የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ — ሰኞ መስከረም 12/ 2007 ዓ/ም
የሰው ልጆች ትልቁ ጥያቄ ዕረፍት ነው፡፡ ሰው ከድካሙ በኋላ፣ ከመኖሩ ቀጥሎ ውስጣዊ ዕረፍትን ይፈልጋል፡፡ ለድካሙም ሆነ ለመኖሩ ዋጋ እንዲሰጥ የሚያደርገው ይህ እርካታ ነው፡፡ ቁሳዊ ፍላጎት ከተሟላ በኋላ፣ ቤትና ንብረት ከተደራጀ በኋላ፣ ትዳርና ልጅ ከተቃና በኋላ ሌላ የሚናፍቅ ነገር አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ያ ሰው፡- ፍለጋ በዓለም ላይ ማለቂያ የለውም ይላል፡፡ ዕረፍት ምንድነው? በማለት ይጠይቃል፡፡ ፍለጋ የሌለበት ግኝትን ተቅበዝባዡ ሰው ይሻል፡፡ ማግኘት ደስ ይላል፣ ስኬትም በጣም ጥሩ ነው፣ የበላይነትም ለጥቂቶች ብቻ የሚገኝ ነው፣ ማንም ያላገኘውን ነገር መጨበጥም ዕድለኛነት ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ የድል ቁጥሮች ቀጥሎ ሰው አሁንም ራሱን በፍለጋ ውስጥ ያገኘዋል፡፡ እርሱም የእርካታና የዕረፍት አገሩ የት ነው? የሚል ነው፡፡
ዓለም የገዛ አባሏንም መደለል እያቃታት በአደባባይም እየተራቆተች ነው፡፡ ዓለማውያን እርካታን ፍለጋ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ፣ አማንያን ደግሞ ወደ ዓለም ሲሄዱ በመንገድ እንዳይተላለፉ ያሰጋል፡፡ ዓለም ግን እንኳን እውነትን ላወቀ የሚሆን እውነቱን ላላወቀ የሚሆንም እርካታ አጥታለች፡፡ አብዝቶ አደንዛዥ ዕፅ የሚወስድ ሰው መደንዘዝ የማይችል እየሆነ ይመጣል፣ ስለዚህ ሕመሙ ይሰማዋል፡፡ ማደንዘዣውም አልቀረም፣ ሕመሙም አልቀረም፡፡ ማደንዘዣ የሚሠራው ለአዲስ አባል ነው፡፡ ለሰነበተው ማደንዘዣ አይሠራም፡፡ እንዳለፉት ዘመናት በዓለም ላይ ጊዜያዊ መርሳትና መደለል እንኳ እየቀረ ነው፡፡ ሰዎች በግልጽ እርካታ እንዳጡ እየተናገሩ ነው፡፡
ታዋቂ የሚባሉ ሰዎች በአደባባይ ደስታ የለንም እያሉ ይናገራሉ፡፡ መሸነጋገል ቀርቶ በግልጽ ስለ እርካታ ማጣት እየተነገረ ነው፡፡ እርካታ ማጣት ሁሉንም የሰው ወገንና ሁሉንም የኑሮ ደረጃ በእኩልነት የሚያሰቃይ ጥያቄ ሆኗል፡፡
ስለለመድነው የምናደርገው ስለወደድነው የምናደርገው ማለት አይደለም፡፡ መልመድ መውደድ እየመሰለ ያደናግራል፡፡ ቢሆንም ሰዎች እንደ ድሮ በሱስ ውስጥ ከሚያገኙት መደለል ይልቅ የሚመጣው አስፈሪ ነገር እየታያቸው ነው፡፡ ሥጋዊ ዕውቀታቸው በራሱ ሥጋዊ ደስታቸውን እየተጋፋው ነው፡፡ በእያንዳንዱ ስህተት የሚከተለውን ጉዳት ማወቃቸው እርካታ ቢስ እያደረጋቸው ነው፡፡ ምክንያቱም የዓለም ደስታ በጨለማ ካልሆኑ በብርሃን ፊት መቆም የማይችል ነውና፡፡ በርግጥ ወደ ዕረፍት ለመድረስ ዕረፍት ማጣት ወሳኝ ነው፡፡ አንድ ያልሞከርነው ዕረፍት አለ እርሱ ማን ይሆን?
“ማን” እና “ምን” የሚሉ ቃላቶች ወሳኝ ቃላት ናቸው፡፡ “ማን” ሕይወት ላለው ነገር ሲሆን “ምን” ሕይወት ለሌለው ነገር የሚቀጸል ነው፡፡ እርካታ ሕይወት ያለው ነገር ነው፡፡ ሕይወት ያለውን ነገር ሕይወት ከሌለው ቁሳቁስ መፈለግ ሞኝነት ብቻ ሳይሆን አድካሚም ነው፡፡ ሕይወት የሚገኘው ሕይወት ካለው ነገር ነው፡፡ ታዲያ የሕይወት መገኛ ማን ነው?
የማንኛውም መልካም ጉዞ መነሻው ዕረፍት ነው፡፡ ከዕረፍት ቀጥሎ የሆነ ጉዞ ኃይልና አስተሳሰብ የታደሰበት ጉዞ ስለሆነ በጉልበት ይጨረሳል፡፡ ካላረፍን የመጣንበትን መገምገም፣ የምንሄድበትን መለካት አንችልም፡፡ ዕረፍት የረጅሙ ጉዞ መነሻ፣ የኃይል ማደሻ፣ ሰላም ማፈሻ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሕይወት ያለ ዕረፍት አይጀምርም፡፡ ከዕረፍት በፊት መዛል፣ መድከም፣ መሸነፍ፣ መውደቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እነዚህ ነገሮች ዕረፍትን አስፈላጊ ያደርጉታል፡፡
በጠራራ ፀሐይ ስንጓዝ ሁላችንም የራሳችን ጥላ አለን፡፡ ነገር ግን ጥላ ፍለጋ እንገሰግሳለን፡፡ ለምን በራሳችን ጥላ አናርፍም? ስንል በራስ ጥላ ማረፍ አይቻልም፡፡ ሰዎች ጥሩ እንደሆንን ይነግሩናል፣ እኛን በማግኘታቸውም እንዳረፉ ይተርኩልናል፡፡ ሰዎች በእኛ ያረፉትን ያህል ግን እኛ በራሳችን ማረፍ አልቻልንም፡፡ አዎ በጥሩ ወይም በራስ መልካምነት ማረፍ አይቻልም፡፡ ታዲያ አንድ የሚያሳርፈን የመልካሞች መልካም ምንድነው?
ቃሉ፡- “የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል÷ ከመከራም ሥጋት ያርፋል” ይላል (ምሳ 1÷33)፡፡ ማረፍ መረጋጋት እንደሆነ ቃሉ ይነግረናል፡፡ ዝም ብሎ መቆም ወይም መቀመጥ ሳይሆን መረጋጋት ጌታን ትክ ብሎ መስማት ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚሰማ ሰው ከመከራ ሥጋት ያርፋል፡፡ ዛሬ ስንቀደስ ነገ ድንቅ ናትና ዛሬ የሚሰማ የነገ ፍርሃት የለበትም፡፡ እግዚአብሔር ለሚወዱትና ለሚሹት ያዘጋጀላቸው ታላቅ የዘመን በረከት ዕረፍት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሲቆጣም የሚነሣው/የሚወስደው/ ዕረፍትን ነው፡፡
በነቢዩ በዳዊት፡- “እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ፡፡ ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ” ይላል (መዝ 94÷11)፡፡ ይህ ቃል አስቀድሞ የተነገረው እስራኤል ወደ ከነዓን እየተጓዙ ሳለ በምድረ በዳ ነው፡፡ እንደገና ከነዓንን ከወረሱ ከ400 ዓመታት በኋላ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም አለ፡፡ በምድረ በዳ ላይ የነበሩት እስራኤላውያን ወደ ዕረፍቴ አይገቡም የሚለውን ቃል ሲሰሙ ሁለት ነገሮችን ተረድተዋል፡፡ የመጀመሪያው እስከ ዛሬ ዕረፍት የሚሉት ሰንበትን ነበር፡፡ የሰንበት ዕረፍት እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው የመጨረሻ ዕረፍት ይመስላቸው ነበር፡፡ ይህ ሰንበትም በኦሪት የታዘዘ ሳይሆን በጥንተ ፍጥረት የተሰጠ ነው፡፡ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብሎ ሲናገር ለካ የእግዘአብሔር ዕረፍቱ ሰንበት አይደለም፡፡ ዕረፍቱ በቀን ላይ የተመሠረተ አይደለም ብለው አሰቡ፡፡ ሁለተኛ ዕረፍቱ የምንወርሳት ከነዓን ናት ብለው እንደገና አሰቡ፡፡ ዕረፍቱን ከቀን ላይ አነሱና ወደ ቦታ ለውጠው አሰቡ፡፡ ከነዓንን ወርሰው መኖር ከጀመሩ ከ400 ዓመታት በኋላ በነቢዩ በዳዊት ወደ ዕረፍቴ አይገቡም አለ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ ለሕዝቡ ያዘጋጀውና ተስፋ የሰጠው ዕረፍት በቀንና በቦታ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ታዲያ እውነተኛው ሰንበት ማን ይሆን? ስንል ያ የሕይወት ሰንበት፣ ያ የውበት መደምደሚያ፣ ያ የበቃኝን ኑሮ የሚያለማምድ፣ ያ የጥም ቆራጭ፣ ያ የሙከራ ማብቂያ፣ ያ የሕይወት ጉልላት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ማረፍ በእርሱ ነው፡፡ እርሱ በሠራው የአዳኝነት ሥራ መደላደል ነው፡፡ የእርሱ መሥዋዕትነት መለኮትን ያረካ ከሆነ እኛን ማርካቱ የማይጠረጠር ነው፡፡
እርሱ ራሱ በልዑል ቃል፡- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ÷ ወደ እኔ ኑ÷ እኔም አሳርፋችኋለሁ” ብሏል /ማቴ. 11÷28/፡፡