀት እየከበደ መጥቷል፡፡ መቼም ዘመኑ ያው ነው፣ ይመሻል ይነጋል የጎደለው ነገር የለም፡፡ እኛ ግን ያው አይደለንም፡፡ ሁልጊዜ የምንቆጥረው ስላቆሰሉን ሰዎች ነው። ስላቆሰልናቸው ሰዎች ቆጥረን አናውቅም፡፡ እኛንም ሌሎች የእኔ ማለት አስቸግሯቸው ይሆናል፡፡ 
ሰውን የእኔ ለማለት ትልቅ ድፍረት ይጠይቃል፡፡ ይኸውም ሰው የእግዚአብሔር ነው፡፡ የፈጠረውና የሞተለት ባለመብቱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰውን የእኔ ሲል የሚያምርበት እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን የእኔ የሚለው የይቅርታ ዕድልም ስለሚሰጥ ነው፡፡ እኛ የምንመራበት መመሪያ “ብርሌ ከነቃ አይሆንም ዕቃ” የሚል ነው፡፡ እግዚአብሔር በሸክላ ሠሪው እጅ እንዳለው ሸክላ የተበላሸውን እንደገና ይሠራዋል፡፡ እኛ ለሰዎች ጽድቅን ብንነግራቸው እንጂ አናጸድቃቸውም፡፡ አጽዳቂው ጌታ ግን ስለሚለውጣቸው የእኔ ይላቸዋል፡፡ እውነተኛ ፍቅር ያለው ከይቅርታ በኋላ ነው፡፡ የእኔ ብለን ለመጥራትም ይቅርታን መሞላት ያስፈልጋል፡፡ 
ሰዎች ከእኛ ጋር ያላቸው ግንኙነት መስመሩ አንድ ነው፡፡ አለቃችን መስመሩ የአሠሪነት ነው፡፡ አስተማሪያችን መስመሩ የትምህርት ነው፡፡ ጓደኛችን መስመሩ የመዋደድ ነው፡፡ የትዳር አጋራችን መስመሩ የኑሮ ነው፡፡ መንግሥት መስመሩ የገዢነት ነው፡፡ ሥራችንን ስንለቅ ከአለቃችን፣ ትምህርት ስንጨርስ ከመምህራችን፣ ስንጣላ ከጓደኛችን፣ ሰማንያ ሲቀደድ ከትዳራችን፣ ሞት ሲመጣ ከልጃችን፣ አገር ስንለቅ ከመንግሥታችን እንለያያለን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን መስመር ግን የማይቆጠር፣ በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይም ነው፡፡ ተኝተን ስንነቃ ቤተሰቦቻችንን እናያለን፡፡ ሞተን በሰማይ ስንቆም ግን እግዚአብሔርን እናየዋለን፡፡ ስለዚህ እኛ የእርሱ ነን፡፡ 
የሰው ሁሉ ፍጻሜው እግዚአብሔር ነው። “ውሎ ውሎ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከሞት አይቀርም” እንደሚባለው ከዚያ በላይ አንድ ቀን በፊቱ መቆማችን አይቀርም፡፡ ዛሬ ልንሸሽ እንችላለን፡፡ የፍቅር ጥሪውን መሸሽ ይቻላል፡፡ ፍቅር ነጻነት ነውና፡፡ የፍርድ ጥሪውን ግን መሸሽ አይቻልም፡፡ ፍርዱ ሰማይና ምድርን ይገዛልና፡፡ አዎ የሰው ሁሉ ፍጻሜው እግዚአብሔር ነው፡፡ አረጋውያን ሲቆርቡ፣ ወኅኒ የወረዱ ንስሓ ሲገቡ፣ የታመሙ ቄስ ሲያስጠሩ፣ ብዙ የዘፈኑ መዝሙር ሲያወጡ… የሰው ሁሉ ፍጻሜው እግዚአብሔር እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
አንድ የታወቁ ባላባት ነበሩ፡፡ ባሪያቸውን ድረውት በግቢአቸው ውስጥ ቤት ሰጥተውት፣ ሀብት አካፍለውት መኖር ጀመሩ፡፡ አንድ ቀንም ያ ባሪያ ከእርስዎ አላንስም ለማለት፡- “ያለኝን ሀብት ልንገርዎ” አላቸው። “አዎ” አሉት፡፡ ይህ፣ ይህ አለኝ አላቸው፡፡ እርሳቸውም የእኔን ሀብት ደግሞ ልንገርህ አሉት፡፡ “አዎ” አለ፡፡- “መጀመሪያ አንተ ቀጥሎ ያንተ የሆነው ሁሉ” አሉት ይባላል፡፡ ኪሳችን ሲሞላ ሀብታችን ሲደረጅ እግዚአብሔር የማያስፈልገን ይመስለናል፡፡ አለኝ በቃ ጸሎት ድሀ ይጸልይ ማለት እንጀምራለን፡፡ ነገር ግን እንኳን የእኛ የሆነው ሀብት ራሳችንም የራሳችን አይደለንም፡፡ ራሳችንም የእግዚአብሔር ነን፡፡ 
በነቢዩ በኢሳይያስ፡- “ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ አንተ የእኔ ነህ”ብሏል፡፡ (ኢሳ.43÷1)፡፡ መቤዥት መግዛት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ በተፈጥሮ ዋጋ ዳግመኛ በልጁ የደም ዋጋ ተቤዥቶናል፡፡ በሁለት ዋጋ ወይም በድርብ ዋጋ የእግዚአብሔር ሆነናል፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ሲፈጥረን ዳግመኛም ሲያድነን የራሱ ሆነናል፡፡ አሁን ያለነው በነጋዴው እጅ ሳይሆን በገዢው እጅ ነው፡፡ ነጋዴው ዕቃውን መቼ ከእጄ በወጣ እያለ ስእለት ይሳላል፡፡ ገዢው ግን ማንም ከእጄ አይነጥቃቸውም እያለ ይንከባከበናል፡፡ ለምንኖርበት ቤት ሁለት ካርታ ቢኖረን የእኛ ለማለት ትልቅ መተማመን አለን፡፡ ስለይዞታቸው የሚናገሩ ሰዎች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በደርጉም ይኸው ያለኝ መረጃ ሲሉ አፋቸው ሙሉ ነው፡፡ እግዚአብሔርም የእኔ ናቸው ሲለን በድርብ ዋጋ ገዝቶን ነው፡፡ 
ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ”(1ቆሮ. 6÷19-20) ብሏል፡፡ 
ሥጋችን ከእግዚአብሔር በአደራ የተቀበልነው እንጂ በባለቤትነት የያዝነው አይደለም፡፡ ከራሳችን ንብረት ይልቅ የአደራ ንብረት ጥንቁቅ ያደርጋል፡፡ ቢጠፋ መክፈል ስለማንችል ብቻ ሳይሆን ታማኝነትን ማጉደል ያስፈራናል፡፡ የራሳችን ቢጠፋ እንመርጣለን፡፡ ሥጋችንም እንዲሁ በዝሙት የምንጥለው ሳይሆን በንጹሕ ላስረከበን ጌታ በንጽሕና የምናስረክበው የአደራና የእግዚአብሔር ንብረት ነው፡፡ 
ይልቁንም ክርስቶስ ስለ እኛ ሲሞት ሥጋችን ቤተ መቅደስ እንዲሆን ተገዛ፡፡ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ነው፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር በሰሎሞን ወይም በዘሩባቤል መቅደስ ሳይሆን የሚከብረው በሰውነታችን መቅደስ ነው፡፡ በተደጋጋሚ እንደተነገረው ልዑል የሰው እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም/የሐዋ. 7፡48፤17፡24/፡፡ ልዑል የሰው እጅ በሠራው መቅደስ ካልኖረ የሚኖረው የራሱ እጅ በሠራው መቅደስ በሰው ልጅ ላይ ነው፡፡ 
ቤተ መቅደስ ሁለት ነገሮችን ይፈልጋል፡፡ የመጀመሪያው ንጽሕና ሁለተኛው ፀጥታ ነው፡፡ እንዲሁም በሰውነታችን መቅደስ ከኃጢአት መራቅ እንዲሁም ከጭንቀት ራሳችንን መጠበቅ አለብን። እግዚአብሔር ዋጋ ከፍሎብናል። ዋጋ ከከፈለብን አይጥለንም። ዋጋ ከከፈለብንም እኛ የእርሱ ነን። ለብዙ ዘመናት እኛ የራሳችን፣ እኛ ዓለም፣ እኛ የሰይጣን ነበርን። አሁን ግን አለማወቃችን እንደ ትላንት ካለፈ እኛ የእግዚአብሔር ነን።
“ውዴ የእኔ ነው እኔም የእርሱ ነኝ” /መኃ. 2፡16/ ይላል። ትልቁ የእምነት ምላሽ የእኔ ናችሁ ላለን ጌታ ያንተ ነኝ ማለት ነው። ራሳችንን በኮንትራት ሳይሆን ዳግም የእኔ ላንለው ለጌታችን ልናስረክብ፣ የእርሱ የክብር ዕቃዎች ልንሆን ይገባል። የእርሱ ባንሆን የምንሆነው ለጥፋት ነው። የእርሱ መሆን ትልቅ ደስታ ነው። እግዚአብሔር አባወራ የሆነበት ሕይወትም በሰላም የተሞላ ነው። በዓለም ላይ ሰዎች የራሳቸው ወይም የእግዚአብሔር ናቸው። የእግዚአብሔር ከሆኑ በኋላም መልሰው የራሳቸው የሆኑ ብዙዎች ናቸው።
 ይህች ቀን ግን የቃል ኪዳን ማደሻ ዕድል ናትና እናንተ ኮብላዮች ወደ ቀደመው ትዳራችሁ ወደ ትልቁ ጌታ እልፍኝ እንደገና ግቡ። የእርሱ የሆናችሁም ዓለም አላመለጣችሁም አልከሰራችሁምና እርሱን በማመን ጽኑ። ከእርሱ ርቃችሁ የምትኖሩም ዛሬ ብትሸሹት አንድ ቀን በማትሸሹት በሞት ሠረገላ ተጭናችሁ ከፊቱ ትቆማላችሁና ተመለሱ።
                                  በእውነት እኛስ የእርሱ ነን?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ