የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መግለጥ አለመቻል

አንድ የሚነገር አባባል አለ፡- “ምንጊዜም አንተን የሚያበሳጭህ ሰው አንተን ወዶህ ፍቅሩን በትክክል መግለጥ የማይችል ሰው ነው ።”

በዚህ ዓለም ላይ ከልባቸው ወድደው ፍቅራቸው መግለጥ ያልቻሉ ሰዎችና ሳይወዱ እንደሚወዱ የሚመስሉ ሰዎችን እናገኛለን ። ከልባቸው ወድደው ፍቅራቸውን መግለጥ የማይችሉ ሰዎች የተለያዩ ምክንያቶችን ያነሣሉ ።

ባልወድ ኖሮ አብሬ መኖር አልችልምና መውደዴን በቃል መግለጥ አስፈላጊዬ አይደለም ።

መውደዴን የምወደው ሰው ሊያውቀው ይገባዋል ።

የቤት ወጪዬን አላጓደልኩምና መውደዴ ምን ጥርጥር አለው ?

የተሻሉ ሰዎችን ትቼ ይህን ኑሮ እየኖርሁ ነውና የከፈልኩት መሥዋዕትነት ፍቅሬን ስለሚገልጥ መውደዴን መናገር አስፈላጊዬ አይደለም ።

ብዙ የውጭ ዕድሎቼን የሰረዝኩት ይህን ፍቅር በማክበሬ ነውና ፍቅሬን በሌላ መንገድ መግለጥ አስፈላጊዬ አይደለም ይላሉ ። 

እነዚህ ሰዎች አብሮ መኖር ማለት ፍቅር ብቻ አለመሆኑን አልተረዱም ። ሰው ከጎረቤቱ ፣ ከዘበኛውና ከቤት ሠራተኛውም ጋር አብሮ ይኖራል ። ይህ ግን ፍቅር ላይሆን ይችላል ። የምንወደው ሰውም ግንኙነቱ ከአንደበታችን ጋር እንጂ የልባችንን ላያውቅ ይችላልና በራሱ ማወቅ አለበት ብሎ ማሰብ አይገባም ። የቤት ወጪ ማሟላትም የፍቅር መገለጫ መሆን አይችልም ። ከሠራተኞች ጋር የሚኖሩም ያሟላሉ ። የትላንት መሥዋዕትነትም የዛሬን ፍቅር ሊገልጥ አይችልም ። ትላንት የከፈልነው ዋጋ ለትላንት ስሜታችን ትክክል ነበረ ፣ ያንን ግን ሁልጊዜ እያወሩ መውደዴ ይታወቅልኝ ማለት ትክክል አይደለም ። 

ከልባቸው ፍቅር ሳይኖር ወደድሁ የሚሉ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች የጠጡ ወይም ሳይጠጡ በገንዘብ ፍቅር የሰከሩ ናቸው ። ምንም ተግባር የላቸውም በአፍ ቁልምጫና በጣፈጠ ጨዋታ መውደዳቸውን ያወራሉ ። ቀልደኞችም ይጫወታሉ ፣ ስለሚወዱን ሳይሆን ቀልደው ስለሚኖሩ ነው ። የሚያቆላምጡንም የሚወዱን ላይሆኑ ይችላሉ ፣ ልምድ ስለሆነባቸውም ነው ። እውነት ተኝታ ውሸት ዓለምን ዞራ እንደምትመለስ ልክ እንደዚሁ ከልባቸው የሚወዱ ተረጋግተው ሳሉ ሐሰተኛ አፍቃሪዎች ግን የቃላት ዝናብ ሲያዘንቡ ይውላሉ ። እውነተኛ ፍቅር በልብ ሲኖር ባለቤቱን ደስ ያሰኛል ፣ በአፍ ሲገለጥ ተወዳጁን ያስደስታል ፣ በተግባር ሲገለጥ ሁለቱም ያንጻል ። በፍቅር ውስጥ ያለው ሕንጸት እንጂ ጊዜ መግፋት አይደለም ። የሚያንጽ ፍቅር በልብ ፣ በቃልና በተግባር ሕያው መሆን አለበት ። ራሳችንን ከፍቅር ጎድለን ስናገኘው ፣ ትላንት የምንወደውን ሰው ዛሬ መውደድ ሲያቅተን ከመጨነቅ መጸለይ መልካም ነው ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ካልረዳን ራሳችንንም መውደድ አንችልም ። ፍቅር የባሕርያችን ሳይሆን ከእግዚአብሔር የምንካፈለው ጠባይ ነውና እንደገና እንዲሞላን መለመን ያስፈልገናል ። 

ከልባቸው የሚወዱ ሰዎች ፍቅራቸውን መግለጥ አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ፍቅራቸውን በተሳሳተ መንገድም ሊገልጡት ይችላሉ ። የሚያበሳጩ ነገር ግን እየወደዱ ያሉ ሰዎች አሉ ። የሚወድ ሰው እንዴት ያበሳጫል ? ከተባለ እነዚህ ሰዎች ፍቅራቸው መግለጥ ስላቻሉ ነው ። በጣም ከተጎዳን በኋላ ሊነቁ ይችላሉ ፣ እነርሱ ግን እንደሚወዱን ብቻ በማሰብ የሚያጠፉትን ጥፋት የሚያውኩትን ስሜት አይረዱም ። ብዙ ልጆች ወላጆቻቸውን በሽተኛ ያደረጉት በዚህ መንገድ ነው ። ልጆቹ የሚነቁት ግን ወላጆቻቸው ካለፉ በኋላ ነው ። ፍቅራቸውን በስድብ የሚገልጡም አሉ ። ፍቅር ቅዱስና አክባሪ ነው ። እነዚህ ሰዎች ግን መውደድ የሚገለጠው በዚህ መንገድ ስለመሰላቸው ሊገልጡት ይችላሉ ። ብሰድበውም የእኔ ስለሆነ አይቀየመኝም በማለት ሊሆን ይችላል ። ሰው ራሱን ሲሰድብ ቢውል ራሱ እንደማይቀየመው እንደ ራሳቸው ያዩትን ሰውም መስደብ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ ። ማኩረፍንም የፍቅር መግለጫ የሚደርጉ ሰዎች አሉ ። ማኩረፍ ሰላምን የሚያናጋ ነገር ነው ። የሚያኮርፉ ሰዎች የሚወዱት ሰው እንዲያባብላቸው ፈልገው ሊሆን ይችላል ። አሊያም የሚወዱትን ሰው እንደ መልአክ በማየት ትንሽ ስህተቱን መታገሥ አለመቻል ነው ። ኩርፊያ ልብን ብቻ ሳይሆን መልክንም የሚያበላሽ ፣ የበራውን ቤት የሚያጨልም ነው ። የአንዳንድ ሰዎች ኩርፊያ ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ያለ ያስመስለዋል ። እስከ ዓመት የሚያኮርፉ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ያለፈውንና ወደፊት የሚፈልጉትን ነገር ማስፈጸም የሚፈልጉት በኩርፊያ አስገዳጅነት ነው ። መወያየት ማድመጥ አይችሉም ። ኩርፊያ በእልህ አሊያም ፍቅርን ገለጥሁ በሚል ስሜት ሊከሰት ይችላል ። 

ፍቅራቸውን በመምታት የሚገልጡ ሰዎችም አሉ ። እንኳን ሰው እንስሳ በማይመታበት ዘመን እንዲህ ማሰብ ከባድ ነው ። ነገር ግን ሰው የማኅበረሰቡ ውጤት ነውና ከማኅበረሰቡ ያየውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ፍቅሩን በዱላ የሚገልጥ ሰው አለ ። “ሚስትህን በአበባም ቢሆን አትምታት” የሚል የሂንዱ አባባል አለ ። አበባ ቢሆንም የታሰበበት አሳብ ግን ክፉ ነው ። አንዳንድ ሴቶች ባሌ ካልመታኝ እንደሚወደኝ በምን አውቃለሁ ? ይላሉ ። ይህ በሽታ ነውና መታከም ያስፈልጋቸዋል ። ዱላ የሚሰነዝሩ አፍቃሪዎች በዕድሜአቸው መጨረሻ ላይ አቅማቸው ሲደክም የተመታው ሰው እየጠላቸውና እያስታወሰ ያንገበግባቸዋል ። ደግሞም ለእርሱ ሚስቱ ብትሆንም ለልጆቹ ግን እናት ናትና የልጆቹን ጥላቻ እንደሚያተርፍ ማሰብ ያስፈልጋል ። ብዙ ዓይነት የፍቅር መግለጫ እያለ ዱላን የፍቅር መግለጫ ማድረግ ተገቢ አይደለም ። 

ቅናትን የፍቅር መግለጫ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ከዛር ለሚከፋው ቅናት ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡት የፍቅር መግለጫ ስለመሰላቸውም ነው ። ቅናትን የሚወልድ የበታችነት ስሜት ነው ። ያ ሰው ዛሬም የምንወደውን እኛን ትቶ ሌላ ፈልጎ ከሄደ በሰላም መሸኘት ይገባል ። ሰው አብሮ መኖር ያለበት ከሚወደው ጋር ነው ። ቅናት ግን ያንን ሰው ላጣው እችላለሁ እያለ በቤት አስሮ ፣ አካል አጉድሎ ፣ ከሰው ለይቶ ያኖራል ። በጣም የሚቀኑ ሰዎች በልጆቻቸው ሳይቀር እየቀኑ ልጆችሽ አጠገብሽ አይቀመጡ እያሉ ሲበሳጩ እናውቃለን ። ቅናት የፍቅር መግለጫ ሳይሆን በሽታ ነው ። የተቀናባቸው ሰዎችም ራሳቸውን ከማዋደድ አንድ ቀን ሞት ሊያመጣብኝ ይችላል በማለት ማስጣል አለባቸው ።

የአሠርቱ ትእዛዛት ሁለተኛው ክፍል ፍቅረ ቢጽ ወይም ወንድምን መውደድ ነው ። በዚህ ክፍል ውስጥ አክብሮት አለ ። የምንወደውን ሰው ወንዱን እንደ ወንድም ፣ ሴቷን እንደ እህት ማክበር ይገባል ። አክብሮት የፍቅር መገለጫ ነው ። አክብሮት ማለትም መረዳዳት ነውና የፍቅር መገለጫው መረዳዳት ነው ። የወንድምን ሕይወትና ጤና መጠበቅም “አትግደል” በሚለው ትእዛዝ ተገልጧል ። ሁለተኛው የፍቅር መግለጫ የወንድምህን ሕይወት መንከባከብ ነው ። “አታመንዝር” የሚለው ትእዛዝም ሦስተኛው የፍቅር መግለጫ በቃል ኪዳን መጽናትን የሚያመለክት ነው ። “አትስረቅ” የሚለውም የወዳጅን ንብረቱን መጠበቅ እንደሚገባ የሚገልጥ ነው ። አንድን ሰው ስንወደው ሕይወቱን ብቻ ሳይሆን የእርሱ የሆነውን ንብረትም እንጠብቃለን ። “በሐሰት አትመስክር” የሚለውም የወዳጅን ስም መጠበቅ እንደሚገባ የሚገልጥ ነው ። አንድን ሰው ስንወደው ስሙን እንጠብቃለን ። “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ” ይላል ። የባልንጀራን ትዳር መቀማት ፣ ሎሌውን ማስኮብለል ፣ ሀብቱን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ይህን መመኘት እንኳ አይገባም ። አንድን ሰው ስንወደው ትዳሩን አጥብቆ እንዲይዝ እንመክረዋለን ፣ ሎሌዎቹንም አግዙት እንላለን ። ማረሻ በሬውን ወይም ሥራውን ፣ መጓጓዣ አህያውን ወይም መኪናውን አንመኝም ። የእርሱ የእኔ ነው ብለን በደስታው ደስ ይለናል ። የእርሱ የሆነውን ከተመኘን ግን እርሱን መጥላት እንጀምራለን ። 

ፍቅራችንን የምንገልጥበት ብዙ መልካም ነገሮች አሉ ። ፍቅራቸውን በመልካም መንገድ መግለጥ ያልቻሉትንም ልናውቅላቸውና ልናግዛቸው  ይገባል ። ፍቅር ለሚወደው መንገድ ያሳያል ።

ፍጻሜ የሌላት የእግዚአብሔር በረከት በሁላችን ላይ አድራ ትኑር ! አቤቱ ፍቅርን ከነመግለጫው ስጠን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ