የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መካሪ አታሳጣን

“ገላጋይ አጥቼ ግልገሌን በላኋት ።”

ሕይወትን ወደ ኋላ ዞር ብለን ስንመለከት ሁለተኛ ዕድል የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን ። እርሱን የበደልነውን ያህል ሰዎችን ብንበድል ኖሮ ገሃነመ እሳትን ቢሰጡን እንኳ አይረኩም ነበር ። ብዙ ፍቅር ሰጥተናቸው ፣ ብዙ መልካም ነገር አብረናቸው አሳልፈን በአንድ ንግግር የሚለዩን ይኖራሉ ። ብዙ ዓመት ስቀንላቸው አንድ ቀን በራሳችን ጉዳይ ስናኮርፍ “የሰው ፊት እሳት ነው” ብለው ሊሸሹን ይችላሉ ። እግዚአብሔር ግን ያለማቋረጥ እያሳዘነው ያለማቋረጥ ይወደናል ። ችግራችንን ሳይሆን ችግራችን የመጣበትን ችግር እያየ ይራራልናል ። ሁልጊዜም ተስፋ ያደርገናል ። በእኛም ደስ ይለዋል ። ትእዛዙንም የሰጠን ስለሚተማመንብን ነውና ያከብረናል ። ዛሬን የመጨረሻ ግንኙነት በማለት አይጠራውም ፣ ስህተትን ዘላቂ ጠባያችን አድርጎ አይመለከተውም ። እርሱ የማያቋርጥ ዕድልን በመስጠት የታወቀ ነው ። ታዲያ በዚህ ጥቅጥቅ ባለው የሕይወት ደን ውስጥ የሚታወሱን ጸጸቶች አሉ ። ለምን እንዲያ ሆነ ? ለምን እንዲህ አደረግሁ ? የምንልባቸው ነገሮች አሉ ።

ወዳጆቻችን በየዘመናቱ የፈኩ ከዋክብት ናቸው ። ድንገት ጭልም የሚሉት ግን በእነርሱ ደካማነት ብቻ ሳይሆን በእኛም ትዕግሥት ማጣት ነው ። ወዳጆች የመጀመሪያ ቀን ያሳየናቸውን ሁልጊዜ ይፈልጉታል ። “አታስለምድ አታስቀር” ይባላል ። ካስለመዱ መቀጠል ይገባል ። ካስቀሩ ቅሬታ ያመጣል ። በዓይናችን የምናያቸውን ወዳጆች በጆሮአችን መገምገም አይገባንም ። ከጆሮ ዓይን ይበልጣል ። እነርሱ ፈቅደው ውስጣቸውን ካልገለጡልን በቀር ስለ እነርሱ ጥልቅ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ አይደለም ። እግዚአብሔር የሰጠን አቅም የሌሎችን ጓዳ ለመሰርሰር የማይተርፍ ነው ። ዘላቂ ግንኙነት ደስ ይላል ። ፍቅር ግን የጋራ በመሆኑ ልሂድ ያለውን ማቆም አይቻልም ። ደግሞም በልቡ ሂዶ በአካል ከቀረ ሰው ጋር መኖር ሬሳ ታቅፎ እንደ መኖር ነው ። አንዳንድ ወዳጆቻችን በጣም ቀናዎች ነበሩ ። ፍጹምነትን ስንፈልግባቸው መልካምነታቸውን እንደ ክፋት አየነው ። በዚህ ምክንያት ገፋናቸው ። አንዳንድ የትዳር አጋሮች በጣም መልካሞች ነበሩ ። በሰው ወሬ ፣ ትዳራችንን ከጎረቤት ትዳር ጋር በማነጻጸር ቤታችንን አፈረስነው ። አለመውለዳችንን እንደ ርግማን ፣ ሀብት አለመያዛችንን እንደ ትዳር ውድቀት አየነው ። ያወሩልን ምነው ባስታረቁን ፣ ሰብቅ የነገሩን ምነው ዝም ባሉን ኖሮ ብለን ዛሬ ላይ እንቆጫለን ። ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ሳሉ የወንድና የሴት ችሎታ አደረግናቸው ። የሀብት ጥያቄም ፍቅርን ካፈረሰ ትዳሩ ሸቀጥ እንጂ ትዳር አልነበረም ። ቢሆንም ምነው ዘመዶቼ ተዉ ፣ ተዪ ባሉኝ እንላለን ። ምነው የሃይማኖት አባቶቼ በገሠጹኝ ኖሮ ብለን እንቆጫለን ።

ወታደር የሚማርክ ነገር አለው ። ዋስትና የሚፈልጉ ወታደር ማግባትን ይወዳሉ ። ወታደር ሥነ ሥርዓቱ ፣ ለአለቃው መገዛቱ ፣ ሕይወቱን ለአገር መስጠቱ ፣ ቆራጥነቱ ደስ ይላል ። ዘላለም ሞልቃቃ ሁኖ ከመኖር እንደ ወታደር ለአንድ ቀን ቆራጥ መሆን ብዙ ታሪክ ይለውጣል ። ደስታንም ይሰጣል ። ልጅን ለወታደርነት ማብቃት ይቻላል ። እንደ ወታደር አድርጎ ማሳደግ ግን አይቻልም ። ምክንያቱም ወታደርነት ምርጫም ፈቃድም ነው ። ልጅ መሳሳቱ ትምህርት ቤቱም ነው ። ቆሞ ከመሄዱ በፊት ብዙ ሺህ ጊዜዎች ይወድቃል ። ትክክል ከማሰቡ በፊት ብዙ የስህተት አሳቦችን ያስባል ። መሳሳት ካልተፈቀደለት ልጅ ሊታነጽ አይችልም ። ልጆቻችን እንደ ራሳቸው እያደጉ ሳለ የአገሩን ልጆች በማየት ጭቆና ማድረግ ፣ በዱላም ትክክለኛውን መንገድ አሳያለሁ ብሎ መነሣት ፣ የግል ንዴታችንን ልጆቻችን ላይ መወጣት ተገቢ አይደለም ። ከልክ በላይም ማድረግ ፣ ከልክ በታችም መጨቆን በልጆች ላይ የምንፈጽመው በደል ነው ። መውለድን ስናስብ ኃላፊነትንም አብሮ ማሰብ ይገባል ። በዕድሜ የገፉት ልጅ ስንወልድ ከአያያዝ ፣ ከአስተጣጠብ ጀምሮ ያሰለጥኑናል ። ስለ አስተዳደግም መጠየቅ ያስፈልገናል ።

“ገላጋይ አጥቼ ግልገሌን በላኋት” ይባላል ። ገላጋይ አስፈላጊ ነው ። አንድ ቀን የእብድ ሥራ መሥራታችን የማይቀር ነውና ገላጋይ ያስፈልገናል ። ለገላጋዩም አንድ ቀን ገላጋይ እንሆንለታለን ። ዛሬ ብንታመም አስታማሚ እናገኛለን ፣ አስታማሚአችንን አንድ ቀን እናስታምመዋለን ። በየተራ እንድንቸገር አድርጎ ሕይወትን ያዋቀረ እጅ ቡሩክ ነው ። ሁሉም በአንድ ጊዜ ሲቸገር ከባድ ነው ። ግልግልን አርዶ መብላት ሥጋው ለስላሳ ነው ። አንድ ቤተሰብን ግን የማያጠግብ ነው ። ለዕለት ከፊል ደስታን ይሰጣል ። ነገን ያለማየት ውጤት እንደሆነ ግን አዋቂ ሁሉ ይረዳዋል ። ግልገልን ለማረድ ቢላዋ ሲስል ገላጋይ ከመጣ ይገሥጸዋል ። ያቺ ግልገል ብታድግ ነገ ሙክት ትሆናለች ፣ እናት ሁናም ብዙ በጎችን ትወልዳለች ። ከአንድዋ ብዙ ይገኛል ። በማረድ ውስጥ አንድ መቶ ብር የሚያተርፈው ሰውዬ ፣ ገላጋይ ቢያገኝ ግን የማይቆጠሩ ሺህ ብሮች ወደፊት ያገኛል ። ግልገሏን ቢተዋት በባንክ ገንዘብ እንዳስቀመጠ ይቆጠርለታል ። እየወለደ ይመግበዋል ።

ብዙ ግልገሎቻችንን ገላጋይ አጥተን አርደናቸዋል ። ራእያችንን ለእልህ አርደነዋል ። ወዳጆቻችንን ለወረት አድልተን ገፍተናቸዋል ። ንብረታችንን በስሜት አብደን ሸጠናል ። የምንሰጥ የነበርን ተቀባይ የሆነው ምናልባት ግልገላችንን አርደን ነው ። አዲስ ትውልዶችን የቀጨነው ፣ የማይረካው ፍላጎታችን መጠቀሚያ ያደረግናቸው ገላጋይ አጥተን ነው ። ገላጋይ የሚገላግለው በፍቅር እጅ ፣ በምክር ፣ በጸሎት ነው ። ቢላዋ የያዘውን እብድ እጁን የሚይዘው ገላጋይ ነው ። “ተው ታገሥ” እያለ በምክር የሚያበርደው ገላጋይ ነው ። “በስመ አብ በል ሰይጣንን ገሥጸው” እያለ የሚጸልየው ገላጋይ ነው ። ገላጋይ የመሥዋዕትነት ልብ ፣ የምክር ሀብት ፣ የጸሎት ኃይል ያስፈልገዋል ። ገላጋይን ለመስማት አክብሮትን ማዳበር ይገባል ። አግም አደግ ስንሆን ምክርን መስማት ያቅተናል ። ሁሉን በማስተዋሌ ልፍታው ስንል ጸሎትን እናቆማለን ። ሕይወት ያለ ገላጋይ ብዙ ግልገሎቻችንን የምናርደባት የጸጸት ኮረብታ ናት ። ነገን የሚያዩልን ገላጋዮች ፣ ወጋገን የሚፈነጥቁልን መካሪዎች ያስፈልጉናል ። “የሚቆጡንን መካሪዎች አታሳጣን” ብሎ መጸለይ ትልቅ ሊጦን/ልመና ነው ። አስታራቂ ያስፈልገናል ። የምንሰማውና የምናከብረው አባት ያሻናል ። ያጠፋናቸው አዋቂዎችና አባቶች ለዛሬው መቅበዝበዛችን ያስፈልጉን ነበር ። “ተራጋሚ ራሱን ደርጋሚ” እንዲሉ አዋቂዎችን ስንጎዳ እኛው እንጎዳለን ። የልጆች ቤት ገላጋይ የለውም ። የበለው ዕድር የቅርጫ ሥጋ ያደርገናል ። ዛሬ የምናርደው ግልገላችን ዕድሜአችን ሲገፋ ያጸጽተናል ።

አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ ፣ መካሪ አታሳጣን ። ተመክሮ መመለስን አድለን ።

የብርሃን ጠብታ 23

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 16 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ