የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምን ላድርግ ?

አባ ፓምቦ አባ እንጦንስን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- “ምን ላድርግ ?” ሽማግሌውም እንዲህ አለው ፡- “በራስህ ጽድቅ አትተማመን ፣ ስላለፈው ድርጊትህ አትቆጭ ፣ ምላስህንና ሆድህን ተቆጣጠር ።
ብዙ ዘርተው ጥቂት ማጨድ ያቃታቸው ፣ ፍቅር ሰጥተው ስድብ የተመለሰላቸው ፣ ለማስደሰት ሞክረው ሰዎች የተከፉባቸው ፣ የቤታቸውን ጣራ በጠገኑ ቊጥር ያፈሰሰባቸው ፣ መልካም ለመሆን ሞክረው አስመሳይ የሚል ስም የተሰጣቸው ፣ ሲያጠፉም ሲያለሙም ምስጋና የተነፈጋቸው ፣… “ምን ላድርግ ?” በማለት ግራ የመጋባት ጥያቄ ያቀርባሉ አባ ፓምቦ ግን “ምን ላድርግ ?” ያለው ለእግዚአብሔር ለመኖር ፣ ለወደደው አምላክ የተመረጠውን ለማድረግ አስቦ ሲሆን ፣ ጥያቄ ግራ የመጋባት ሳይሆን ቀኙን የመምረጥ ነው
ሁለት የደነዙ ቢላዎች እንኳ ሲሳሳሉ ምላጭ ይሆናሉ ሁለት የበረቱ አባቶችማ እርስ በርሳቸው ሲመካከሩ ይኸው ለትውልድ የምክር ብርሃን ይፈነጥቃሉ ድንጋይና ድንጋይ ፣ እንጨትና እንጨት እንኳ ሲፋጭ እሳት ይወጣቸዋል የተቀደሱ አባቶችማ ሲጠያየቁ ረቂቅ የሆነው መንፈሳዊ ኑሮና መንፈሳዊ ውጊያ ፍንትው ብሎ ይብራራል አባ ፓምቦ አባት ቢሆንም ከአባ እንጦንስ ለመመከር ዝቅ ያለ ነበር ለመሞላት ዝቅ ማለት ያስፈልጋል ከወራጁ ከፍ ያለ ማድጋ አይሞላም ዝቅ ያለና ባዶ ሁኖ የቀረበ ማሰሮ ግን ይሞላል በዚህ ጨለማ ባጠላበት ዓለም ላይ የቅዱሳን አባቶች ምክር የሚመራ ኮከብ ነው ኮከቡም የሚያደርሰው ክርስቶስ ጋ ነው ክርስቶስ ጋ የደረሰም ይሰግዳል ፤ ያለውን ሁሉ ይሰጣል
ከመደበኛ የትምህርት መርሐ ግብር ለየት ያለው ጥያቄና መልስ ያለው መማማር ነው ጥያቄና መልስ መምህርና አስተማሪውን የሚያሳትፍ ትልቅ የትምህርት መርሐ ግብር ነው መምህሩ በውስጡ የተደበቀውን እውቀት የሚያወጣው በጥያቄ ነው የመምህሩ መደበኛ ትምህርት ለተማሪዎቼ “ይህ ያስፈልጋቸዋል” ብሎ ያቀረበው ማዕድ ሲሆን ጥያቄ ግን ተማሪው “ይህ ያስፈልገኛል” ብሎ ያማረው ምግብ ነው ጥያቄ የተማሪ የነጻነት ሜዳ ነው የማይረሱ ትምህርቶች በጥያቄና መልስ የሚሰጡ ናቸው አስተማሪው ተማሪውን የሚያውቅበት ፣ የራሱን እውቀትና ምን ያህል ማስተማሩን የሚለካበት ሚዛን ጥያቄ ነው ጥያቄ አስተማሪ ይበልጥ እንዲያነብ ያደርገዋል የሚጠይቅ ተማሪ ሲጠይቅ አላውቅም እያለ ነውና ጥያቄ ትሑት ያደርጋል በርግጥ ለፈተና የሚጠይቁ ያልታደሉ ወገኖች አሉ ጥያቄ ተማሪና አስተማሪን ያቀራርባል የምናመልከው አምላክ ጥያቄን የሚፈራ አምላክ አይደለም
አባ ፓምቦ፡- “ምን ላድርግ ?” ብሎ ጠየቀ ይህ ጥያቄ የእውቀት ጥያቄ ሳይሆን የመለወጥና ክርስትናን ተጨባጭ የማድረግ ጥማት ነው ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ሲያስተምር በትምህርቱ የተነካው ሕዝብ፡- “ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት፡- ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው።” የሐዋ. 2፡37 ምን ላድርግ ? ማለት ልብ ሲነካ የሚቀርብ ጥያቄ ነው አንድ ሰው የክርስቶስ ፍቅር በልቡ ውስጥ ሲጠልቅ ምን ላድርግ ? ይላል
አባ እንጦንስ ካስተላለፈው ምክር አንዱ፡- “በራስህ ጽድቅ አትተማመን” የሚል ነው “ምን ላድርግ ?” ለሚል ጥያቄ ስላለፈው አድራጎትህ አትተማመን የሚል መልስ መስጠቱ የሚገርም ነው ለቀጣይ አድራጎት ለተጠየቀ ጥያቄ መልስ ተደርጎ የተሰጠው ያለፈው በጎነትህ ላይ አትተማመን የሚል ነው የቅዱሳን አባቶች ሁሉ የሠመረ ጎዳና በራሳቸው በጎነት ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቸርነት ላይ መደገፋቸው ነው ነቢዩ ዳዊት፡- “ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም” ብሏል መዝ. 15 ፡ 2 በራስ ጽድቅ መተማመን ባለፈው ያንን አልፌዋለሁ ብሎ አሁን ግን አልወድቅም በሚል ስሜት መዘናጋትም ነው በራስ ጽድቅ መተማመን ማለት ሌሎች ላይ መፍረድና እኔ እሻላለሁ ብሎ ማሰብ ነው
አባ እንጦንስ ሁለተኛው ምክሩ፡- “ስላለፈው ድርጊትህ አትቆጭ” የሚል ነውባለፈው ድርጊትና በተናዘዙበት ስህተት መቆጨት ራስን እየመረዙ መኖር ነው “እንዴት እኔ ይህን አደርጋለሁ ?” ማለትም መመጻደቅ ነው ሌሎች የሚሠሩትን ስህተት ካልሠራን እግዚአብሔር ስለረዳን እንጂ የማይሠራ ሥጋ ስለተሸከምን አይደለም “ባለፈ ክረምት ቤት አይሠራም” እንደሚባል ባለፈው ዘመን መቆጨት ያለውን ዘመን ማቃጠል ነው እግዚአብሔር ይቅርታ እንዳደረገልን ካመንን ከኅሊናችን ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልገንም “የአንድ ግብ መድረሻ ለሌላ መነሻ ነው” ይባላል ንስሐም የኃጢአት መጨረሻ የጽድቅ መነሻ ነው ስለ ክፉ አድራጎት መጸጸት በራሱ በጎነት ነው እየተጸጸቱ መኖር ግን በእግዚአብሔር አለማመን ነው የሚመለስ ሰው እንጂ የማይበድል ሰው አይደለንም
ምላስህንና ሆድህን ተቆጣጠር” ሦስተኛው ታላቅ ምክር ነው ምላስ ባለቤቱን አስሮ የማስቀመጥ አቅም አለው ሕይወትና ሞትም በአንደበት ላይ ነው የምንጓዘው ወደ ተናገርነው ነው ስለዚህ ምላስን መቆጣጠር ይገባል ሆድን መቆጣጠርም ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ ጤንነት ወሳኝ ነው ተገኘ ተብሎ መብላት ፣ እንደ ዔሳው ለምግብ ጎምዥቶ ብኵርናን መሸጥ አይገባም ፍላጎት ገደብ ከሌለው በምድር በሰማይ ከርታታና የማይረካ ሰው ያደርገናል መቆጣጠር በጥንቃቄ መኖርን የሚያመለክት ነው ጠቢቡ፡- “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል ፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል” ይላል ምሳሌ 2፡11
ጌታ ሆይ ፣ በአንደበቴ ሳይሆን በልቤ የታዘብኩት እንኳ ፈተና ሁኖ ይመጣብኛል አለሁ ስል ይበልጥ አልኖርም ስምል ፣ ስገዘት የበለጠ እወድቃለሁ አምላኬ ትላንት የዛሬውን ሕይወቴን እንዲያውክ ፈቅጄለታለሁ በአንደበቴ ላይም ገና ባለሥልጣን አልሆንሁም እባክህን ጌጠኛውን የጽድቅ መጎናጸፊያ አልብሰኝ በዘላለማዊ ክብርህ አሜን
የበረሃ ጥላ 1
መስከረም 1 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ