የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ማኅደረ እግዚአብሔር

 አባ ጳኵሚስ እንዲህም አለ፡- ድህነት ፣ መከራ ፣ ከድሎት መራቅና ጾም  የገዳማዊ ይወት መሳሪያዎች ናቸው ። እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፡- ” እነዚህ ሦስት ሰዎች ፥ ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም ፥ ቢኖሩባት ሕዝ. 14፡14 ። ኖኅ ቁሳዊ የሆኑ ነገሮችን ቸል ማለትን ይወክላል ። ዳንኤል ማስተዋልን ሲወክል ኢዮብ ደግሞ መከራን ይወክላል ። እነዚህ ሦስቱ ተግባሮች አንድ ሰው ላይ ከተገኙ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ያድራል ። (ጳኵሚስ 60)
የእግዚአብሔር ቃል በመጠን ስለ መኖር ይናገራል ይልቁንም ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጠን መኖር ለሦስት ነገሮች እንደሚጠቅም ይገልጻል የመጀመሪያው፡- ለክርስቶስ መምጣት ዝግጁ ለመሆን ፤ ሁለተኛ ለመጸለይ ፣ ሦስተኛ የዲያብሎስን ውጊያ ለማሸነፍ በመጠን መኖር እጅግ አስፈላጊ ናቸው /1ጴጥ. 1፡13፤ 4፡8 ፤ 5፡8 / ሐዋርያው ጳውሎስም ኑሮዬ ይበቃኛል እንድንል ያስተምረናል የተባረከው አባት አባ ጳኵሚስም ለአንድ ገዳማዊ ሕይወት ለሚመራ መነኮስ ድህነት አስፈላጊ መሆኑን ይናገራል ሁሉም ገዳም ባይገባም እያንዳንዱ ክርስቲያን ልከኛ ሕይወትና የምናኔ ኑሮ መኖር እንዳለበት ራስን ስለ መካድና መስቀሉን ስለ መሸከም የነገረን ጌታችን አስታውቆናል በአጭር ቃል የክርስቲያን ሕይወት የመናኝ ሕይወት ነው
አባ ጳኵሚስ ሁለተኛ የጠቀሰው ነገር “መከራ” ነው ሰዎች መከራ ሲመጣባቸው ውስጣዊ ትኩሳት ይቀጣጠልባቸዋል መፍትሔ ፍለጋ በሮችን ማየት ይጀምራሉ ሊረዱአቸው የሚችሉ ሰዎችን ይፈልጋሉ የጸሎትን ኃይል ይጠቀማሉ የሌሎችን መከራ አቅርበው እንዲሰማቸው ይፈቅዳሉ ይህ ችግር እስኪያልፍ ድረስ መኖርን ይመኛሉ ይህን አልፌ ብሞት እንኳ አይቆጨኝም ይላሉ ይህን ሁሉ በረከት የሚያስገኝ መከራ ነው መከራ የሌለበት ሕይወት ግን በተቃራኒው ነው መከራ የሌለበት ሕይወት መሰላቸትን ያመጣል ፣ በራስ ዓለም ብቻ መንቀዋለልን ያስከትላል ፣ ሰዎች አስፈላጊዬ አይደሉም የሚል አመለካከት ያፈራል ፣ ስለ ሌሎች መከራ ስሜት አልባ ይሆናል ፣ የሚኖርበት ምክንያት ያንስበታል ፣ ሞትን መመኘት ይጀምራል በሕይወትና በሞት መካከል ያለው ልዩነት እየጠፋበት ፣ ድንዛዜ እያጠቃው ይመጣል
ከድሎት መራቅና ጾም አስፈላጊ መሆኑን አባ ጳኵሚስ ይናገራል ዘመናዊው ዓለም እንኳ እየደረሰበት ያለው ነገር ድሎትና ምግብ ገዳይ መሆኑን ነው የአኗኗር ዘይቤአችን ዕለት ፣ ዕለት እየተለወጠ በመሆኑ የማያስፈልጉ የሰውነት ክብደት መጨመሮች እነርሱን ተከትለው የሚመጡ በሽታዎች እየተበራከቱ ነው እንቅስቃሴ ማድረግ ፣ ስፖርት መሥራት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ከዛሬው ዓለም በፊት የነበሩ አባቶች የደረሱበት ምሥጢር ነው አንድ ትልቅ አባት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ቤት የመንፈስ ልጆቻቸው ሠርተው እዚህ ተቀመጡ አሏቸው እርሳቸው ግን በማግሥቱ ጠፍተው ወደ መጠነኛ ቤታቸው ገቡ መልሳቸው አጭር ነው ፡- “ልትገድሉኝ ነው ወይ ?” እኒህ አባት አሁንም ከመቶ ዓመት በላይ ሁኗቸው አሉ ፣ ምግባቸውን ያበስላሉ ፣ ገበያ ወጥተው ይገዛሉ ያሉበትን የክብር ሕይወት በጥንቃቄ ስለ ያዙት ዕድሜ አግኝተዋል “ዕድሜና ስንቅ እንደ ያዥው ነው” ይባላል ምቾት ገዳይ ነው ምግብ ለመኖር አስፈላጊ የሆነውን ያህል በመጠኑ ካልሆነ ሕይወትን ያሳጥራል ሁሉም የምግብ ዓይነት አስፈላጊ ሲሆን ከሁሉም ላይ በመጠን ፣ በመጠን መውሰድ ለጤና አስፈላጊ ነው ጾም የምንጾመው ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ነው ጾም ግን በኢአማንያን ዘንድም አለ ለጤንነት አስፈላጊ ነው እያሉ ውለው ምሽት የሚቀምሱ ብዙ ከሃዲዎች አሉ
አባ ጳኵሚስ በነቢዩ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ላይ ስለ ተጠቀሱትና ስለ ተመረጡት ሦስት ሰዎች እግዚአብሔር የተናገረውን ይጠቅሳል እነዚህ ሦስት ሰዎች፡- ኖኅ ፣ ዳንኤልና ኢዮብ ናቸው ኖኅ ቁሳዊ የሆኑ ነገሮችን ቸል ማለትን ይወክላል ። ዳንኤል ማስተዋልን ሲወክል ኢዮብ ደግሞ መከራን ይወክላል ። እነዚህ ሦስቱ ተግባሮች አንድ ሰው ላይ ከተገኙ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ያድራል ይላል
ኖኅ መርከብን ለመሥራት የሚያስችል ሀብት ካለው ባለጠጋ ሰው ነው የመረጠው ኑሮ ግን በመጠን መኖርን ነው በመጠን መኖር ማለት ድህነት ማለት አይደለም ኖኅ የሚታየውን ዓለም ንቆ ነበር እርሱ ይህ ዓለም ይጠፋል እያለ መርከቡን ሲሠራ ወደ ጭፈራና ሥጋዊ ደስታ የሚሄዱ ሰዎች ይዘብቱበት ነበር ኖኅ ግን የሚታየውን ደስታ ንቆ ለማይታየው መከራ በመዘጋጀቱ ተርፎ የሚያተርፍ ሆነ ኖኅ ዳግማዊ አዳም እስኪሆን ድረስ የፍጥረት ጉዞ በእርሱ ቤተሰብ እንደ ገና ቀጠለ የዓለምም ሕዝብ በልጆቹ ተጠራ ሴም ፣ ካም ፣ ያፌት ተባለ ንብረት ቢኖረን ተግባራዊ የምናደርጋቸው የእግዚአብሔር ትእዛዛት አሉ አሥራት ማውጣት ፣ ለድሀ መመጽወት እነዚህ ሁሉ ሲኖረን የምናደርጋቸው መንፈሳዊ ተግባራት ናቸውበመጠን መኖር ግን የእግዚአብሔር መቅደስ ለመሆን መዘጋጀት ነው
ዳንኤል አስተዋይ ሰው ነበር ባቢሎናውያን ክብሩን ጠብቀው የማረኩ ነበሩ ስለዚህ ዳንኤልን በቤተ መንግሥት አስቀምጠው የአገሩን ነገር እንዲረሳ ብዙ ገበታ ዘርግተውለት ነበር እርሱ ግን በቤተ መንግሥት የመነነ ሰው ነበር ጥሬ እየቆረጠመ የወዛ ነቢይ ነው በዚህም ማስተዋሉ ተገልጧል ዓለም አስብታ እንደምታርድ ተረድቷል
ጻድቁ ኢዮብም በመከራ ስለ መታሸት ትልቅ ምሳሌ ነው ኢዮብ ታሪክ ያገኘው በምቾቱ ሳይሆን በመከራው ነው ብዙ መከረኞች በዓለም ላይ አሉ እርሱ ግን በትዕግሥቱ ሲመሰገን ይኖራል ማጣቱን በምስጋና ስለ ተቀበለ እግዚአብሔር እጥፍ በረከትን ሰጥቶታል የኢዮብ የምቾት ዘመኑና የካሣው ዘመን 42 ምዕራፍ ካለው ከኢዮብ መጽሐፍ ሁለት ምዕራፍ ብቻ የወሰዱ ናቸው ምቾት ታሪክ የለውም መከራ ግን ብዙ ታሪክ አለው እጣን ሲጠበስ ይሸታል ፣ ክርስቲያንም በመከራ ውስጥ ያውዳል
ቁሳዊ ሀብትን መናቅ ፣ ማስተዋልና በመከራ መደሰት እነዚህ የሚያስፈልጉ ሲሆኑ ማኅደረ እግዚአብሔር ለመሆን ያበቁናል
ጸሎት
አንተ ገናና ፣ አንተ ብርቱ ፣ አንተ ቅዱስ ፣ አንተ ኃያል ጌታዬ በልቡናዬ ጉልበት ተንበርክኬ እሰግድልሃለሁ ይህች ቀን ሳታልፍ ይህንን ስማ ብለህ ስለፈረድህልኝ ፣ የማይገባኝና ትላንት እና የማይገባኝንም ነገ ስላዘጋጀህልኝ አመሰግንሃለሁ በታሪኬ ላይ ክብርህ ድል ነሥቶ ይውጣ ተወለደ ሞተ የሚል የማቱሳላን ታሪክ አልባ ዕድሜ ሳይሆን የቅዱስ እስጢፋኖስን የሥራ ዕድሜ አድለኝ ብዙ መሥራት ብዙ የማለም እንጂ ብዙ የመኖር ውጤት አለመሆኑን ግለጽልኝ ትንሽ ጊዜ ያለው ብዙ እንደሚሠራ አስተምረኝ በማይናወጠው ዙፋንህ ለዘላለሙ አሜን
የበረሃ ጥላ 5
ሰኞ መስከረም 5 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ