የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መጽሐፍ ቅዱስ / ክፍል ስምንት

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ

ቅዱስ ቃሉ
                                                        ማክሰኞ ሐምሌ 29 2006 ዓ.ም.
በክፍል ሰባት መልእክታችን የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት በቅኝት መልክ ዓይተናል። በዛሬውና በክፍል ስምንት ጥናታችን ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ወይም መጽሐፍ ቅዱስ፡-
– የሚነበብ፣
– የሚጠና፣
– የሚመረመርና
– የሚተረጎም መሆኑን እናያለን፡፡
ቃሉ ይነበባል
እግዚአብሔር ቃሉን የሰጠው ለልጆቹ እንጂ ለሊቃውንት አይደለም፡፡ ስለዚህ አማኒ ሁሉ ሊያነበው የሚገባ መጽሐፍ ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያለመዱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ግን መስማት የሚፈልጉ ብዙዎች፣ ሰባክያንን ብቻ በመስማት ተወስነው ተቀምጠዋል፡፡ ነገር ግን ወደ ምንጩ አይቀርቡም፡፡ ቃሉ ግን የምንሰማው ብቻ ሳይሆን የምናነበውም ነው፡፡ ስለዚህ ቃሉን በትጋት ማንበብ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን የፍቅርና የመጽናናት፣ የምሪት መልእክት አለው፡፡ ፈጥነን የምንቆሽሽ፣ ያበጀን እየመሰለን የምናጠፋ፣ ሜዳ ላይ የሮጥን እየመሰለን ወደ ገደል የምንዘረጋ ተላላዎች ነንና የቃሉ ራጅ እንዲያየን መፍቀድ አለብን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የምኩራብ ንብረት በነበረበት ዘመን ሰዎች ቃሉን ለማንበብ እየጓጉ ለመስማት ብቻ ይገደዱ ነበር፡፡ ዛሬ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የግል ንብረታችን ሆኗልና ማንበብ ይገባናል፡፡ “መጽሐፍ ቅዱስ የጠረጴዛ መጽሐፍ እንጂ የመደርደሪያ /የሼልፍ/ መጽሐፍ አይደለም” እየተባለ የሚነገረውም ለዚህ ነው፡፡ አንድ ሰባኪም መጽሐፍ ቅዱስን ስለማንበብ ሲናገር ፡- “ዓለም ስድስት ቀን የምታገኘውን ሰው በሰባተኛው ቀን እያስተማርን ብቻ መንፈሳዊ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ዕለት ዕለት ቃሉን በማንበብ መትጋት ያስፈልገናል” ብሏል፡፡ ሌላውም አዋቂ፡- “በመጽሐፍ ቅዱስ ዝሆን ሊዋኝባቸው የሚችል ጥልቆች አሉ፤ እንደዚሁም የበግ ግልገል ሊሄድባቸው የሚችል ጥልቅ ያልሆኑ ውሀዎች አሉ። ሌላው ቅዱስ ደግሞ እንደዚህ ይላል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመንገዱ ለመሄድ ለሚፈልግ ለአዋቂ ብርሃን ነው እንጂ አስቸጋሪ አይደለም” ብሏል።

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዲሬክተር የነበሩ አንድ ሰው ከዛሬ 64 ዓመት በፊት በጻፉት መጽሐፍ፡- “ምግብ ለሰውነት አስፈላጊ እንደሆነ፤ እንዲሁም ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ለመንፈሳዊ ሕይወት አስፈላጊ ነው፡፡ ሙዋቹ የእንግሊዝ ንጉሥ ጆርጅ 5ኛ ማናቸውም ሥራ ቢኖርባቸው መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ያነቡ ነበር ይባላል፡፡ ጆን ክሪዞስቶም በሌሎች ቅዱሳን መጻሕፍት በየቀኑ ከሚያጠኑት በላይ የሮሜን መልእክት በሳምንት ሁለት ጊዜ ያነቡት ነበር፡፡ …  አንድ ትልቅ ሠራተኛ ማለዳ ማለዳ የመጀመሪያዎችን ሁለት ሰዓቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና በጸሎት ያሳልፋቸው እንደ ነበረ፤ ከመሞቱ በፊት መስክሮ ተናገረ ይባላል፡፡ የሥራውም መከናወን ምክንያት ይህ መሆኑን መሰከረ፡፡ ሥራህ ለመጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የተወሰነውን ጊዜ በማናቸውም ምክንያት እንዳያሰናክልብህ ተጠንቀቅ” ብለዋል /መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚጠና፡ በሐፍዝ ዳውድ፡1939 ዓ.ም.፡፡ ገጽ 20/፡፡ የእኛ መመሪያ ግን የተገላበጠ ይመስላል፡- “መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትህ ሥራህን እንዳያሰናክልብህ ተጠንቀቅ” የሚል ሳይሆን አይቀርም፡፡
ቃሉ ይጠናል
መጽሐፍ ቅዱስ ተነቦ የሚታለፍ ብቻ ሳይሆን ደግመን የምናነበው እያንዳንዱ ቃልና ፊደል እንዲሁም ሐረግና አንቀጽ የመናገር ብቃት ያለው መጽሐፍ ነው፡፡ ታሪኩ ታሪካችን፣ ተግሣጹ ተግሣጻችን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ብዙ ዘዴዎች ቢኖሩም ከተጻፈበት ዓላማ ተነሥተን ስናነብ ግን ይበልጥ ይበራልናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእምነትና የመታዘዝ መጽሐፍ በመሆኑ እምነትና መታዘዝ ቃሉን ይከፍትልናል፡፡
ለብዙ ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስን የመረመሩ ሰዎች እንደሚናገሩት መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም መዝገበ ቃላት፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ ስፍረ ዘመንና መልክአ ምድራዊ ጥናቶች ወሳኝ ቢሆኑም መጽሐፉ መንፈሳዊ እንደ መሆኑ ሁለት ነገሮች በእምነት ሲፈጸሙ ትርጓሜው ከንጋት ይጠራል፡፡ እነርሱም፡-
   ክርስቶስን ማመን፡- ብሉይ ኪዳን ሕዝብን ለክርስቶስ ያዘጋጀ፣ የጥላ አገልግሎት የሰጠ፣ ሰማንያ አምስት ከመቶ በክርስቶስ የሚፈጸም ትንቢቶችን ያዘለ ሲሆን አዲስ ኪዳን ደግሞ የክርስቶስን መምጣት የተረከ፣ ጥላ ሳይሆን የሚጨበጥ አካል የሆነ፣ ትንቢት ሁሉ በክርስቶስ መሟላቱን በመግለጥ ለዳግመኛ የክርስቶስ ምጽአት ቤተ ክርስቲያንን የሚያዘጋጅ ነው፡፡ ስለዚህ መላው መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ሥዕል ነው፡፡ የክሩን ጫፍ ከያዝን እስከ መጨረሻው መምዘዝ እንደምንችል ስለ ክርስቶስም ካወቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ አሳብ ይገባናል፡፡ ማወቅ ብቻም ሳይሆን ማመንን ይጠይቃል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂ ዳግመኛ እንዲህ ብለዋል፡- “በምታነበው በእያንዳንዱ ምዕራፍ ኢየሱስን ተመልከተው። ክርስቶስ የማዕዘን ደንጊያ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ አርእስት እርሱ ነው። በኤማሁስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር ሲነጋገር እርሱ ያለውን ተመልከት፡- ከሙሴና ከነቢያት ጀምሮ ስለርሱ በመጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ይተረጉምላቸው ነበረ/ሉቃ.24፡27/። እንደ ኦሪት ዘሌዋውያን የመሰለ መጽሐፍ ላይ ላዩን ብታነብ የሚጠቅም ትምህርት የሌለበት መስሎ ታገኘዋለህ። ነገር ግን ኢየሱስን በልዩ ልዩ መሥዋዕትነት፡ በሊቀ ካህንነትና በማናቸውም ልብስ ሁሉ በቤተ መቅደስና በውስጡ ባሉት ስትመለከተው ሁኔታው ሁሉ ይለወጣል። ስለዚህ በምታጠናው ቁጥር ሁሉ ኢየሱስን ፈልገውና በሰዎችና በከተማዎች ስም ሳይቀር ውበትና ኃይል በሱ /በቁጥሩ/ ታገኛለህ” /መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚጠና፡ ገጽ 37-38/።
   መታዘዝ፡- መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሁሉ በሙሉነት ስንታዘዝ መጽሐፍ ቅዱስ ይገባናል፡፡ መጽሐፉ የመታዘዝን ምላሽ የሚጠይቅ እንጂ ተራ የታሪክና የፍልስፍና መጽሐፍ አይደለም፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ቃሉ በመንፈስ ቅዱስና በኃይል የወጣ ስለሆነ ራሱን ማስፈጸም ይችላል፡፡ እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት መረጃ መጻሕፍት ወሳኝ ቢሆኑም የመታዘዝን ያህል ግን አይሆኑም፡፡ እግዚአብሔር ቃሉን የሰጠን እንድናደንቅለት ሳይሆን እንድንታዘዝለት ነውና፡፡
ቃሉ ይመረመራል
ማዕድን የሚገኘው ጠልቀን በቆፈርን ቊጥር ነው፡፡ እንዲሁም የቃሉን ሀብት ለማግኘት በጥልቀት መመልከት ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በጸሎት፣ በጽሞናና በአክብሮት የሚጠና መጽሐፍ ነው፡፡ ለማወቅ የሚዳግት መጽሐፍም አይደለም፡፡ ነገር ግን አትኲሮትን የሚሻ መጽሐፍ ነው፡፡ በቃሉ ውስጥ በጥልቀት ባየን ቊጥር ከመገንዘብ በላይ የሆነ የቃሉን ኃይልና የመንፈሱን ረድኤት እናገኛለን፡፡ በተመስጦም ይህን ዓለም እንረሳለን፡፡ ችግሮቻችንና ገዝፈው የሚታዩን ተራራዎቻችን ያንሱብናል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ወደ ልቡም አሳብ እንቀርባለን፡፡ ቅዱስ ፍርሃትና እርካታ ያለው አምልኮን እናገኛለን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤርያ አይሁድ በማድነቅ ይተርካል፡- “ …እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፡- ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ” ይላል (የሐዋ. 17፥10-11)፡፡ እነዚህ ሰዎች ልበ ሰፊነታቸው፡-
1-                       የሚያመሳክሩት ከልማዳቸው ጋር ሳይሆን ከቃሉ ነበር፤ ቃሉ ያላቸውን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ነበሩ፡፡
2-                      ይህን ተግባር የሚያከናውኑት አልፎ አልፎ ሳይሆን ዕለት ዕለት ነበር፤ ስለዚህ ከቃሉ ጋር ዝምድና ነበራቸው፡፡ እውነተኛ የሆነ የልብ ጥማት ይታይባቸዋል፡፡ የእውነት አሰሳ ላይ ነበሩ፡፡
3-                      የሰሙትን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ካመሳከሩ በኋላ በሙሉ ፈቃድ ይቀበሉ ነበር፡፡ ይህ ማለት ለተረዱት እውነት ሁለንተናቸውን ይሠዉ ነበር፡፡
ዛሬ ደግሞ የምናየው በተቃራኒው ነው፡፡ ፈጽሞ አልሰማም በማለት ውስጥን ብቻ በማዳመጥ ክርስትናን ለመኖር መሞከር፣ መጽሐፍ እያለን መጽሐፍ አልባ ለመሆን እየሞከርን ነው፡፡ ነገር ግን ከማንም ጋር ለመነጋገር ብቻ ሳይሆን ሚዛናዊ ለሆነ አእምሮም አንድ ማዕከል የሆነ ነገር ያስፈልገናል፡፡ ማዕከላችንም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ሁለተኛው ዛሬ ያለው ችግር፡- ቃሉን የምናነበው ለእኛ ምላሽ ሳይሆን ለመናፍቃን መልስ ፍለጋ ነው፡፡ ቃሉ ግን መከራከሪያ ሳይሆን ምግባችን ስለሆነ በየዕለቱ ማንበብ ያስፈልገናል፡፡ እምነታችንን ለመጠበቅም ማንበብ ተገቢያችን ነው፡፡ ሦስተኛውና ዋናው ችግር ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀብለን ካለንበት ክፉ ሕይወት ለመውጣት ውሳኔ አናደርግም፡፡ እንደ ቤርያ ሰዎች ልበ ሰፊ መሆን በእውነት ያስፈልገናል፡፡ ኧረ እናስተውል። ያለነው በዘመን መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ቃሉ፡-
   ይነበባል
   ይጠናል
   ይመረመራል የሚለውን ዓይተናል። በቀጣዩ ቃሉ ይተረጎማል የሚለውን እናያለን።  ክብር ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን።
                                             -ይቀጥላል-
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ