የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምነው በማለዳ

 አንዲት የጎጃም ሴት ሁለት ልጆችዋን ውኃ ወሰደባት ። ኀዘኑ ከባድ ፣ የማይወረወር የእሳት አሎሎ ፣ የማይቆረጠም የብረት ቆሎ ፣ የማይያዝ የነፋስ ደበሎ ነበር ። እናት ቋንቋ አጥታ ፣ አቅሏን ስታ ያዙኝ ልቀቁኝ ትላለች ። አልቃሽ መጥታ ስታለቅስ እንዲህ አለች፡-

“እቴ ልጆችሽ የት በረሃ ዋሉ ?

ምነው በማለዳው መጠጥ መጠጥ አሉ ፤”

በበረሃ የዋለ ሰው ውኃ ፣ ውኃ ይላል ። እነዚህ ልጆች ግን ከሰፈራቸው ያልራቁ ፣ የጎረቤት ወንዝ የወሰዳቸው ጭዳ ናቸው ። በሕፃንነት መጠጥ መጠጣት አልተለመደም ። እነዚህ ልጆች ግን በውኃ እንደ ሞቱ አስታወሰች ። መጠጥ ማለት ጭልጥ ፣ ጥፍት ፣ እልቅ ፣ እልም ማለት ነው ። በማለዳው በልጅነታቸው እንደ ሞቱ በቅኔ መናገርዋ ነው ። በሰሙ ውኃ እንደ ወሰዳቸው ስትገልጥ በወርቁ ደግሞ በልጅነታቸው ማብቃታቸውንና ማለቃቸውን አዘክራለች ። 

አገሬ ላይ ጉድፍ አልይ ብለው ከተማውን ለማጽዳት ደፋ ቀና ይሉ የነበሩ ፣ ገበታ የመሰለ ጎዳና ለማየት የናፈቁ ፣ አፍንጫቸውን አታሽትት ብለው ገሥጸው ፣ ኩሩ እጃቸውን “ቆሻሻ ብትነካ በውኃ የማይጸዳ የለም” ብለው መክረው ፣ እኛ የጣልነውን ያነሡ ፣ እኛ ያቆሸሽነውን ያጸዱ ፣ በነቀሉት አረም አበባ የተከሉ ፣ በቆሻሻው ክምር ፋንታ የማረፊያ ሣር የተከሉ ዛሬ ወዴት አሉ ? የገዛ ቆሻሻችንን ሲያነሡ “ተለክፈው ነው” ያልናቸው ፣ “ክብራቸውን አይጠብቁም ወይ?” ብለን ያዋረድናቸው ፣ “እናንተ የቆሻሻ ፖሊስ” ብለን የሰደብናቸው ዛሬ ወዴት ብን አደረግናቸው ? የኢትዮጵያን ክብር በዓለም መድረክ የጠየቁ ፣ ወራሪዎችን ያጋለጡ ፣ ከሰለጠነው ምድር የአገሬ ጭቃ ይሻለኛል ብለው የተመለሱ ፣ ነጻ ሕዝብ ነን ብለው የሞገቱ ፣  በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኅብረቶች መሥራች የነበሩ ፣ ከእናት አገር የተነጠለችውን ምድር መልሰው የቀላቀሉ ፣ የኢትዮጵያን ሣንቲም ከሚገባን በላይ አንወስድም ብለው የእናት መቀነትን መስረቅ የተጠየፉ የት አሉ ? ኢትዮጵያን ስለማስተዋወቃቸው ቀብራቸው እንዲጠፋ አደረግን ፣ በፍርድ አደባባይ ቆመው ስለ አገራቸው በመሟገታቸው ያለ ፍርድ እንዲገደሉ አደረግን ። በሚሠሩበት ዕድሜ የተቀጠፉ ፣ በሚያማክሩበት ሽምግልና ደብዛቸው የጠፉ ብዙ ወገኖች አሉ ። ኢትዮጵያም መንታ ልጆቿን የዘመን ጎርፍ ወስዶባታልና ጎረቤት አገሮቿ ልቅሶ ከቻሉ እንዲህ ብለው ያልቅሱ፡-

“እቴ ልጆችሽ የት በረሃ ዋሉ ?

ምነው በማለዳው መጠጥ መጠጥ አሉ ፤”

እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ብልጭ ብለው የጠፉ ፣ መጡ ስንላቸው የቀሩ ፣ አበሩ ስንላቸው የጨለሙ ፣ አየናቸው ሲባል የተሰወሩ ፣ ደረሱ ስንላቸው ነደው ያለቁ ፣ ከፍ አሉ ስንላቸው ብናኝ የሆኑ ፣ አገኘናቸው ሲባል መንፈስ የሆኑ ብዙ ልጆች ኢትዮጵያ ነበሩአት ። የጅምር አገር እንጂ የፍጻሜ ምድር አይደለችምና በጥሩ የጀመሩ በጥሩ የማይጨርሱባት ፣ ከፍ ከፍ ያሉ የማይሰነብቱባት ፣ ለጥቂት ጊዜ ታይተው ለዘላለም እልም የሚሉባት ምድር ለምን ሆነች ? እነዚያ ብዕራቸው እሳት የሚተፋ ፣ ቀለማቸው የትውልድን መልክ የሚቀይር ፣ መጽሐፋቸው አፍርሶ የሚሠራ እነርሱም ብዕራቸውም ተደመሰሱ ። የተማሩ ሰዎች ባልተማሩ ፣ የሚጽፉ ሰዎች ፊደል በጠፋቸው ሰዎች እንደ ቆሻሻ ተወገዱ ። “እንኳን መጻፍ ማሰብም ያለብህ እኛ የፈቀድነውን ነው” በሚሉ ጽኑዓን ተገፍተው ወደቁ ። ሸራውን ወጥረው ፣ ዓለምን ሰብስበው ፣ ዘመናትን አዋሕደው ፣ መንፈስን አጉልተው ፣ ሰማይን አንጎዳጉደው ፣ ቅዱሳንን በምድር ጋብዘው ይሥሉ የነበሩ ሠዓሊዎች ዛሬ የሉም ። የለብ ለብ አገር ሁኖ ጥርት ያለ ሥራ የሚሠሩ ፣ እንኳን የሚያሞግሳቸው የሚሰድባቸውም አጥተው ፣ “ማነው የተሳሳተው እኔ ወይስ ጀማው ?” ብለው ራሳቸውን ተጠራጥረው እንዲበንኑ አደረግን ። ኢትዮጵያ እኅት አገር ብታገኝ እንዲህ ተብሎ ቢለቀስላት ይወጣላት ነበር፡- 

“እቴ ልጆችሽ የት በረሃ ዋሉ ?

ምነው በማለዳው መጠጥ መጠጥ አሉ ፤”

ነገሥታቱ በጎ ማሰብ ሲጀምሩ ፣ የአገር ከፍታ ሲታያቸው ፣ የአንድነትን ውል ማሰሪያ ሲያጠብቁ ፣ ድንበራቸውን አስፍተው ሲያዩ ፣ ረሀብን ሊበቀሉ ሲነሡ ፣ ሥልጣኔን አቅርበው ወገንን ለማሳረፍ ሲከጅሉ በወረኞች ስድብ ፣ በካህናት ውግዘት ፣ በመሳፍንት አድማ ፣ በሽፍቶች ሁከት ፣ በመድኃኒተኞች መርዝ ፣ በአገር ልጆች ባንዳነት ፣ በእናት ጡት ነካሾች ፣ ግለሰብን ከአገር ለይተው በማያዩ ጭፍኖች ፣ የጋራ ጠላትን በማይለዩ መንደርተኞች ፣ ያለ አቅማቸው ዙፋን በሚያምራቸው ምንደኞች ተወገዱ ። ያለፉት መቶ ሃምሳ ዓመታትን ብናይ እንኳ በክብር የተቀበረ ንጉሥ ብዙ አልታየም ። በመጡበት ፍጥነት ይሄዳሉ ፣ ቅን ሲያስቡ ይቆረጣሉ ። ሥራ በአገራችን ተጠልቶ ሴራ ዕድሜ የሚያረዝም ሆነ ። ለማይወደው መሪ የሚሰግድ ወገን ፣ የማይወደውንም ሕዝብ የሚመራ መሪ ተከሰተ ። ላለማደግ ተጠንቅቀን ስለምንጓዝ ፣ የድንጋይ ብርድ ልብሱን አንሥተው ፣ ከመቃብር ሊያወጡን የሚከጅሉትን “ምነው ረበሻችሁን ?” ብለን አጠፋናቸው ። የሚሠራ እንደሚሳሳት ፣ የማይሠራ ግን እንደማይሳሳት ፤ የሚራመድ እንደሚደናቀፍ ፣ ከመቀመጫው የማይነሣ ግን እንደማይደናቀፍ ገና አላስተዋልንም ። 

መሳፍንት ከመሳፍንት ፣ ንጉሥ ከንጉሥ ሲዋጉ መሐል ገብተው ፣ ታቦት ተሸክመው ፣ መስቀልን ዓላማ አድርገው ጦርነትን የሚያበርዱ እነዚያ አባቶች በኖሩበት ምድር ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር እየተባለ ወንድማማች ሲተላለቅ ተዉ ያለ ፣ መክሮ የመለሰ ፣ ገዝቶ ጦርነት ያስቆመ አልተገኘም ። ሃያ ዓመትን በቅጡ ያላጋመሱ እነዚያ ወጣቶች በአደባባይ ወድቀው ቀሩ ። የወደቀው የሰው አካል ብቻ ሳይሆን አገሪቱ የደከመችለት ጭንቅላትም ነው ። ባልገባቸው ነገር የሚሞቱ ልጆች ሲነሡ ገብቷቸው የሚገላግሉ ለምን አልተገኙም ? ኢትዮጵያ ቅኔ የሚያውቅ ልቅሶ ደራሽ ብታገኝ እንዲህ ብለው ያለቅሱላት ነበር፡-

“እቴ ልጆችሽ የት በረሃ ዋሉ ?

ምነው በማለዳው መጠጥ መጠጥ አሉ ፤”

ጎበዝ ሰባኪ መጣ ይባላል ስም ቀብተው ፣ ጥላሸት ለቅልቀው ፣ ያለ መልኩ መልክ ሰጥተው ፣ ገፍተው ገደል አድርሰው ፣ ገፍትረው ሸለቆ ጥለው “ወደቀ” የሚሉ ብዙ አሰናካዮችን እናያለን  ። የዘመሩ ፣ የሰበኩ ፣ ልጻፍ ፣ ላገልግል ያሉ ዛሬ የሉም ። ምን አቅብጦኝ እዚህ ውስጥ ገባሁ እስኪሉ እንደ አበደ ውሻ አዋከብናቸው ፣ አገሩ እንዲጠባቸው ፣ ሣር ቅጠሉ እንዲጠላቸው አደረግን ። እንኳን ሰዉ የምንጀምራቸው የልማት ሠራዎች ተመርቀው ወዲያው ሥራ ያቆማሉ ። መብራት ልናገኝ ነው ሲባል በወሩ ደለል ሞላ ፣ ቋጥኝ ዘጋው እንባላለን ። ቤት ተሠርቶ ገባን ሲባል ፣ እንደ አውራ ዶሮ በሰው ስጥ የሚጋብዙ ለአስጨፋሪና ለተሳዳቢ “አትንኩኝ” ብለው ይነሰንሱታል ። መንገዱ ተሠራ ሲባል አንጸባራቂ ምልክቶች ተሰረቁ ይባላል ። ባቡር ገባ ሲባል በሀዲዱ ላይ ከብቶች እየተነዱበት በአቅሙ ልክ መሄድ አልቻለም ይባላል ። ኢትዮጵያ እኅት አገሮች ለቅሶ ቢደርሷት እንዲህ ይሏት ነበር፡-  

“እቴ ልጆችሽ የት በረሃ ዋሉ ?

ምነው በማለዳው መጠጥ መጠጥ አሉ ፤”

ለመጀመር የፈራነው ስንጀምረው የማያልቀው ፣ ለማስተማር የደከምንለት ሲማር የምሁር ደንቆሮ የሚሆነው ፣ ጥበብ በቤቱ አደረች የምንለው ሰው በማለዳው ሲጠፋ ስናየው ምንድነው ችግራችን ? ብለን መጠየቅ ያስፈልገናል ። አይለቅላችሁ ብሎ የረገመን ካለ እርግማኑን ማንሣት ያሻናል ። ተከታታይነት ያለው አስተዳደር ፣ ቋሚነት ያለው ሕግ ፣ ያለፈውን የሚያስቀጥል አክባሪነት ፣ የሠራውን የሚያሞግስ አንደበት በጣም ያስፈልገናል ።

እኔም ብዙ ልጆችዋን በማለዳ የቀበረችውን አገሬን እንዲህ እላታለሁ፡- 

“እቴ ልጆችሽ የት በረሃ ዋሉ ?

ምነው በማለዳው መጠጥ መጠጥ አሉ ፤”

ጌታ ሆይ የመፈጸም ጉልበት ሁነን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ