“የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፥ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት በጳንጦስና በገላትያ በቀጰዶቅያም በእስያም በቢታንያም ለተበተኑ መጻተኞች፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።” 1ጴጥ. 1፥ 1-2 ።
ሐዋርያው ስለ ሥላሴ ይናገራል። እግዚአብሔር አብን ፣ እግዚአብሔር ወልድን ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ያነሣል ። በስም ፣ በአካል ሦስት መሆናቸውን ይናገራል ። እንዲሁም የኩነት ሦስትነታቸውን ይገልጻል። አብ ልብ ፣ ወልድ ቃል ፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ መሆኑ የኩነት ወይም የመሆን የኋኝነት ሦስትነት ይባላል ። እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው ማለት ፣ ማወቅ የከዊነ ልብ ተግባር ነው ። አብ ለራሱ ልብ ሁኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ እወቀታቸው ፣ ማሰቢያቸው ፣ ማቀጃቸው ነውና ። ሥላሴ አንድ ፈቃድ አለው የምንለው በአብ ልብነት ነው ።
ቅዱስ ጴጥሮስ አሁንም ስለ ወልድ ይናገራል ። የደሙን መረጨት ንዝሓተ ደሙን ያነሣል። ደም የሥጋ ነው ፣ አዳኝ ደም መሆኑ ጌታችን ፍጹም ሰው ፣ ፍጹም አምላክ መሆኑን የሚገልጥ ነው። መታወቅ ፣ መረጨት ፣ መቀደስ የሚሉት ቃላት ለአማንያን ተነግረዋል። በሥላሴ መታወቅ ፣ መረጨትና መቀደስ ፍጹም ደስ ይላል ። ዓለም ሳይፈጠር በልበ ሥላሴ ታወቅን ፣ በዘመን ፍጻሜ በልጁ ደም ተዋጀን ፣ በመንፈስ ቅዱስም ተቀደስን ። ስላወቀን ሞተልን ፣ ስለሞተልን ተቀደስን። መዳናችን ሥላሴያዊ ነው ። ዮሐ. 3፡16 ። ኢየሱስ ብቻ የሚል አስተሳሰብ የሰባልዮስ ኑፋቄ ነው። ስለ ምእመናን ሲናገር የተመረጡ ይላል ። የሚገርመው የተመረጡት ተበትነዋል ፣ እንግዶች ሁነዋል ። መመረጣችን ላለመሰደዳችን ዋስትና አይደለም ። ከሰማይ አገራችን ርቀን መኖራችን እንዲታወቀን እንገፋለን ፣ እንደ ባይተዋር እንታያለን ።
በቡራኬውም ከሥላሴ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ ይላል ። ጸጋ ሰው የዳነበት ምሥጢር ነው ። ሰላምም ፍሬው ነው! ጸጋ ይቀድማል ፣ ሰላም ይከተላል ። ድኅነተ ነፍስ ያላገኘ ሰው ፣ ሰላም ሊኖረው አይችልም። /ማቴ. 16፡26/ ። ጸጋ ሥሩ ፣ ሰላም ዘለላው/ፍሬው ነው ! በመቀጠል አማንያን ያሉበትን ሁኔታ ይገልጣል ። የተበተኑና መፃተኞች ይላቸዋል ። መበተናቸው አገር አጥተው መንከራተታቸው ነው ። መፃተኛነታቸው ባይተዋር መደረጋቸው ነው ። አሁን ያሉበት ሥጋዊ አድራሻ ጳንጦስ፤ ገላትያ፣ ቀጰዶቅያ ፣ እስያ ነው ። የነፍሳቸው አድራሻ ግን ልበ ሥላሴ ነው። በዚህች ዓለም እንግዳ ነኝ ብሎ መቀበል የአማኝ ወጉ ነው ! እንግዳ ምንም ቢመቸው መሄዱ አይቀርም ።
አባት እናትን ቢያጡ ሥላሴ አባት እናት ነው ። ርስት ጉልት ቢቀሙ ሥላሴ አገር ነው ። ቅ/ ጴጥሮስ ስለ ራሱ ይናገራል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ይላል ። ሐዋርያ ሂያጅ ገስጋሽ ፣ መልእክተኛ ፣ የንጉሥ ደብዳቤ አድራሽ ነው ። ሐዋርያ በሥልጣን የተላከ ነው ። ሐዋርያ ጌታችንን ያየ ፣ የሰማ ነው ። የቄሣር ሳይሆን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ መሆን መታደል ነው ።
በእግዚአብሔር አብ ታውቀናል ። ነቢዩ እንዲህ ይላል፡- “አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው።” ኢሳ. 63፡16 ። ያለመታወቅ ሕመም ለሚሰማን እግዚአብሔር ያውቀናል ። መረጨትም መንፃት ፣ የእግዚአብሔር መሆን ፣ የደሙን ማኅተም መቀበል ነው ። የሚቀድሰንም መንፈስ ቅዱስ ነው ።
“ይታዘዙ ዘንድ” ይላል ። የመታወቁ ፣ የመረጨቱ ዓላማ መታዘዝ ነው ።
ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከሁላችን ጋር ይሁን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተጻፈ ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም.