የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /10

ወዳጄ ሆይ !

ወንጌል ሰባኪዎች ክንፍ የሌላቸው መላእክት ናቸው ። የማይደክሙ መላእክት ሳሉት የሚደክሙትን ፣ የማይበድሉ ሠራዊት ሳሉት የሚበድሉትን ሰባክያን የመረጠ እግዚአብሔር ነው ። እነርሱን መናቅ ምርጫህ ትክክል አይደለም ብሎ እግዚአብሔርን መናቅ መሆኑን አትርሳ ።

ወዳጄ ሆይ !

በደንብ ያላሰርከው በቀላሉ ይፈታል ። በወረቀት ያላሰፈርከው በቶሎ ይረሳል ። በውል ያላተምከው ቃል ብቻ ሁኖ ይቀራል ። እግዚአብሔር እንኳ ኪዳኑን በመጽሐፍ አስፍሯልና ጽሑፍና ፊርማ አለመተማመን መስሎ አይሰማህ ። ሞት የሚባል ድንገተኛ ጥሪ አለና ለቤተሰብህ ችግር እንዳታስቀር በወረቀት ማስፈርን አትርሳ ።

ወዳጄ ሆይ !

ግብዣህ የባለጌ እንዳይሆን ሁለት ባላጋራዎችን በአንድነት አትጥራ ። ሰውን ለማስታረቅ ብዬ ነው ካልህ ሰው የሚታረቀው በሽምግልና እንጂ በአንተ ድግስ አይደለም ። መድኃኔ ዓለም እርቅን የፈጸመው በቃና ዘገሊላ ሳይሆን በቀራንዮ ነው ። በወይን ሳይሆን በደሙ ነው ። ድግስህ ሁከት እንዳይገጥመው የተጣሉ ሰዎችን በአንድነት አትጥራ ።

ወዳጄ ሆይ !

መሬትህ በሚሸከመው መጠን ቤትህን ሥራ ፣ ወዳጅህ በሚችለው መጠን ምሥጢር ንገረው ፣ ተማሪህ ባደገበት መጠን መግበው ። የሌላው የሆነችውን ሴት ላንተ አትመኝ ። ያንን ጥላ ስትመጣ አንተን ጥላህ መሄድ እንደምትችል እያስተማርሃት ነው ። አንቺም የሌላውን ባለትዳር አትመኚ ። ቢመጣም የሚፈልግሽ ለሥጋዊ ደስታ እንጂ ለዘለቄታው አይደለም ። አንቺም ጥበቃው ያደክምሻል ።

ወዳጄ ሆይ !

ሁላችንን ያቀፈ እግዚአብሔር ነውና ሰዎችን እንዳቀፍህ አይሰማህ ። መንፈሳዊ ሞት ከሥጋዊ ሞት እንደሚቀድም እወቅ ። በመንፈስ ሙተው በሥጋ የሚኖሩ አያሌ ናቸውና ። ያመለከው ሰው የምትገረፍበት ጅራፍ ፣ የምትደማበት ጦር ነው ። ትልልቅ ቤተ መንግሥቶች ብትሠራ እንኳ በትንሽ መቃብር እንደምትወሰን አትዘንጋ ።

ወዳጄ ሆይ !

ሰው መሆን በዓለም ላይ ያለው የትልቁ ማኅበር አባል መሆን ነው ። ሰው መሆን ራስንና አገርን ለመግዛት የሚጠቅም ነው ። ሰው መሆን የአምላክ አምሳል ፣ የክርስቶስ ዘመድ መሆን ነው ። ሰው መሆን የሁለት ዓለም ወራሽ መሆን ነው ። ሰው መሆን የመላእክት ወዳጅ የሚያደርግ ነው ። ሰው ሁኖ መፈጠር ፈቃደ ሥላሴ ነው ፣ ሰው ሁኖ መኖር ግን የሰው ምርጫ ነው ።

ያጋሩ